

ማኅበራዊ በፀጥታና በወረርሽኝ ችግሮች የተጎዳው የላሊበላ ከተማ ለገና በዓል አንድ ሚሊዮን እንግዶችን እጠብቃለሁ…
ቀን: December 29, 2024
የኮሮና ወረርሽኝ፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ እንዲሁም ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የአማራ ክልል ጦርነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደደቆሰው የተነገረለት የላሊበላ ከተማ፣ በየዓመቱ ታኅሳስ 29 ቀን ለሚከበረው የገና በዓል አንድ ሚሊዮን ያህል እንግዶች እንደሚጠብቅ አስታወቀ፡፡
ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ፣ ለገና በዓል የሚደረገውን ዝግጅት ስምንት ኮሚቴዎች ተዋቅረው ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከነበሩት ጊዜያት በተሻለ እንግዶች ወደ ከተማው እንዲመጡ ከሚዲያ ተቋማት ጋር በመሆን ማስታወቂያ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም የገና በዓል ከሃይማኖታዊ ባህልነቱ በተጨማሪ ለላሊበላ ከተማ የኢኮኖሚ መሠረትና ለሕዝቡ ማኅበራዊ ሕይወት፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ሆቴሎችና የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ቱሪስት አስጎብኚዎችና ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ ሌሎችም ዝግጅት እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ከተማዋ ከሚደረጉ የአውሮፕላን በረራዎች በተጨማሪ፣ ከባህር ዳርና ከጎንደር ተጨማሪ በረራዎች እንዲኖሩ የከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከተው አካል ጋር መነጋገሩንና ፈቃድ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡
የላሊበላ ከተማ ቱሪዝም በኮሮና ወረርሽኝ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትና በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ያደረሱበት ኢኮኖሚያ ጫና ከባድ እንደሆነ ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት ከ40,000 በላይ የውጭ አገር ቱሪስቶች ይጎበኙት የነበረው የላሊበላ ከተማ፣ ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ በዓመት ወደ 776 ወርዶ እንደነበር፣ የሰሜኑ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ሲገታ ደግሞ በ2015 እና 2016 ዓ.ም. ቢያንስ የተሻለ ቁጥር ያላቸው ቱሪስቶች ይመጡ ነበር ብለዋል፡፡
በ2017 ዓ.ም. አምስት ወራት ላሊበላን 930 የውጭ አገር ቱሪስቶች የጎበኙ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ መረጃ ካለፈው ዓመት በአንፃራዊ የተሻለ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በከተማው አንፃራዊ ሰላም እንዳለ የተናገሩት ኃላፊው፣ በበዓሉ ምክንያት የእንግዶች ቁጥር ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በዚህም በመጪው ሳምንት ለሚከበረው የገና በዓል 1,500 ያህል የውጭ አገርና አንድ ሚሊዮን ያህል የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ይመጣሉ ተብሎ እንደሚገመት ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ የቅዱስ ላሊበላ ገዳም አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ሕርያቆስ ፀጋዬ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያያት፣ ትልቁ እንቅፋት የፀጥታ ችግር ነው ብለዋል፡፡ በ2016 ዓ.ም. ከነበረው የፀጥታ ሁኔታ አንፃር አሁን የተሻለ እንቅስቃሴ በመኖሩ፣ አምና ለገና በዓል ይመጣሉ ተብሎ ሲጠበቁ ከነበሩ ሁለት ሚሊዮን እንግዶች ሩብ ያህሉ ብቻ መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡ በዚህም ያለፈውን ዓመት ግምት ውስጥ በማስገባት በዚህ ዓመት አንድ ሚሊዮን እንግዶች ይመጣሉ የሚል ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡
የደብሩ አስተዳዳሪ የከተማው ሕዝብም ሆነ የቤተ ክርስቲያኗ ሕይወት በቀጥታም ሆነ በተዘዋሪ ከቱሪዝም ጋር የተሳሳረ በመሆኑ፣ የሚመለከታቸው አካላት ቱሪዝሙ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ጥሪ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ ‹‹ማራኪ በሆነው ቅርስና ውብ ሆኖ በሚከበረው የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሕዝበ ክርስቲያኑ፣ ኢትዮጵያውያንና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ገናን በላሊበላ ያክብሩ፤›› ሲሉ ጥሪ አድርገዋል፡፡
ምክትል ከንቲባና የባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊው በበኩላቸው፣ በአማራ ክልል ካለው የፀጥታ ችግር የተቀዛቀዘው የቱሪስት ፍሰት እንዲሻሻል ቅስቀሳ የማድረግ፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በመተባበር የማስተዋወቅ፣ ኤምባሲዎች ያስቀመጡትን የጉዞ ማስጠንቀቂያ እንዲያላሉ ከኤምባሲዎች ጋር በመነጋገር መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡
በከተማው ሙሉ ለሙሉ የኢንተርኔት አገልግሎት መሟላቱን ጠቅሰው፣ የአውሮፕላን በረራ በበቂ ሁኔታ እንዲኖር በአውሮፕላን ትኬት ላይ ተገቢ ያልሆነ ጭማሪ እንዳይደረግ የከተማ አስተዳደሩ ከክልሉ ቱሪዝም ቢሮና ከፌዴራል ተቋማት ጋር በመሆን ውይይት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ ያሉ ሆቴሎች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ ማሳሰቢያ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
በተደጋጋሚ ችግሮች የተጎዳውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃትና ኅብረተሰቡን ለመደገፍ፣ ለሕዝቡ ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የዕለት ዕርዳታ በማቅረብ፣ ሥራ አጥተው ለቆሙ አስጎብኚ ድርጅቶች መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በማገናኘት ድጋፍ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ መከናወኑን፣ በቀጣይ የሰላሙ ሁኔታ ተስተካክሎ ወደ ነበረበት የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲገባ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
አክለውም ከተማዋ ከቱሪዝም በተጨማሪ የኢንቨስትመንት አማራጭ ስለሌላትና የከተማው ማኅበረሰብ የኑሮ መሠረቱ ቱሪዝም በመሆኑ፣ ሕይወትን ወደ ነበረበት ለመመለስ ሁሉም ሰው ለሰላም መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