

ከ100 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ችግር ውስጥ ላሉበት የቡግና ወረዳ ለተረጂዎች የቀረበ የምግብ ዕርዳታ
December 29, 2024
በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን በቡግና ወረዳ ተከሰተ የተባለው የምግብ እጥረት በርካቶችን ግራ አጋብቶ ነው የሰነበተው፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የምግብ ችግር የገጠማቸው እናቶችና ሕፃናት ምሥሎች ሲሰራጩም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩ በፀጥታ ችግር የተፈጠረ አደጋ ስለመሆኑ ምክንያት የሚያቀርቡ ነበሩ፡፡ ችግሩ የምግብ እጥረት ሳይሆን ወደ አካባቢው የምግብ ዕርዳታ መላክ ባለመቻሉ የደረሰ ነው የሚል መረጃም በአንዳንዶች ቀርቧል፡፡
በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች የምግብ ዕርዳታውን በዘረፋና በሌላም ከኅብረተሰቡ እየነጠቁ ስለሚጠቀሙት ነው ዕርዳታው ያልገባው የሚለውም ጎላ ብሎ ሲደመጥም ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ በተቃራኒው መንግሥት ራሱ ነው የአካባቢውን ኅብረተሰብ ከቦና ዕርዳታ እንዳይገባ አድርጎ የሚያስርበው የሚለውም ድምዳሜ በርካታ መከራከሪያ ይቀርብበታል፡፡
በዚህ ተቃርኖ መካከል ግን ሕዝብ እየተራበ መሆኑ ነው የሚነገረው፡፡ ይህን ደግሞ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ በረድኤት ሥራ ላይ የተሰማሩ ብቻ ሳይሆኑ፣ የመንግሥት አካላትም አረጋግጠውታል፡፡
ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ በአካባቢው የነፍስ አድን ሕክምና በማቅረብ ሥራ ላይ የተሰማራ የአንድ ዕርዳታ ድርጅት ባልደረባ ስለአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ሰፊ አስተያየቱን ለሪፖርተር አጋርቷል፡፡
ረቡዕ ታኅሳስ 16 ቀን 2017 ዓ.ም. ከ12 በላይ አጋር ድርጅቶች ወደ አካባቢው ገብተዋል የሚለው አስተያየት ሰጪው የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የዓለም ጤና ድርጅት፣ ዩኒሴፍ፣ ችግሩን ተረድተው አጣዳፊ ዕርዳታ ለማድረግ መንቀሳቀሳቸውን በመግለጽ ነው የሚንደረደረው፡፡
‹‹ከሰኔ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የሕፃናት ምገባ ፕሮግራም ቆሞ ነበር፡፡ ዓለም አቀፉ የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የሚያቀርባቸው እንደ ኦቲፒ፣ ፕላምፕሌትስ የመሳሰሉ አልሚ ምግቦች ለረዥም ጊዜ ለአካባቢው አልቀረቡም፡፡ ይህ የዩኒሴፍ ምግብ
