ዜና
የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ሠራተኞች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በፖሊስ እየታሰሩ መሆኑን ለፓርላማ…

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: December 29, 2024

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ሠራተኞች በሥራ ቦታ ላይ እያሉ ፖሊስ ያለ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በወንጀል ትጠረጠራላችሁ በማለት እንደሚይዛቸው ለፓርላማ ቅሬታ አቀረቡ፡፡

ሠራተኞቹ አቤቱታውን ያቀረቡት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ታኅሳስ 16 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ባደረገው ድንገተኛ ምልከታ ወቅት ነው፡፡

በምልከታው የኮሚቴው አባላት ከተቋሙ ሠራተኞች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ በበረታ የሥራ ጫና ውስጥ ሆነው በዝቅተኛ ወርኃዊ ክፍያና ጥቅማ ጥቅም ውስጥ እየሠሩ ያሉ ሠራተኞች፣ ምንም በማያውቁት ጉዳይ ፖሊስ በድንገት ወደ ተቋሙ በመግባት ያለ መጥሪያ እየያዘ ይወስዳቸዋል የሚል ቅሬታ ቀርቧል፡፡

ከሠራተኞች መካከል አንዱ ‹‹አቤቱታችንን ፓርላማው ይስማውና ሕግ እንዲከበር ያድርግ፣ አንድ ግለሰብ በምንም ዓይነት ጉዳይ ሊጠረጠር ይችላል፡፡ ነገር ግን ሕጉን ጠብቆ ሊጠየቅ የሚገባው ቢሆንም፣ የደኅንነትና የፀጥታ አካል ነን የሚሉ፣ አንዳንዴ የደንብ ልብስ የለበሱ እንዲሁም አልፎ አልፎ ደግሞ ምንም ዓይነት የደንብ ልብስ የሌላቸው አካላት፣ ያለ ምንም ዓይነት መጥሪያና ያለ ተቋሙ ዕውቅና ሠራተኞችን ከተቀመጡበት ወንበር እየወሰዱ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አክለውም ሠራተኞች የሚሠሩበትን ኮምፒዩተር ሳይዘጉ፣ መሳቢያቸውን ሳይቆልፉና ተቋሙ ሳያውቅ ከተቀመጡበት ፖሊስ ይዟቸው እንደሚሄድና በዚህም የተነሳ ሠራተኞች በሥጋት ከተቋሙ እየለቀቁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹በፖሊስ ስም ተቋሙ ውስጥ እየመጡ ‹‹ፖሊስ ነን›› ከማለታቸው ውጪ በግለሰብ ፈቃድ ይታዘዙ ወይም በፖሊስ ተቋም ይታዘዙ ሳይታወቅ የፈለጉትን ሠራተኛ አስነስተው ሲወስዱ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት አያውቅም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የፖሊስና የደኅንነት ተቋማት ሕጉን እንዲያከብሩ ግፊት አድርጉልን ሲሉ የጠየቁት የተቋሙ ሠራተኞች፣ ተጠርጥረው የተወሰዱ ሠራተኞች ነፃ እየተባሉ ሲለቀቁ ለተፈጠረው የሕግ ጥሰት ጠያቂም ተጠያቂም እንደሌለና በዚህም የተነሳ በርካታ ሠራተኞች ከተቋሙ እየለቀቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ተቋም በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር የሚተዳደር ቢሆንም፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ከዓመት በፊት ለራሱ ሠራተኞች መቶ በመቶ የደመወዝ ጭማሪ ሲያደርግ፣ የአገልግሎቱ ሠራተኞች ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ብዙ ጊዜ እሑድንም ጨምሮ እየሠሩ፣ የሚከፈላቸው ደመወዝ እዚህ ግባ የማይባልና እንደ ፍትሕ ሚኒስቴር ጭማሪ አለመደረጉን ተናግረዋል፡፡

ለ50 ሠራተኞች በወጣ ማስታወቂያ 20 ሠራተኞችን ማግኘት አልተቻለም ያሉት የተቋሙ አንድ ከፍተኛ ባለሙያ፣ ፓርላማው መፍትሔ እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ተቋም አገልግሎት ሰጪ ብቻ ሳይሆን ገቢ ሰብሳቢ መሆኑም የተጠቀሰ ሲሆን፣ በ17 ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶቹ በቀን ከሚያስተናግዳቸው ከ6,000 በላይ ባለጉዳዮች ወደ ስምንት ሚሊዮን ብር፣ በዓመት 1.5 ሚሊዮን ባለጉዳዮችን አስተናግዶ ወደ 2.5 ቢሊዮን ብር እንደሚያስገኝ ተገልጿል፡፡

‹‹በሠራነው ልክ ሊከፈለን ይገባል፣ እስከ ማታ አንድ ሰዓት ድረስ እየሠራን ነው፡፡ ሥራው ፋታ የማይሰጥ ነው፣ የሻይና የምሳ እረፍት የለንም፡፡ ሠራተኛ ይለቃል ነገር ግን አይተካም፣ መንግሥት ከሌሎች ተቋማት ጋር እኩል አያየንም፤›› የሚሉ ቅሬታዎችም ተሰምተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው የመስክ ምልከታ መሪ አቶ አደሌ ኦዳ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹አንድ ዋጋ እየከፈለ፣ መስዋዕትነት እየከፈለ ያለ ሠራተኛ በፖሊስ በቀጥታ የሚያዝ ከሆነ ጉዳዩን በትኩረት እናየዋለን፤›› ብለዋል፡፡