በጆርጂያ ዋና መዲና ቲብሊሲ የሚገኘው ሆሊ ትሪኒቲ ካቴድራል ቤተ-ክርስትያን
የምስሉ መግለጫ,በጆርጂያ ዋና መዲና ቲብሊሲ የሚገኘው ሆሊ ትሪኒቲ ካቴድራል ቤተ-ክርስትያን

ከ 7 ሰአት በፊት

ከቱሪዝም ጋር በተያያዘ በአንዳንድ አገራት “በጣም ብዙ ጎብኚ መጣብን” በሚል ተቃውሞ ማሰማት ጀምረዋል።

በተቃራኒው እኒህ አራት ሀገራት እጃቸውን ዘርግተው ጎብኚዎችን እየተቀበሉ ይገኛሉ።

እንደጣሊያን እና ስፔን ያሉ የቱሪስት መስህቦችን ለመጎብኘት ረዣዥም ሰልፎችን መሰለፍ ይጠይቃል። ተመሳሳይ የቱሪስት መስህብ ኖሯቸው በቀን አንድም ሰው የማያገኙ ስፍራዎችም ጥቂት አይደሉም።

ባላደጉ አገሮች ከቱሪዝም የሚገኘው ገንዘብ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችንና የማኅበረሰብ መገለግያዎችን ለመገንባት ይረዳል። ሥራ ይፈጥራል፤ ስልጠናዎችን ያስገኛል። የአካባቢው ነዋሪዎች ባህል እና ወጋቸውን በኩራት እንዲያካፍሉም ዕድል ይሰጣል። በጥሩ መንገድ ከተመራ ቱሪዝም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ትልቅ ሊሆን እንደሚችል እሙን ነው።

እነዚህ አራት መዳረሻዎች ቱሪዝምን በመጠቀም ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት እና ጎብኚዎችን በክብር ተቀብለው ለማስተናገድ ከተዘጋጁ በጣት ከሚቆጠሩ አገራት መካከል ናቸው።

ለመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ጎብኚዎች ወደእነዚህ ሀገራት ለመግባት ቪዛ ያስፈልጋቸዋል? እንዴትስ ሊያገኙ ይችላሉ?

ግሪንላንድ

ግሪንላንድ

ዋና ከተማዋ ኑክ አዲስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እአአ በ2026 ታገኛለች። የቱሪስት መናኸሪያዋ ኢሉሊሳትም ሌላ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ታገኛለች።

ይህንን ተጠቅማ ግሪንላንድ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣውን ጎብኝዎቿን ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ ነች። ይህ ከዚህ ቀደም ትልልቅ አውሮፕላኖችን የሚያስተናግድ አውሮፕላን ማረፊያ ላልነበራት ግሪንላንድ በቱሪዝም ዘረፍ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።

አውሮፕላን ማረፊያው ብዙ ቱሪስቶች ከማስተናገድ ባለፈ ለገቢ እና ለወጪ ንግድም ትልቅ እገዛ በማድረግ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል። ግሪንላንድ በሁለት ዋና ዋና የቱሪዝም ዓይነቶች ላይ አተኩራለች። የመጀመሪያው በምስራቃዊ ግሪንላንድ የሚደረግ ጉዞን እና አሳ ነባሪን መመልከትን ሲያካትት ሌላኛው ደግሞ የኮከብ እና የሰሜን መብራቶችን ዕይታን ይመለከታል።

ከተለመደው ክረምት ጊዜ በተጨማሪ በበጋ ወቅት ቱሪስቶች እንዲጎበኙ በማድረግ የአካባቢው ሰዎች ዓመቱን ሙሉ ሥራ እንዲኖራቸው ለማስቻል ቱሪስቶች ሁሌም መምጣት አለባቸው።