ሕፃናቱ በምግብ እጥረት ሊከሰት የሚችል ችግርን እንዲቋቋሙ ነው የሚሰጣቸው፡፡ ነገር ግን ይህን ካላገኙ ይሞታሉ፣ ወይም በጤና እክል ተቸግረው ይድናሉ፡፡ በምግብ እጥረት ለሚመጣው ለዚህ ችግር የወተት ሕክምና (ማለትም F-100፣ F-75 በሚባሉ በንጥረ ምግብ በበለፀጉ) ነው ሕፃናቱ ሕይወት አድን ሕክምና የሚደረግላቸው፡፡ ስለዚህ የቡግና ሕፃናት በከፋ የረሃብ አደጋ ላይ ወድቀዋል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ በዚያ ቀጣና የሚንቀሳቀስ የታጠቀ የፋኖ ኃይል ምግቡን ስለሚጠቀም እንዳይገባ አድርጎታል፡፡ ለ17 ወራት የተቋረጠ የምግብ ሥርጭትም በመጨረሻ ዓለም ያየውን ዓይነት የረሃብ ቀውስ በቡግና አድርሷል፤›› ብሏል፡፡
‹‹የዓለም የምግብ ፕሮግራም ወደ ከፋ የምግብ እጥረት ችግሩ ሳይሸጋገር መካከለኛ የምግብ እጥረት ለገጠማቸው ሰዎች የሚቀርብ ፕላምፕ ሰፕ (Plumpy Sup) የተባለ፣ እንዲሁም ለእናቶች የሚሰጥ ሲኤስቢ (CSB) የተባለ ዱቄት ማቅረብ ጀምሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህም የሚቆራረጥ ነበር አቅርቦቱ፡፡ ከ16 ቀበሌዎች ለስምንቱ በነሐሴ ወር ለማቅረብ ተሞክሮ ነበር፡፡ ይህ በፎቶና በምሥል የወጣው አሰቃቂ የሕፃናት ገጽታ የተገኘውም በዚያ ወቅት ምግብ ለመውሰድ ሲመጡ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ነበር “Severe Acute Malnutrition (SAM)” የተባለው አስከፊ የምግብ እጥረት ደረጃ ላይ የደረሱ ሕፃናት መኖራቸው የታወቀው፡፡ የዓለም ምግብ ፕሮግራም አቅርቦት ሳይቆራረጥ ለሁሉም መዳረስ ቢችል እንኳን ችግሩ ሕይወታቸውን አያቆየውም፡፡ የሚያቀርበው ምግብ ዓይነት ዩኒሴፍ ከሚሰጠው ዓይነት ጋር አይገናኝም፡፡ የጤና ባለሙያዎች መድኃኒትም ሆነ ክትባት ለመስጠት በዚህ ሁኔታ አልቻሉም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
‹‹የጤና አቅርቦት የለም፣ ሕክምና የለም፣ መድኃኒት የለም፣ ሆስፒታል የለም፣ አምቡላንስም የለም፡፡ በአጠቃላይ በወረዳው 100 ሺሕ ሕዝብ አለ ይባላል፡፡ የግብርና ቢሮ 110 ሺሕ ሲያደርሰው፣ የጤና ቢሮ መረጃ ደግሞ 101 ሺሕ ይለዋል፡፡ በአጠቃላይ ሆስፒታል የሚያስፈልገው አካባቢ ነው፡፡ ሆኖም ያሉት ጤና ጣቢያዎች አራት፣ ጤና ኬላ ደግሞ 16 ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ መስፋፋትና ማደግ የነበረባቸው ቢሆንም ነገር ግን አካባቢው በጦርነት አዙሪት ውስጥ በመውደቁ ያሉትም ቢሆን ወድመዋል ወይም በቅጡ አገልግሎት አይሰጡም፡፡ ቡግና ወረዳ አንድ ዋና መንገድ ብቻ ያለው አካባቢ ነው፡፡ ከላሊበላ ከተማ ጋር የሚያገናኘው ብቻ ነው፡፡ አካባቢው ከሌላ አጎራባች ወረዳ ወይ ቀበሌ ጋር መገናኘት የማይችል ዝግ የሆነ አካባቢ ነው፡፡ በዚህች አንድ መንገድ ላይ ምንም ነገር እንዳይገባ ከታገደ አካባቢው ችግር ላይ መውደቁ አይቀሬ ነው፤›› ይላል የዕርዳታ ሠራተኛው፡፡
