ዜና ትግራይና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በኢሰመኮ ላይ ወቀሳና ቅሬታቸውን…

ናርዶስ ዮሴፍ

ቀን: December 29, 2024

በትግራይና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በጦርነቱ ወቅትና ቀጥሎም በኮማንድ ፖስት ደንቦች ከለላ በሕግ የተደገፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በግልጽ ይፋ አለማድረጉ በክልሎቹ የሚኖሩ ሕዝቦችና በክልሎቹ መንግሥታት ዘንድ ቅሬታና ቅያሜ መፍጠሩ ተነገረ።

ኢሰመኮ በወንጀል ተጠርጥረው ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች የሰብዓዊ መብቶች አተገባበርን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄደው ብሔራዊ ምርመራ ሒደት፣ ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦች አተገባበር ላይ  ከተለያዩ ክልሎች ከተሰባሰቡ የፍትሕ አካላት ተወካዮች ጋር ባለፈው ሳምንት ባደረገው ውይይት ላይ ክልሎቹ ቅሬታውን ገልጸዋል፡፡ 

በውይይቱ ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል ዓቃቤ ሕግ ቢሮ ተወካይ አቶ አማኑኤል ኃይለ ሥላሴ፣ ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች የሰብዓዊ መብቶችን በተመለከተ በቀድሞው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ እንዲሁም በሶማሌ ክልሎች የተደረገውን ብሔራዊ ምርመራ ውጤት አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፣ ኢሰመኮንና የተወከሉበትን ክልል በሚመለከት በዋናነት በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ ጉዳዮችን አንስተዋል። 

አቶ አማኑኤል ኢሰመኮ በትግራይ ክልል ምርመራ ያላደረገበትን ምክንያት፣ በኮሚሽኑ ላይ አለ ያሉትን የሕዝብ ቅሬታ፣ ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በክልሉ ፍትሕ አካላት በኩል የተወሰዱ የመፍትሔ ዕርምጃዎችንና ወቅታዊ የፖሊስ ጣቢያዎች፣ የማረሚያ ቤቶችና የፍትሕ አካላትም አፈጻጸምን በተመለከተ ጥያቄዎች የተሞሉበት ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

‹‹ትግራይ ክልል ከጥቅምት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በጦርነት ውስጥ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ከጦርነቱ በኋላም ደግሞ ለሁለት ዓመት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ነበር፤›› ሲሉ ተናግረዋል። 

‹‹ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጸምበት የነበረ ክልል እንደሆነ በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ይታወቃል። ስለዚህ በትግራይ ክልል ሊፈጸም የሚችለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በዚህ ሰነድ ላይ ከቀረቡት ክልሎች ከተፈጸመ ጥሰት በላይ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው፤›› ብለዋል። 

‹‹አገራዊ ምርመራው ሲደረግ ለክልሎች ቅድሚያ የተሰጠው በክልሎች በተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክብደት ከሆነ፣ በትግራይ የተፈጸመውን ማጣራት አይቻልም ወይ? ምክንያቱም በክልሉ ብዙ የውስጥና የውጭ ኃይሎች በመከላከያ፣ በሻዕቢያ ሠራዊት፣ በአማራ ኃይሎች፣ በራሱ በትግራይ ሠራዊት ብዙ ጥሰት የተፈጸመበት ክልል ስለሆነ፣ ይህ የኢሰመኮ ምርመራ በትግራይም መደረግ ነበረበት። ወይም ደግሞ ኮሚሽኑ ይህንን እንዳያደርግ የሚከለክለው ኃይል ወይም ሁኔታ አለ ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል። 

አቶ አማኑኤል በጦርነቱ ጊዜ በትግራይ ክልል ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጸም፣ ኮሚሽኑ ሲያወጣው በነበረው መግለጫ ምክንያት በሕዝቡ ዘንድ ብዙ ቅሬታ እንዳለ አስረድተዋል። ቅሬታውም የተፈጸመው ጥሰት እየታወቀ ኢሰመኮ በግልጽ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ነበረበት ከሚል የመነጨ መሆኑን ተናግረዋል። 

በሰሜን ኢትዮጵያ ሁለት ዓመታት የፈጀ ጦርነትና ተከትለውት በመጡት ዓመታት በታወጁ የአስቸኳይ ጊዜ ክልላዊ ደንቦች ምክንያት የተፈጠረውንም ገልጸዋል። 

‹‹በትግራይ ብዙ ጥሰት ሲፈጸም ነበር፡፡ የተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ አያያዝ ችግር፣ የዘፈቀደ እስር፣ መሰወር፣ ከቤተሰብና ከጠበቃ ጋር እንዳይገናኙ መከልከልና ሌሎችም ጥሰቶች ሲፈጸሙ ነበር፤›› ብለዋል። 

