
ከ 6 ሰአት በፊት
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የአዘርባጃን የመንገደኞች አውሮፕላን በመከስከሱ የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ።
በአደጋው 38 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ አውሮፕላኑ የወደቀው በሩሲያ የአየር ክልል ውስጥ ነው።
ለአውሮፕላኑ መከስከስ ሩሲያ ተጠያቂ ስለመሆኗ ፑቲን ያሉት ነገር የለም።
በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር የገና በዓል በተከበረ ዕለት የአውሮፕላን አደጋው ከደረሰ ወዲህ ፑቲን ምንም አላሉም ነበር።
ከአደጋው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት አስተያየት ግን የሩሲያ አየር መከላከያ የዩክሬንን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ለመከላከል ሲሞክር የደረሰ “አሳዛኝ ክስተት” ብለው ገልጸውታል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮድሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው ሩሲያ ስለ ጥቃቱ “ሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ማቆም አለባት” ብለዋል።
አውሮፕላኑ በሩሲያ ቼችኒያ ግዛት ለማረፍ ሲሞክር በአየር መከላከያ መመታቱ ይታመናል።
ወደ ካስፒያን ባሕር ለመሻገርም ተገዷል። ከዚያም በአክታው አቅራቢያ ተከስክሶ ተሳፍረው ከነበሩ 67 ሰዎች 38 ሞተዋል።
አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች ከአዘርባጃን ሲሆኑ፣ የሩሲያ፣ ካዛኪስታን እና ኪርጊስታን ዜጎችም ይገኙበታል።
አብዛኛዎቹ የተረፉት ሰዎች የተቀመጡት አውሮፕላኑ ጀርባ አካባቢ እንደነበር ይታመናል።
- ኢትዮጵያዊያን እጃቸውን ዘርግተው ጎብኚዎችን ወደሚቀበሉት አገራት ለመግባት ቪዛ ያስፈልጋቸዋል?ከ 7 ሰአት በፊት
- ጎዳና ላይ ሰው የሚቃጠልባት በወሮበላ ቡድኖች ቁጥጥር ስር የምትገኘው የሄይቲ መዲናከ 7 ሰአት በፊት
- ዶክተር ቴድሮስ እስራኤል በየመን ከፈጸመችው የአየር ጥቃት “በሕይወት ለመትረፌ እርግጠኛ አልነበርኩም” አሉ28 ታህሳስ 2024
የበረራ ቁጥር ጄ2-8243 ከአዘርባጃን መዲና ባኩ ግሮንዚ እየተጓዛ ሳለ ተኩስ ሲከፈት ነው አቅጣጫ የለወጠው።
ፑቲን ከአዘርባጃን ፕሬዝዳንት ኢልሐም አልየቭ ጋር መነጋገራቸውን ክሬምሊን አስታውቋል።
“በሩሲያ የአየር ክልል ይህ የከፋ አደጋ በመድረሱ የተሰማቸውን ሀዘን ፑቲን ገልጸዋል። ለሞቱት ሰዎች ቤተሰቦች መጽናናትና እና የተጎዱት በአፋጣኝ እንዲያገግሙ ምኞታቸውን ገልጸዋል” ብሏል።
እምብዛም ሀዘናቸውን ሲገልጹ የማይሰሙት ፑቲን በሰጡት መግለጫ አውሮፕላኑ ግሮንዚ ለማረፍ እየሞከረ እንደነበር ተናግረዋል።
የግሮንዚ፣ ሞዝዶክ እና ቭላዲካቭካዝ ግዛቶች በዚያ ወቅት በዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት እየተፈጸመባቸው እንደነበር ተናግረዋል።
“የሩሲያ የአየር ኃይል ጥቃቱን ለለመከት ምላሽ ሰጥቷል” ብለዋል ፑቲን።
ዩክሬን ግን አውሮፕላኑ ላይ የደረሰው ጉዳት “የሚሳዔል ጥቃት ምልክት ስለሚያሳይ ሩሲያ ግልጽ ማብራሪያ መስጠት አለባት” ብላለች።
የሩሲያ አቪዬሽን ባለሥልጣኖች በአካባቢው ያለው ውኔታ በዩክሬን ድሮኖች ምክንያት “እጅግ ውስብስብ ነው” ብለዋል።
የአዘርባጃን የበረራ ባለሙያዎች እንዳሉት የአውሮፕላኑ ጂፒኤስ ከተጠለፈ በኋላ በሩሲያ ሚሳዔል ተመቷል።
አዘርባጃን በቀጥታ ሩሲያን ተጠያቂ ባታደርግም የአገሪቱ ትራንስፖርት ሚኒስቴር አውሮፕላኑ ለማረፍ ሲሞክር “ከውጪ ጣልቃ ገብነት ገጥሞታል” ብለዋል።
የአሜሪካ መከላከያ ባለሥልጣኖች ሩሲያ ተጠያቂ ናት ብለው ያምናሉ።
ሩሲያም አዘርባጃንም ምርመራ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ፑቲን ንግግር ከማድረጋቸው አስቀድሞ የአዘርባጃን አየር መንገዶች ወደ ሩሲያ የሚያደርጉትን በረራ ሰርዘዋል።
ምርመራው እስከሚጠናቀቅ በረራ አይኖርም ተብሏል።