ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር) እና ዘለዓለም ሙላቱ (ዶ/ር) ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት

ማኅበራዊ ለታዳጊ ሴቶች የታቀደው የማኅፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት

የማነ ብርሃኑ

ቀን: December 29, 2024

በኢትዮጵያ የማኅፀን በር ካንሰር ከጡት ካንሰር ቀጥሎ ከፍተኛ የኅብረተሰብ የጤና ሥጋት ነው፡፡ የማኅፀን በር ካንሰር ሒውማን ፓፒሎማ በተባለ በቫይረስ  የሚከሰት ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ የሒውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ኢንፌክሽን የሚከሰቱትም በፆታዊ ግንኙነት ወቅት ነው፡፡ ብዙ የወሲብ ጓደኛ መኖር ወይም ቀድሞ የወሲብ ግንኙነት መጀመር ለበሽታው ያለውን ተጋላጭነት የሚጨምሩ ናቸው፡፡

የማኅፀን በር ካንሰር በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ እያለ ምንም ዓይነት ምልክት የማያሳይ በመሆኑ ምርመራ ማድረግና መከተብ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮም ከታኅሣሥ 21 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ዕድሜያቸው ከ9 እስከ 14 ዓመት ለሆናቸው ሴት ታዳጊዎች፣ በትምህርት ቤትና ከትምህርት ቤት ውጪ የማኅፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት በዘመቻ መልክ ለመስጠት አቅዷል፡፡

ይህንን አስመልክቶም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘለዓለም ሙላቱ (ዶ/ር) በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዮሐንስ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የማኅፀን በር ካንሰር በኢትዮጵያ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በገዳይነቱ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል፡፡ ከ15 ዓመት ዕድሜ በላይ ከሆኑ አምስት ሴቶች መካከል አራቱ የቫይረሱ ተጋላጭ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ7,000 በላይ እናቶች በማኅፀን በር ካንሰር እንደሚጠቁና ከእነዚህም መካከል ከአምስት ሺሕ በላይ የሚሆኑት እናቶች ሕይወታቸው እንደሚያልፍም ተናግረዋል፡፡

‹‹የማኅፀን በር ካንሰር በሽታን ከምንከላከልባቸው የተለያዩ ሥልቶች አንዱ ታዳጊ ልጆች ክትባት እንዲያገኙ ማድረግ ነው፤›› ያሉት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማኅፀን በር ካንሰር ክትባት በዘመቻ መልክ መስጠት ከጀመረ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ከ145,250 በላይ ለሚሆኑ 14 ዓመት ለሞላቸው ሴት ልጆች መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡

ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች ክትባቱን አንድ ጊዜ ብቻ ቢከተቡ በቂ መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች ያረጋግጣሉ የሚሉት ኃላፊው፣ በተያዘው ዓመትም ጤና ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የማኅፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ከታኅሣሥ 21 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በከተማዋ እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

በክትባት ዘመቻው 177,933 የሚሆኑ ታዳጊ ሴት ልጆች ክትባቱን ይወስዳሉ ተብሎ የታቀደ መሆኑንም አክለዋል፡፡  

የክትባት አሰጣጥ ሒደቱ ከዚህ ቀደም ሲደረግ እንደነበረው በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ጣቢያዎችና በጊዚያዊ የክትባት መስጫ ቦታዎች ሲሆን፣ የትምህርት ተቋማት፣ ሌሎች አጋዥ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት፣ የሙያ ማኅበራትና አጋር ድርጅቶች ለዘመቻው መሳካት የበኩላቸውን ትብብር እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘለዓለም ሙላቱ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በሁሉም የመንግሥት፣ የግልና ባለቤትነታቸው በሌሎች ተቋማት በተያዙ ትምህርት ቤቶች ክትባቱ የሚሰጥ በመሆኑ፣ መምህራን፣ የትምህርት አመራሩ፣ ሱፐር ቫይዘሮች፣ ወላጆችና ሌሎችም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ለክትባቱ ስኬታማነት ድጋፍና ዕገዛ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