ጸሀይ በማትወጣበት እና የሙቀት መጠኑ ወደ -50 ዲግሪ ሴልሺየስ በሚሆንበት ወቅት ጎብኚዎችን መሳብ ፈታኝ ሊመስል ቢችልም አገሪቱ ሰማይ የሚያሳዩ ጣሪያ ያላቸው ማረፊያዎችን እና ባህላዊ የበረዶ ቤቶችን በማስተዋወቅ ላይ ትገኛለች።

የቪዚት የግሪንላንድ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ታኒ ፖር የአገሪቱ ዓላማ ቱሪዝምን ለኅብረተሰቡ ጥቅም ማዋል እንደሆነ በመጥቀስ አጽንኦት የተሰጠው ከጥራት ይልቅ ለመጠን እንዳልሆነ ለማሳየት ይፈልጋሉ።

“ኤርፖርቶች ብዙ ወጪ ስለሚጠይቁ ብዙ ቱሪስቶች እንዲመጡ ማበረታታት አለብን። ይህን የምናደርገው ግን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እና የአካባቢው ነዋሪ ሳይጨናነቅ ነው” ይላሉ።

ፖር በቅርቡ በሰሜን ግሪንላንድ ያለውን የጉዞ መሠረተ ልማት ተመልክተው ተመልሰዋል።

“አንድ ሺህ ነዋሪዎች ወዳሉባት ካሲጊያንጉይት ከተማ ሄጄ ነበር፣ በጣም ጥሩ ነበር። በአካባቢው ሙዚየም ውስጥ ታሪካዊ ትርኢቶች እና ብዙ ዓሣ ነባሪዎች አሉ። ዓሣ ነባሪዎቹን ሳላያቸው በፊት ከክፍሌ ሆኜ ሰማኋቸው። በሄድንበት ሁሉ ነበሩ” ብለዋል።

ወደ ግሪንላንድን ለጉብኝት ማቅናት የሻቱ ኢትዮጵያዊያን ቪዛ ማግኘት አለባቸው። ግሪንላንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ኤምባሲ ስለሌላት ቪዛ ማግኘት የሚቻለው በዴንማርክ በኩል እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ጎብኚዎች ከጉዟቸው 1 አሊያም 2 ወር ቀደም ብለው ቢያመለክቱ ይመከራል።

ሞሮኮ፣ ራባት

ሞሮኮ

ሞሮኮ ከስፔንና ፖርቱጋል ጋር በመተባበር የ2030 የዓለም ዋንጫን ከማዘጋጀቷ በፊት የቱሪዝም መሠረተ ልማቷን እያጎለበተች እና አዳዲስ ሆቴሎችን እየገነባች ነው። ውድድሩ ቱሪዝሟን ለማሳደግ ወርቃማ ዕድል እንደሆነ ከመቁጠር ባለፈ በ2030 የቱሪስቶችን ቁጥር በእጥፍ በማሳደግ 26 ሚሊየን ዓመታዊ ጎብኝዎችን ለማግኘት አቅዳለች።

ውድድሩን ለማስተናገድ ሀገሪቱ በትንሹ 100 ሺህ ተጨማሪ አልጋዎች እንደሚያስፈልጋት በመገመት ከበርካታ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ጋር በመስራት እጥረቱን ለመቅረፍ ተጠምዳለች። በዚህ ምክንያትም በርካታ ስመ ጥር ሆቴሎች ከ2030 በፊት የሚከፈቱ ይሆናል።

ሞሮኮ የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ እየሠራች ነው

ባርባራ ፖድቢያል የጉዞ ኤጀንሲው ፍሊ ዊንተር የሞሮኮ ልዩ አማካሪ ሲሆኑ ከ20 ዓመታት በላይ አገሪቷን ጎብኝተዋል። ቱሪዝም ለአገሪቱ ያመጣውን በረከትም ለማየት ችለዋል።

“ቱሪዝም በማራካሽ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። ጎዳናዎች ንጹህ ሆነዋል፤ ሠላማዊ ከመሆን ባለፈ እንደበፊቱ ሰዎች ዕቃ እንዲገዙ አይገፉዎትም። በርካታ ርካሽ በረራዎች ስላሉ በጣም እንደተጨናነቀ ሊሰማዎት ይችላል” ብለዋል።

የሞሮኮ የቱሪዝም ኢንዱስትሪን ለማሳደግ ወደ ማራካሽ የሚደረጉ በረራዎች መጨመር የዕቅዱ አካል በመሆኑ ከተማዋ በቀርቡ እንቅስቃሴዋ ይቀንሳል ተብሎ አይታሰብም። ወደ ዓለም ዋንጫው ስንመጣ ግን ትኩረቱ በአገሪቱ አነስተኛ የጎብኚ መዳረሻ በሆኑትና የስታዲም እድሳት በሚደረግባቸው ካዛብላንካ፣ አጋዲር፣ ፌዝ፣ ራባት እና ታንጊር ከተሞች ላይ ይሆናል።

ከእነዚህ ቦታዎች መካከል ባርባራ ለጎብኝዎች የሚመክሩት የሞሮኮ የባህል መዲና የሆነችውን ፌዝ ነው። ከአጋዲር በቅፅል ስሟ “ትንሿ ማራካሽ” ወደምትባለው ታሩዳንት ሰዎች እንዲጓዙም መክረዋል።

ሞሮኮን መጎበኘት የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን አዲስ አበባ ከሚገኘው የሞሮኮ ኪንግደም ኤምባሲ ቪዛ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።

ሰርቢያ

ሰርቢያ

ሰርቢያ የቱሪዝም ስኬትን ለመመልከት ሩቅ ማየት አይጠበቅባትም። ጎረቤት ክሮሺያ በቂ ናት። የዱብሮቭኒክ ከተማ ግን ከበርካታ ጎብኚ ጋር በተያያዘ ችግር ቢያጋጥማትም፣ ሰርቢያ ዘላቂ ልማት ላይ አጥብቃ እየሠራች የቡድን ቱሪዝምን የሚያበረታቱ ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀት ላይ ትገኛለች።

ይህ የሆነበት ምክንያት የአገሪቱ የቱሪዝም ስትራቴጂ በመቀየሩ ነው። ቀደም ሲል ትኩረቱ በአብዛኛው እንደቤልግሬድ ባሉ የከተማው ተሞክሮዎች ላይ ነበር። ይሁን እንጂ ቱሪዝም የገጠር ኑሮን ለማስፋፋት እና የአነስተኛ ከተማ ኢኮኖሚን ለማሻሻል የሚረዳ መሆኑን በመገንዘብ የተራራ ቱሪዝም እና የገጠር ቱሪዝም የመሳሰሉትን ዋነኛ ትኩረት ሆነዋል።

በኮክስ ኤንድ ኪንግስ የሰርቢያ ልዩ አማካሪ የሆኑት ጆርጅ ኮልቪን “በሰርቢያ ሰዎች ‘ቱሪስት’ የሚለውን ቃል እንደ አዎንታዊ ነገር ያዩታል” ይላሉ።

የአገሪቱ ተራሮች በክረምት የበረዶ ተንሸራታቾችን እና በበጋ የእግር ተጓዦችን ይስባሉ።

ኢኮቱሪዝም እና በኮረብታዎች ላይ የሚደረግ የወፍ እይታ እያደገ ነው። የየአካባቢዎቹ ቢዝነሶች እያደጉ በመሆኑ የሥራ ዕድል ይበልጥ አስተማማኝ እየሆነ ነው። ዓለም አቀፍ ቱሪዝም በ2023 በ20 በመቶ አድጓል።

ኮልቪን ስሊ የአገሪቱ ሁለተኛ ከተማ የሆነችው ኖቪ ሳድ ለጎብኝዎች ይመክራሉ። “በዚህ ክልል ውስጥ የሃፕስበርግ ቅርስ አለ። እንደ ፕራግ እና ቡዳፔስት ያሉ የቸኮሌት መያዣዎችን ያገኛሉ። ቱሪስቶች ግን በብዛት የሉም። ምግቡም የኦስትሪያ ተጽዕኖ አለበት። ለዕይታም የሚማርክ ቦታ ነው” ብለዋል።

