

ማኅበራዊ ታዳጊዎች ላይ ያነጣጠረው የበይነ መረብ ጥቃት
ቀን: December 29, 2024
በዓለም ከ300 ሚሊዮን የሚልቁ ከ18 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎች የበይነ መረብ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የቻይልድላይት ግሎባል ቻይልድ ሴፍቲ ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ሪፖርቱን ካወጣበት ግንቦት 2016 ዓ.ም. ቀድመው በነበሩ 12 ወራት ውስጥ የሠራው ዳሰሳ እንደሚያሳየው፣ በሕፃናት ላይ በበይነ መረብ የሚደረገው ጥቃትና ብዝበዛ ዓለም አቀፍ ይዘት ቢኖረውም፣ በሥውር የሚከናወን መሆኑ በአብዛኛው እውነታውን ለመለየትና ይፋ ለማውጣት ተግዳሮት ሆኗል፡፡ ይህ ችግሩ ችላ እንዲባል ዕድል ሲፈጥር፣ በአንፃሩ ደግሞ በሕፃናት ላይ የሚፈጸም የበይነ መረብ ጥቃት እንደ ወረርሽኝ እየተስፋፋ ይገኛል፡፡
ዓለም አቀፍ፣ ቀጣናዊና ብሔራዊ ሕጎች የትኛውንም ዓይነት የሕፃናት ጥቃትና ብዝበዛ የሚከለክሉ ቢሆንም፣ ጥቃቱ ዓይነቱን ቀይሮና ቴክኖሎጂን መሠረት አድርጎ ይታያል፡፡
ዓለም የገባችበት የቴክኖሎጂ አብዮት ጥቅሞች እንዳሉት ሁሉ የጎንዮሽ ጉዳትን ይዞ ቢመጣም፣ በተለይ ልጆችና ታዳጊዎች የኢንተርኔት አጠቃቀምን መሠረት አድርገው የሚፈጸሙ የሕፃናት ጥቃቶችና ብዝበዛን አይረዱትም፡፡ ደኅንነቱ በተጠበቀ አጠቃቀም ዙሪያ ያላቸው ግንዛቤም አነስተኛ ነው፡፡
ቴክኖሎጂ ይዞ ከመጣቸው የጎንዮሽ ችግሮች ተጠቃሽ የሆነውን የበይነ መረብ ጥቃት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ አገሮችም አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱንም ይጠቁማሉ፡፡
ኢትዮጵያም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የመከላከል ሥራ ጀምራለች፡፡ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕፃናት መብት ጥበቃ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዘቢዳር ቦጋለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እንደ አገር የሕፃናት መብትና ጥበቃን ከማስከበር አንፃር የተለያዩ የፖሊሲ ማዕቀፎች፣ ስትራቴጂዎች፣ መመርያዎችና፣ ጋይድላይኖች በማዘጋጀት በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ተግባራዊ እንዲሆን እየተሠራ ነው፡፡
ከእነዚህ መካከል አንዱ በሕፃናት ላይ በበይነ መረብ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ጥበቃ እንዲያገኙ መሥራት ሲሆን፣ ለዚህ ራሱን የቻለ ፍሬምወርክና በበይነ መረብ ጥቃት ዙሪያ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚያስችል የሥልጠና ማኑዋሎች ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ተዘጋጅተዋል፡፡
ይህንን ከዩኒሴፍ፣ ከቻይልድ ፈንድና ከሌሎች ጋር በጋራ በመሆን ወደ ክልሎች የማውረድ በተለይ ችግሩ በስፋት በሚታይባቸው በትምህርት ቤቶች፣ በቤተሰብና በማኅበረሰብ አደረጃጀቶች ውስጥ ኅብረተሰቡ ልጆቹን ከችግሩ እንዲከላከል ግንዛቤ የመፍጠር ሥራው ተጀምሯል ብለዋል፡፡
ሕፃናትና ተማሪዎች ቴክኖሎጂን ባልተገባ መንገድ መጠቀም በሚያስከትለው ጉዳት ዙሪያ በትምህርት ቤቶች፣ በሚኒ ሚዲያና በሌሎች ዘዴዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው፣ ያወቁትን ለጓደኞቻቸውና ለቤተሰቦቻቸው እንዲያሳውቁ፣ ለታናናሾቻቸውም ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን ሥራዎች መጀመራቸውን አስታውሰዋል፡፡