ቡግና በሌላ በኩል ዝናብ አጠር ወረዳም ነው፡፡ ያለፈው ዓመት መኸር ምርት አላመረተም፡፡ በዓመት ከ4,000 እስከ 5,000 ኩንታል ማዳበሪያ አካባቢው ያስፈልገዋል፡፡ ነገር ግን እሱ በመቅረቱ የአካባቢው ገበሬ ሳያመርት ነው ያለፈው፡፡ በዚህ የተነሳ ዘንድሮ የአካባቢው ምርታማነት በቅድመ ምርት ግምገማ መሠረት 30 በመቶ ብቻ እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ የድኅረ ምርት ግምገማው ደግሞ ከዚህ ያነሰ ውጤትም ሊታይበት ይችላል፡፡ ሐምሌ ላይ ከፍተኛ የበረዶና ውርጭ መዝነብ ሁኔታ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ አካባቢው ምርታማነቱ ዘንድሮ ወደ ዜሮ ሊገባም ይችላል፤›› ብሏል፡፡
በበአሁኑ ጊዜ ባንክም ሆነ አካውንት ለማንቀሳቀስ ዝግ ነው፡፡ ይህ ነገር ሦስት ወራት አለፉት፡፡ ማኅበረሰቡ ያለችውን ገንዘብ አውጥቶ የዕለት ጉርስ መግዛት ወይም ቤተሰብ ማሳከም እየቻለ አይደለም፡፡ ቡግና ወረዳ አይና ላይ የባንክ አካውንት የከፈተ በሙሉ አካውንቱ ዝግ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የመንግሥት ሠራተኛውም ተቸግሯል፡፡ ፋኖዎች ባንክ ዘረፉ ተብሎ ነው የተዘጋው፡፡ ባንኩ ብቻ ቢዘጋ እንኳ ችግር አልነበረውም፡፡ ነገር ግን የሰዎች አካውንት ዝግ መደረጉ ችግሩን አክፍቶታል፡፡ ገንዘብ ያለው ሰው ከከተማም አስመጥቶ፣ ተበድሮና ተላልኮ መታከም ይችል ነበር፡፡ አሁን ያለው ግን ሁሉም ነገር ዝግ የሆነበት ነው፤›› ያለው የዕርዳታ ሠራተኛው፣ ‹‹ቡግና በባህሪው ዝናብ አጠር አካባቢ መሆኑ ራሱን የቻለ ችግር ነው፡፡ ማዳበሪያ የመሳሰሉ የምርት ግብአቶች ጋሸና ደርሰው ሳይገቡ እንዲመለሱ ነው የተደረገው፡፡ ሴፍቲኔት (Productive Safety Net Program/ PSNP) የሚባለው ፕሮግራም ያቀፋቸው ሰዎችም ከሐምሌ ጀምሮ ለአምስት ወራት ዕርዳታ አላገኙም፡፡ አቅመ ደካሞችና አጋዥ የሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ለሞት ተዳርገዋል ሁሉ ነው የሚባለው፡፡ ችግሩ የአካባቢው መዋቅር በሙሉ ስለተዳከመና ታች ድረስ ወርዶ የሚያጠና ስለሌለ የጉዳቱን ስፋት በቅጡ ማወቅ አይቻልም፡፡ አብዛኛው አመራር ላሊበላ ነው ያለው፡፡ ከወረዳው 54 ኪሎ ሜትር ላሊበላ ይርቃል፡፡ ርቀው ካሉ ቀበሌዎች በተለይም እንደ ቆቦ ያሉ ቦታዎች ተጨማሪ ከወረዳው 42 ኪሎ ሜትር ስለሚርቁ ወደ 97 ኪሎ ሜትር ከላሊበላ ይርቃል፡፡ አንዳንድ ቦታዎች እስከ 150 ኪሎ ሜትር ይርቃሉ፤›› ሲል ያለውን ችግር ዘርዝሯል፡፡
‹‹ሌላው ችግሩን ያከፋው እንደ ወባ ያሉ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ መቀስቀሳቸው ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ሁሉም በወባ ስለወደቀ ያዘመረችዋን ጥቂት ምርቱንም በቅጡ የሰበሰበ የለም ይባላል፡፡ ሙሉ ቤት ታመው ሕክምናም ሲመጡ መታከም ሳይችሉ ወደ ቤት ተመልሰው ሞታቸውን ለመጋፈጥ የተገደዱ ይኖራሉ፡፡ በየቤቱ ሕፃናት፣ እናቶች፣ አቅመ ደካሞች፣ ታማሚዎችና ሌሎችም በረሃብና በጤና ችግር ለከፋ አደጋ መጋለጣቸውን ከዚህ ተነስቶ መገመት ይቻላል፡፡ ከወረዳው ነዋሪ በትሹ 70ና 80 በመቶው አጣዳፊ ዕርዳታ እንደሚፈልግ ነው የሚገመተው፡፡ በየቀበሌው የተኙ ነዋሪዎችን በቶሎ ለመታደግ ዩኒሴፍ ወደ አካባቢው እንዲገባ የተፈቀደለት በመሆኑ፣ ገብቶ የነፍስ አድን ምግብ እያቀረበ ይገኛል፡፡ በሒደት አቅም አግኝተው ክሊኒክ ለሚመጡ ደግሞ ሕክምና ለመስጠት ጥረት ይደረጋል፤›› ብሏል፡፡