ወደ ሰርቢያ ለጉብኝት ማቅናት ያሰቡ ኢትዮጵያዊያን ቪዛ ማግኘት አለባቸው። በአዲስ አበባ የሰርቢያ ኤምባሲ ለጊዜው ሥራ ማቆመኡን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረ-ገፅ ይጠቁማል። ቪዛ ለማግኘት ማመልከት የሚቻለው ኬንያ በሚገኘው ኤምባሲው በኩል አሊያም በኢ-ሰርቪስ ነው።

ጆርጂያ

ጆርጂያ

ከቱርክ፣ ሩሲያ እና አዘርባጃን ጋር በጥቁር ባህር የምትዋሰነው ጆርጂያ ሁሉንም ጎብኚዎች ለመቀበል ተዘጋጅታለች።በ አዲሱ የ10 ዓመት ዕቅድ መሰረት ቱሪስቶች አገሪቱን ብቻቸው ከመጎብኘት ጀምሮ የህዝብ ማመላለሻ እና የመርከብ ወደቦችን በመክፈት ዝግጁ ሆናለች።

“ቱሪዝም በጆርጂያ በአንፃራዊነት አዲስ ነው” ሲሉ የጆርጂያ ዋይልድ ፍሮንቲየተርስ ባለሙያው ናታሊ ፎርድሃም ይናገራሉ።

“በአንፃራዊነት አዲስ የሙያ መንገድን በማቅረቡ በጣም ድንቅ መመሪያዎችን እናያለን። የእሱ አካል ለመሆን በጣም ጓጉተዋል። ጥሩ እንግሊዝኛ ይናገራሉ። ከተለያዩ አካባቢ ከመጡ ሰዎች ጋር እንዴት መላመድ እንደሚችሉ ይማራሉ። እናም ብዙ ጎብኚዎች ጓደኛ ስለሚያገኙ በድጋሚ ለመጎብኘት ፍላጎት አላቸው” ብለዋል።

በማደግ ላይ እንዳለ የቱሪዝም አገር እና በምዕራብ አውሮፓ እንዳለው አይነት መንገድ መሠረተ ልማት ባይኖርም ከቱሪዝም የሚገኘው ገቢ እነዚህን መሰል የመሠረተ ልማቶች እንደሚያስፋፋ ተስፋ አለ።

“ትብሊሲ በዓለም ላይ የምወዳት ዋና ከተማ ናት” ሲሉ ፎርድሃም ይናገራሉ።

“የሚያማምሩ በኮብል ስቶን ያጌጡ መንገዶች፣ እውነተኛ ውበት ያላቸው የጥንት ግንባታዎች፣ ቤተ-መዘክሮች እና ሌሎችም መዳረሻዎች አሉ። ከዛም የከተሞች ዋሻን፣ የሶቪየት የምህንድስና ጥበብ እና ታሪክ አለ። ስታሊን እዚህ ነው የተወለደው። የሰሜን እና ደቡብ ተራሮች፣ የዩኔስኮ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት እና አስደሳቹ ወይን እና ምግብ ጎብኚዎችን ይጠራሉ። የሚታይ ብዙ ነገር ስላለ ቢያንስ የአንድ ሳምንት ጉዞ ያስፈልግዎታ።”

ኢትዮጵያዊያን ወደ ጆርጂያ ለማቅናት ቪዛ ያስፈልጋቸዋል። ይህን ለማድረግ ወደ ጆርጂያ ኢ-ቪዛ ድረ-ገፅ ማቅናት ይጠይቃል። ድረ-ገፁ ሁሉንም መረጃዎች አሟልቶ የያዘ ነው። በኢትዮጵያ የጆርጂያ ኤምባሲ ድረ-ገፅም እንዲሁም በኦንላይን ቪዛ እንዴት እንደሚገኝ የሚጠቁም መረጃ ይዟል።