
ከ 1 ሰአት በፊት
የግብፁ ፕሬዝደንት አብድል ፋታህ አል-ሲሲ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የገቡትን ስምምነት “በቅርበት እየተከታተሉ እንደሆነ” ተናገሩ።
አል-ሲሲ ይህን ያሉት ከፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማኽሮን ጋር በነበራቸው የስልክ ልውውጥ እንደሆነ አናዶሉ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የግብፁ ፕሬዝደንት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አሸማጋይነት የገቡትን ስምምነት ጠቅሰው “[ስምምነቱ] በአፍሪካ ቀንድ ፀጥታ እና መረጋጋት ሊያመጣ እንደሚችል ተስፋ እንዳላቸው” ፅሕፈት ቤታቸው ዘግቧል።
ፕሬዝደንት አል-ሲሲ እና ፕሬዝደንት ማኽሮን ቅዳሜ ዕለት በሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ፣ በጋዛ እና በሶሪያ ስላለው ሁኔታ በስልክ ውይይት ማድረጋቸው ተዘግቧል።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ከጥቂት ሳምንት በፊት ቱርክ ተገኝተው የአንካራ ስምምነት እንደፈረሙ ይታወሳል።
አል-ሲሲ ይህ ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ “መረጋጋት እንደሚያመጣ” ተስፋ ጥለው “ዓለም አቀፍ ሕግን ተከትሎ ሊሆን እንደሚችልም” እምነት እንዳላቸው መግለፃቸውን አናዶሉ አስነብቧል።
ፕሬዝደንቱ “በአፍሪካ ቀንድ ያለው መረጋጋት እና የግብፅ ብሔራዊ ጥቅምት የተሳሰሩ ናቸው” ማለታቸውም ተዘግቧል።
አል-ሲሲ “ለሶማሊያ ድጋፍ ለማድረግ እየሠሩ” እንደሆነ ጠቅሰው ይህ ድጋፍ “በሁለትዮሽ ግንኙነት አሊያም በአፍሪካ ሕብረት የሰላም አስከባሪ ሚሽን” አማካይነት እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማኽሮን ባለፈው ሳምንት ወደ አዲስ አበባ አቅንተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር መምከራቸው ይታወሳል።
- የጸጥታው ምክር ቤት ለአዲሱ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ፈቃድ ሰጠ28 ታህሳስ 2024
- ኢትዮጵያዊያን እጃቸውን ዘርግተው ጎብኚ ወደሚቀበሉት አገራት ለመግባት ቪዛ ያስፈልጋቸዋል?ከ 7 ሰአት በፊት
- በደቡብ ኮሪያ አንድ አውሮፕላን ሲያርፍ ባጋጠመው አደጋ 167 ሰዎች ሞቱከ 7 ሰአት በፊት
የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) የተባለው ሰላም አስከባሪ ኃይል በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት እንደሚሰማራ ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ የተሰማራው አትሚስ የተባለው የሰላም አስከባሪ ኃይል ከኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ብሩንዲ እና ጂቡቲ ወታደሮች የተውጣጣ ነው። የሰላም አስከባሪው ኃይል አል-ሸባብ የተባለውን ታጣቂ ቡድን የሚያደርሳቸውን ጥቃቶች ሲመክት ቆይቷል።
ለቀጣዪ ተልዕኮ አውሶም የሚሰማሩ ወታደሮች ከየትኛው አገር እንደሚሆኑ የመምረጥ ኃላፊነቱ የሶማሊያ ሲሆን ኢትዮጵያ በዚህ ተልዕኮ ወታደሮቿን ታሳትፋለች የሚለው እስካሁን አልታወቀም።
ኢትዮጵያ በአትሚስ ስር 3 ሺህ ያህል ወታደሮችን እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት እስከ 7 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አሰማርታለች።
ኢትዮጵያ እና ነፃ ሀገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ ባለፈው ዓመት ጥር የገቡትን ስምምነት ተከትሎ የአዲስ አበባ እና ሞጋዲሹ ግንኙነት እጅጉን ሻክሮ ቆይቷል።
ነገር ግን በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ አጋማሽ በቱርኩ ፕሬዝደንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን አሸማጋይነት ሁለቱ ሀገራት የአንካራ ስምምነት ፈርመዋል።
ግብፅ በአዲሱ የሰላም አስከባሪ ኃይል (አውሶም) ውስጥ በመካተት ሠራዊቷን እንደምታሰማራ የግብፁ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከቀናት በፊት መናገራቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ፊርማቸውን ባኖሩበት የአንካራ ስምምነት መሰረት፤ “ሶማሊያ በአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ስር ሆነው በአገሯ የተሰማሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች መስዋዕትነት ዕውቅና ትሰጣለች።”
ከዚህ በተጨማሪ ስምምነቱ “የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላላፊያ ማግኘቷ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ሁለቱ አገራት ዕውቅና ይሰጣሉ” ሲል ያትታል።