ይህን ሁሉ ሰፊ ማብራሪያ ስለቡግና አካባቢ ሲሰጥ የሚደመጠው ይህ የዕርዳታ ሠራተኛ፣ ሥራውን ለመሥራት በሚንቀሳቀስበት ወቅት የታዘበው በርካታ መሆኑን ነው የተናገረው፡፡ አስተያየት ሰጪው ሲቀጥልም፣ እቅጩን ንገረኝ ካልክ ኮማንድ ፖስቱ ካላገደ በስተቀር ዕርዳታ ለማቅረብ የሚያደናቅፍ አንዳችም የፀጥታ ችግር በአካባቢው አላየሁም፤›› በማለት ይገልጻል፡፡ ‹‹የእኛ መኪናዎችም ሆነ የሌሎች ድርጅቶች ዕርዳታ አቅራቢዎች ይገባሉ፡፡ ትናንት ዩኒሴፍ ገብቷል፡፡ ችግሩ ረሃብ ነው፣ የመድኃኒት እጥረት ነው፣ የፀጥታ ችግር በአካባቢው የለም፡፡ አንድ ጊዜ ክትባት መጣ፡፡ ክትባት ሰጪዎቹ ወደ ወረዳው እንዲገቡም ተደረገ፡፡ በየቀበሌው የተኛው ሕዝብ ግን ከወባ ወረርሽኝ ሊታደጉኝ መጡ ብሎ በደስታ ተቀበላቸው፡፡ ይሁን እንጂ ክትባት እንጂ ሕክምና እንደማይሰጡት ሲያውቅ በተስፋ መቁረጥ ነው የተመለሰው፡፡ በወረዳው የአምቡላንስ ችግር በመኖሩ የታመመን ቀረብ ወዳለ ቦታ ወስዶ ለማሳከምም አይቻልም፡፡ በባጃጅ ኮንትራት ለመሄድ ሕዝቡ እየተገደደ ነው፡፡ ከወረዳው ወደ ከተማ በባጃጅ ለመሄድ ደግሞ ከአሥር እስከ 15 ሺሕ ብር ይጠየቃል፡፡ ሰዎች ሕመሙ ብቻ ሳይሆን የኑሮና የአገልግሎት ውድነቱም ነው እየገደላቸው ያለው፡፡ ወደ ታች ወይም ወደ ቀበሌዎች ከገባህ ብዙ አሰቃቂ ነገር ነው የሚታየው፡፡ በትግራይ ጦርነት ወቅት ከባድ ውጊያ የተካሄደበት ቦታ ነው፡፡ ከዚያ ለማገገም እየጣረ ሳለ ደግሞ ከፋኖ ጋር ሌላ ጦርነት ተጀመረ፡፡ ሰው በዚህ የተነሳ የደረሰበት አደጋ ከፍተኛ ነው፡፡ እርሻው ብቻ ሳይሆን እንስሳቱም ዋጋ አጥተዋል፡፡ ለምሳሌ አምስት ሺሕ ብር ይሸጥ የነበረ ፍየልና በግ ዛሬ ገዥ ካገኘ ከሁለት ሺሕ ብር በላይ አያወጣም፡፡ በአጠቃላይ የአካባቢው ሲስተሙ ነው የተናጋው፡፡ ብዙ ሰዎች በተስፋ ማጣት ውስጥ ወድቀዋል፡፡ በተለይ ወጣቶች የፋኖ አባልና ደጋፊ ነህ እየተባሉ ስለሚሳደዱ ወዴት እንደሚሄዱ ግራ መጋባት ውስጥ ናቸው፤›› በማለት ነው የዕርዳታ ሠራተኛው የተመለከተውንና የታዘበውን በሰፊው የዘረዘረው፡፡
በየወሩ የሚታተመው የእንግሊዘኛው ሪፖርተር መጽሔት ዘጋቢ በቅርቡ በአማራ ክልል ስላለው ሁኔታ ታች ድረስ በየከተማውና በየገጠሩ ተዟዙሮ ሰፊ ቅኝት ያደረገበትን ሪፖርት ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡ በዚሁ ጥንቅር መታዘብ እንደተቻለውም፣ በአማራ ክል በየትኛውም ቦታ መቼ ግጭት፣ መቼ ሰላም እንደሚከሰት፣ እንዲሁም መቼ ደግሞ መደበኛ እንቅስቃሴ እንደሚመለስ መገመት አስቸጋሪ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ፊታቸውን ጭንብል በሸፈኑ የታጠቁ የፀጥታ ኃይሎች ታጅበው በጥብቅ ጥበቃ በኮንቮይ ከቦታ ቦታ እንደሚንቀሳቀሱ መመልከት ተችሎም ነበር፡፡ ለቡግና ቅርብ በሚባሉ እንደ ጋሸና፣ ወልዲያና ድልብ አካባቢዎች ከባድ ውጊያዎች በሚካሄዱበት ወቅት ወደ ቦታው ያቀናው የሪፖርተር ዘጋቢ ሠራዊቱ በተለይም በወሎ አካባቢዎች ጥብቅ ኬላዎችን መሥርቶ ሲጠብቅ አይቶ ነበር፡፡ የክልሉ ባለሥልጣናት በእነዚህ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የሚከተላቸው አጀብና ጥበቃም ከሆሊውድ የጦርነት ፊልሞች ጋር እንጂ ከሌላ ነገር ጋር ሊነፃፀር የማይችል እንደሆነባቸው ነው በመጽሔቱ የተዘገበው፡፡ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያልተደነገገ ቢሆንም፣ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ጥብቅ የሰዓት እላፊና የእንቅስቃሴ ገደቦች ሲተገበሩ መታዘቡን መጽሔቱ ይጠቅሳል፡፡ ትራንስፖርት በቀላሉ ስለማይገኝ የተገኙ መኪናዎች ሁሉ በሕዝብ በተጨናነቀ ሁኔታ እንደሚንቀሳቀሱ ታውቋል፡፡ የመንግሥት ቢሮዎች ባዶአቸውን የሚውሉ ሲሆን፣ በከተሞች አካባቢ አንፃራዊ ሰላምና የጥይት ጩኸት የማይሰማበት ድባብ ቢኖርም በገጠር አካባቢዎች ግን ሁሌም የግጭትና የጦርነት ድባብ የሰፈነ መሆኑም ታውቋል፡፡
በድሮ የሳይንስ ትምህርቶች ማራስመስ (Marasmus) እና ኳሻኮር (kwashiorkor) እየተባለ የተማረ ሰው፣ በአማራ ክልል ቡግና የተከሰተ ተብሎ የተሰራጨውን የሕፃናት ፎቶ ሲመለከት በቀለም የቀሰመው ድቅን እንደሚልበት ይገመታል፡፡ አንገታቸው የሰለለ፣ የራስ ቅላቸውና ሆዳቸው የተነፋ፣ እጃቸውና እግራቸው አጥንቱ እስኪታይ የቀጠነና ዓይናቸው የጎደጎደ ሕፃናት ምሥል በትምህርት ቤት አስከፊ የምግብ እጥረት ምልክቶች በሚል ተማሪዎች እንዲያውቋቸው የሚደረጉ የሳይንስና የኑሮ ዘዴ ምእራፎች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ችግር ከዘመናት በኋላ ምናልባትም ከ1977 ዓ.ም. የረሃብ አደጋ ወዲህ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ ተከስተዋል መባሉ ብዙዎችን ያስደነገጠ ጉዳይ ነው የሆነው፡፡ በዚህ ወቅት ቡግናን ጨምሮ በአማራ ክልል አብዛኛው አካባቢዎች የሰብል ምርት የሚሰበሰብበት፣ ጎተራ የሚሞላበት፣ ሠርግና ሌላም የበዓላት ድግሶች የሚበዙበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በክልሉ ያለው ሁኔታ ፀጥታው የደፈረሰ በመሆኑ ቡግና በከባድ የምግብ እጥረት እንደገጠመው ነው የተረጋገጠው፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለሙ ይመር መረጃ ሲጠየቁ፣ መረጃ የሚሰጠው በኮማንድ ፖስት በኩል ነው የሚል ነበር ምላሻቸው፡፡
ሆኖም በቀናት ልዩነት በአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ በጽሑፍ ይፋ በተደረገ ንግግራቸው፣ በዞናቸው ያለው ዕርዳታ ፈላጊ ቁጥር 80 በመቶ መቀነሱንና ለብዙዎቹ በቂ ዕርዳታ መከፋፈሉን የሚጠቁም ይዘት ነበረው፡፡ የኮሙዩኒኬሽን ገጹ አክሎ እንዳስነበበው ለ110,563 የቡግና ነዋሪዎች ከኮምቦልቻ መጋዘን ተጓጉዞ 16,583 ኩንታል እህል ተከፋፍሏል፡፡ በአካባቢው የፀጥታ ችግር ስለነበር የዕርዳታ ማከፋፈል ሥራው መዘግየቱን ያመለከተው መረጃው፣ ይሁን እንጂ በተደረገው ርብርብ በቂ ዕርዳታ ማድረስ መቻሉን ገልጿል፡፡