ሐሳባቸውን ሲያጠናክሩም፣ ‹‹እነዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተግባርና በሕግ የተደገፉ ነበሩ። በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ ሦስት ደንቦች ወጥተው ብዙ ጥሰት በሕግ ሽፋን ለማስፈጸም ጥቅም ላይ ውለዋል። በዚህም ሳቢያ በሕግ ሽፋን ብዙ ጥሰት ሲፈጸም ነበር፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ 

‹‹በግልጽ ከቤተሰብም ሆነ ከጠበቃ ጋር የመገናኘትን ጨምሮ የዋስትና መብትም መብት መሆኑ ቀርቶ፣ እንደተለየ ሁኔታ የሚተገበርበት (In Exception) ሒደት ነው የነበረው፤›› ብለዋል። 

በውይይቱ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የመጡ ተወካይም በኢሰመኮ ላይ ተመሳሳይ ቅሬታ አሰምተዋል።

‹‹ካማሺ አካባቢ ወጣ ያለ ከኦሮሚያ ጋር የሚዋሰን ቦታ አለ፣ በርካታ ሰዎች አሉ። የታሰሩ ሰዎች አሉ። ስለእነሱ እንጽፋለን፣ ምላሽ አይሰጡም፡፡ እዚያ አካባቢ ኢሰመኮ ሄዶ መረጃዎችን ይዞ ይመጣል፣ ግን እስካሁን እየጮህን ያለነው እኛ ብቻ ነን። ምንድነው እየሆነ ያለው? እዚህ አካባቢ ያሉ ሰዎች መፍትሔ የማያገኙበት ምንድነው ችግሩ?›› ሲሉ ጠይቀዋል።

‹‹እኛ ዘንድ የኮሚሽኑ ቅርንጫፍ አለ። እኛ አካባቢ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ግድያዎች ለሚዲያው አንድ ቀን እንኳ ሲደርሱ የማናየው ለምንድነው? የእኛን ችግር ለምንድነው ኢሰመኮ ለፌዴራል መንግሥት በሚዲያ የማያደርሰው? ዜጎች እየሞቱ፣ እየተፈናቀሉና ንብረታቸው እየተዘረፈ እያለ፣ ኮሚሽኑ የእኛን ጥያቄዎች ለምንድነው ይፋ የማያደርገው? ብዙ ጊዜ ሚዲያ ላይ ስለእኛ የሚባሉ ነገሮች የሉም። እኛ ዘንድ እስከ 30 ቀበሌዎች ድረስ ይፈናቀላሉ፣ ግን እንዲህ እንዲህ ተደርጓል ተብሎ ለምንድነው ይፋ የማይደረገው የሚል ጥያቄ ነው ያለኝ፤›› ብለዋል።

አቶ አማኑኤል ደግሞ ለጥሰቶቹ እንደ መፍትሔ የተወሰዱ ዕርምጃዎችን በተመለከተ በሰጡት ገለጻ፣ በተለይ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ የጠቀሷቸው የኮማንድ ፖስት ክልላዊ ደንቦች ተግባር ላይ እንዳይውሉ መሰረዛቸውንና መደበኛ የሕግ ሥርዓት እንዲመለስ ተወስኖ ተግባራዊ መደረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ 

ከዚህም በኋላ በአስቸኳይ ጊዜ ደንቡ መሠረት የተፈረደባቸው፣ ክስ የተመሠረተባቸው ወይም ደግሞ በምርመራ ማጣራት ላይ የነበሩ ጉዳዮች ሁሉም በመደበኛ ሕግ እንዲተዳደሩ መደረጋቸውን ገልጸዋል። 

በኮማንድ ፖስት ወቅት ለተፈረደባቸው በሙሉ ውሳኔ ለመስጠት የሚሆን የይቅርታ አሰጣጥ አዲስ ደንብ ፀድቆ፣ ክሱ የተቋረጠ ወይም ክሱ የተነሳ፣ ይቅርታ እንዲሰጥ የተደረገና አሁንም ይህ አሠራር እየተተገበረ እንዳለም ገልጸዋል። 

አቶ አማኑኤል በተለይም ከፖለቲካ እስረኞች ጋር በተያያዘ እንደ ፍትሕ አካል በየዘርፉ ተደጋጋሚ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንዲሰጥና እንዲሰማሩ መደረጉን፣ ጥቆማ ሲደርስም በሕግ መሠረት ጥሰቱን የፈጸሙ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ እየተደረገ ነው ብለዋል። 

ይሁንና ተወካዩ የማረሚያ ቤቶችና የፖሊስ ጣቢያዎች ውድመትና ከፊል ጉዳት፣ እንዲሁም የክልሉን የፍትሕ አካላት የአቅም ማነስ ጠቅሰው ከኢሰመኮ ድጋፍ ጠይቀዋል። 