በሥውር የሚደረገውን ጥቃት፣ ተጠቂዎች ወጥተው ለመናገር የሚፈሩበት፣ ለሚመለከተው አካል ለመንገር የሚቸገሩበት፣ የት መሄድ እንዳለባቸው የማያውቁበት ሁኔታ መኖሩን በመግለጽም፣ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶችና ሕፃናት በተዘጋጁ የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት የበይነ መረብ ጥቃት ለደረሰባቸው ልጆችም የሥነ ልቦና ድጋፍ አገልግሎት መስጠት መጀመሩንና ጥቃቱ ልዩ ሕክምና የሚፈልግ በመሆኑም፣ በአንድ መስኮት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ባለሙያዎች መሠልጠናቸውን አክለዋል፡፡
ልጆች ራሳቸውን የሚጎዱበት፣ የሚቆዝሙበት፣ ትምህርት በአግባቡ የማይከታተሉበት፣ ከቤተሰብ ያላቸው ግንኙነት የሚቋረጥበትና ከራሳቸው ጋር የሚታገሉበትን አስከፊ የሥነ ልቦና ጫና የሚፈጥረው የበይነ መረብ ጥቃት ችግር፣ ቅርብ ጊዜ የታየና እየሰፋ የመጣ በመሆኑም በቀጣይ ችግሩ የደረሰባቸውን ሕፃናትና ወጣቶች እንዴት እንደግፋለን? የሚለው ላይ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ጥቃቱን የሚፈጽሙ አካላት እንዲቀጡ የሚያስችል አንቀጽ በወንጀል ሕጉ ላይ ባለመኖሩ፣ ይህንን ለማካተት ከፍትሕ አካላት ጋር እየተሠራና ግንዛቤ እየተሰጠ እንደሆነም ወ/ሮ ዘቢደር ገልጸዋል፡፡
እንደ አገር የፍትሕ ፎረም ለማቋቋም እንዲሁም ቀድሞ የነበረውን ለማጠናከር እየተሠራ መሆኑን፣ ፎረሙ ሕፃናት ላይ በበይነ መረብ የሚፈጸም ጥቃት እንዴት ምላሽ ይሰጠዋል? የሕግ አንቀጾች እንዴት መሻሻል አለባቸው? የሚለውን ከፍትሕ አካላት ጋር በመመካከር እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
ፎረሙን ለማቋቋም የመነሻ ሰነድ እየተዘጋጀ ሲሆን፣ በቀጣይ በፌዴራል ደረጃ የፎረሙ አባል ከሚሆኑ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ በፌዴራል ደረጃ፣ በኋላም ክልሎች የራሳቸውን እንደሚያቋቁሙ ጠቁመዋል፡፡
እንደ አገር በሕፃናት፣ በሴቶችና በወጣቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ዓይነት እየበዛና የጥቃት መጠኑ እየጨመረ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ዘቢደር፣ ይህንን የሚከታተል አካል መኖር ስላለበት ፎረሙ ይህንን የሥራው አካል አድርጎ ይይዛል ብለዋል፡፡
በሕፃናትና በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ላይ ይፋ የሆነው ስትራቴጂ መተግበር የጀመረ ሲሆን፣ በዚህ ስትራቴጂ በሕፃናት ላይ የሚደርሱ የበይነ መረብ ጥቃቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራባቸው ተብለው መካተታቸውን ጠቁመዋል፡፡
እንደ ወ/ሮ ዘቢደር፣ በኢትዮጵያ የጥቃቱ ስፋትና መጠን ላይ ጥናት ተደርጎ ቁጥሩ ባይታወቅም ጥቃቱ ይፈጸማል፡፡ ጥቃቱ በጥበብና ረዥም ተግባቦትን ተከትሎ የሚፈጸም በመሆኑ ይፋ አይወጣም፡፡ በበይነ መረብ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ፎቶ በመላላክ፣ በማግባባት የሚጀመረው ግንኙነት፣ በኋላ ቴክኖሎጂን መሠረት አድርገው በሚቀነባበሩ ተንቀሳቃሽ ምሥልና ፎቶዎች ተደግፈው ወደ ማስፈራራት ይቀየራሉ፡፡ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወንዶች የተጠየቁትን ካላደረጉ ‹ምሥሎቹን ይፋ እናደርጋለን› ብለው በማስፈራራት ለተጨማሪ ጥቃትና ብዝበዛ ይጠቀሙባቸዋል፡፡
ልጆች ይህንን ለወላጅ ወይም ለታላቅ የማይናገሩ መሆኑ፣ የፍትሕ አካላት ጋር መሄድ እንደሚቻል አለማወቃቸውና መፍራታቸው፣ ፖሊስ ጋር ጉዳዩን ይዘው ሲሄዱ ለችግሩ ክብደት ሰጥቶ ወደ ፍትሕ ለማድረስ የጎላ ነገር አለመኖሩንም አንስተዋል፡፡