‹‹በጦርነቱ ምክንያት ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች ወድመዋል፣ የተለያዩ ጉዳቶች ደርሰውባቸዋል። በዚህ ላይ ደግሞ የሰው ኃይል እጥረት አለ፡፡ የአስተዳደርም ሆነ የመርማሪ እጥረት፣ እንዲሁም የአቅም ማነስ ጉዳዮችም አሉ። ስለዚህ ኢሰመኮ በሚችለው አቅም የበጀት ድጋፍም ማድረግ የሚችልበት ወይም ደግሞ ተደጋጋሚ ሥልጠና የሚሰጥበትና የአቅም ግንባታ ድጋፍ የሚሰጥበት ሁኔታ ካለ ይህንን ሊያግዘን ይገባል፤›› ብለዋል። 

የትግራይ ክልል የዓቃቤ ሕግ ቢሮ ተወካይ ላነሷቸው ጥያቄዎችና ሐሳቦች የኢሰመኮ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል። 

በኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሞላልኝ አስማረ ምርመራው ለምን በሁሉም ክልሎች አልሆነም? በሚል ለተነሳው ጥያቄ በምርመራ ወቅት የነበረው ነባራዊ የፀጥታ ሁኔታ ታሳቢ መደረጉን ጠቅሰው፣ ኮሚሽኑ የአቅም ውስንነት እንዳለበት ተናግረዋል። 

‹‹ነፃና ገለልተኛ ብንሆንም እንደ ማንኛውም የመንግሥት ተቋም ስለሆንን ባለን ሀብት (Resource) ላይ ውስንነቶች አሉ። ምርምር ሒደትና ዘዴ አለው፡፡ ለምርምሩ እነዚህን ክልሎች መውሰዳችን የፍትሕ ሥርዓቱ ሪፎርም ስላለ ለእሱ ግብዓት ይሆናል በሚል ነው። ስለዚህ ከዚያ አንፃር ቢታይ ጥሩ ነው፤›› ብለዋል። 

በተጨማሪም በትግራይ ክልል ምርመራው ለምን አልተደረገም በሚል ከክልሉ ዓቃቤ ሕግ ተወካይ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹በብሔራዊ ምርመራው ግኝት እንደ ሰነድ ያስቀመጥነው እውነት ነው በማለት የምርመራ ሥራውን ለማከናወን ተቋማት ይገኙልናል ወይ የሚለውን ታሳቢ  ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡ 

‹‹በትግራይ ክልል ለተነሳውና አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ለምርመራው የሚያስፈልጉት ተቋማት ከማረሚያ ቤት፣ ከፍርድ ቤት፣ ከፖሊስና ከዓቃቤ ሕግ እነዚህ ይገኙልናል ወይ ነው  የሚለውንም ገምግመን ነበር። ስለዚህ እኔ በቀጣይ ምላሽ እንዲያገኝ የሚደረግ ፍላጎት አድርጌ ነው የምወስደው። በቀጣይ ላለው ደግሞ እንሠራለን አንሠራም? እንችላለን አንችልም? የሚለው በኮሚሽነሩ ምላሽ ይሰጥበታል፤›› ብለዋል። 

በኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ኮሚሽነር አብዲ ጅብሪል (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በጥናቱ የተካተቱ ቦታዎችን በተመለከተ ብዙ ጊዜ ምርመራዎች በሚደረጉበት ወቅት ስለናሙና እንደሚያስተምሩ ገልጸው፣ የተፈጠረውን ለማሳየት ይወክላሉ ተብለው በተወሰዱ ናሙናዎች ነው ሁኔታዎች የሚታዩት ብለዋል።

በጥናቱ በተካተቱ ቦታዎች በተቻለ መጠን ያለውን መዋቅራዊ ችግር ለማሳየት ያሉትን ችግሮች ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ፣ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች ያላቸው ሰዎች የነፃነትን መብት በተመለከተ ያሉትን ችግሮች ማወቂያ ሆኖ፣ ችግሩ ከምን የሚነሳ ነው የሚለውን ለማየት ብዙ ሥራዎች በምርመራው መከናወናቸውን አስረድተዋል።

የትግራይ ክልል ጉዳይም ከናሙና አንፃር መታየት እንዳለበት፣ ነገር ግን በምርመራው ወቅት በነበረው የፀጥታ ጉዳይ ምክንያት ለማካተት አለመቻሉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኮሚሽነሩ፣ ‹‹አጽንኦት መስጠት የምፈልግበት ጉዳይ ነው፤›› በማለት፣ ‹‹በመጀመሪያ ብዙ ጊዜ የሚያስቸግረን እንደ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም የሰብዓዊ መብቶችን ማሳካትና መጠበቅ የማን ኃላፊነት እንደሆነ ብዥታ አለ። የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ለምሳሌ ትግራይ ክልልን ከወሰድን ዋናው ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ ስለዚህ ዋናው ኃላፊነቱ በአንደኛ ደረጃ የፍትሕ ቢሮው ነው። ከዚያ አልፎ የሰብዓዊ መብቶችን መከበር ስንጠይቅ ከሁሉ አስቀድመን የምንጠይቀው መንግሥትን ነው። ምክንያቱም አስፈጻሚ አካል ነው መንግሥት፣ መንግሥት ኃላፊነቱ ነው፤›› ብለዋል።