በቻይልድ ፈንድ ከፍተኛ የፕሮጀክት አስተዳደርና ሀብት ማሰባሰብ ባለሙያ አቶ ዓለሙ ዘመነ በበኩላቸው፣ በሕፃናት ላይ በበይነ መረብ የሚደርሱ ጥቃቶችን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ፕሮጀክት ተቀርፆ፣ እ.ኤ.አ. ከ2023 ጀምሮ በ20 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ዓለሙ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየተተገበረ ለሚገኘው ፕሮጀክት መነሻው፣ ዩኒሴፍና ሌሎች አጋር አካላት በሕፃናት የበይነ መረብ ጥቃት ዙሪያ የሠሩት ዳሰሳ ሕፃናት በበይነ መረብ በሚመጣ ጥቃት በሰፊው ሰለባ እየሆኑ ስለመምጣታቸው ማሳየቱና ችግሩን መከላከል እንደሚገባ በመጠቆሙ ነው፡፡
በተለይ ኮቪድ በተከሰተ ጊዜ በርካታ ተማሪ ባለበት ሆኖ በበይነ መረብ የሚማርበት ሁኔታ መፈጠሩ፣ ወላጆችም ስልክ፣ ላፕቶፕና የኢንተርኔት ግንኙነት ሲያመቻቹ ስለጎንዮሽ ጉዳቱና መከላከያው አለመገንዘባቸው አንዳንድ ታዳጊዎችን የችግሩ ሰለባ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
ዳሰሳው ብዙኃን ሕፃናት ስልክና ኢንተርኔት እንደሚጠቀሙ፣ ነገር ግን እንዴት ራሳቸውን ጠብቀው መጠቀም እንዳለባቸው የማያውቁ መሆናቸውን ያሳየ ሲሆን፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ያላወቁ ሕፃናትና ታዳጊዎች ደግሞ ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ ይሆናሉ ተብሎም ታስቧል፡፡
እንደ ዳሰሳው፣ ቴክኖሎጂው ሲቀርብ ከትምህርት ባሻገር ምን ይዞ ሊመጣ ይችላል? ምን ጉዳት ያስከትላል? ግንዛቤው አለ ወይ? የሚሉት ላይ ትኩረት አለመሰጠቱ በበይነ መረብ የሚደርሱ ጥቃቶች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል፡፡
ቻይልድ ፈንድም ይህንን ዳሰሳ ተከትሎ ለቻይልድ ፈንድ ኮሪያ ያቀረበው ፕሮፖዛል ተቀባይነት በማግኘቱ፣ ችግሩን ቀድሞ ለመከላከል ያስችላል ያለውን ፕሮጀክት በትምህርት ቤቶች ውስጥ እየተገበረ ይገኛል፡፡
ችግሩን ለመከላከልም፣ በአዲስ አበባ በሚገኙ የተመረጡ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የአቅም ግንባታና ሥልጠና፣ የማኅበረሰብ ውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የዲጂታል ዕውቀትን ማጎልበት፣ የፖሊሲ ውትወታና በትብብር መሥራት እንዲሁም የበይነ መረብ ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችል የሥርዓት ግንባታ ድጋፍና የመረጃ፣ ትምሕርትና ተግባቦትን ያካተተ የሙከራ ፕሮጀክት እየተተገበረ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅም ተሞክሮውን ወደ ክልል ለማስፋፋት የሚሠራ መሆኑንም አቶ ዓለሙ ተናግረዋል፡፡
መተግበር ከጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ፕሮጀክት ከሳምንት በፊት የተገመገመ ሲሆን፣ በግምገማው ፕሮጀክቱ መተግበር ከጀመረ ወዲህ የተማሪዎች ተሳትፎ እንዲጨምርና የበይነ መረብ ጥቃትን መከላከል በሕፃናት ፓርላማ አጀንዳ እንዲሆን ማስቻሉ ታይቷል፡፡
በፕሮጀክቱ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች መተግበራቸው የመምህራን፣ የወላጆች፣ የተማሪዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ ከማስቻሉም ባለፈ የግንዛቤ ለውጥ እየታየ መሆኑን አቶ ዓለሙ ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱን ከአምስት አገር በቀል ድርጀቶች ጋር እየተገበሩት መሆኑንም ነግረውናል፡፡