የአማራ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሪት ፍቅር አየለ በበኩላቸው፣ በቡግና ወረዳ ተከሰተ የተባለው ረሃብ ከክልሉ ቁጥጥር ውጪ አለመሆኑን ሲናገሩ ተደምጠው ነበር፡፡ አስፈላጊና በቂ ዕርዳታ ለአካባቢው ነዋሪ እየደረሰ ነው ብለዋል፡፡
ተጠሪ የሆኑ መሥሪያ ቤቶች ስለቡግና ይህን መሰል ሪፖርት ባቀረቡ ማግሥት ግን በርካታ አሰቃቂ ምሥሎች በማኅበራዊ የትስስር ገጾች በተለያዩ የዜና አውታሮች መሠራጨት ቀጠሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በአማራ ክልል ምን እየሆነ ነው የሚል ጥያቄ ማስነሳት ጀመረ፡፡ ጉዳዩ ያውም በወሎ አካባቢ መከሰቱ እየተጠቀሰ የወሎ ረሃብ በቡግና ተደገመ የሚል ብይን እስኪሰጥ ድረስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሰጪው በዛ፡፡ ከዚህ አለፍ ሲልም መንግሥት በትግራይ ጦርነት ወቅት ሲሰነዘርበት የነበረው ውንጀላ ከቡግና ጉዳይ ጋር ተያይዞ መነሳትም ጀመረ፡፡
በወቅቱ ‹‹Tigray Siege›› የሚል ስም ተሰጥቶት በነበረው ዓለም አቀፍ ዘመቻ የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹን ከቦ ያስርባል እየተባለ ሲወቀስ ቆይቷል፡፡ ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ በመጠቀም ወንጀል በተደጋጋሚ እየተከሰሰ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር ጉዳዩ ለዓለም አቀፍ ዳኝነት ሲቀርብ መቆየቱም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ መንግሥት የትግራይን ሕዝብ አስራበ፣ የተመድን ምግብ መከልከልና በጦር መሣሪያነት ያለ መጠቀም ስምምነት ጣሰ፣ በሚልም ከባድ ዓለም አቀፍ ጫና ሲካሄድበት መቆየቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
ከዚህ ውዝግብ ገና ያልወጣው መንግሥት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የዞረ ድምር ውጤት ባለቀቃት አገር፣ ከትግራይ ክልል አጋጣሚ ጋር በተነፃፃሪነት እየተነሳ ያለ ክስተት በሰሜን ወሎ ቡግና ወረዳ እንደገና እንዲከሰት ለምን ፈቀደ የሚለው ብዙ እያጠያየቀ ነው የሚገኘው፡፡
የቡግናው ጉዳይ ዓለም አቀፍ ትኩረት መሳብ ሲጀምርና ጫና ሲበረታ፣ የአካባቢው ባልሥልጣናት ዕርዳታ እንዲገባ መፍቀዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ሰኞ ታኅሳስ 14 ቀን ምሽት በብሔራዊ ቴሌቨዥን የተሠራጨው የአካባቢውን ባለሥልጣናት ዋቢ ያደረገ አንድ ዘገባ፣ ስለሁኔታው አፈጣጠርና መንግሥት ስለወሰዳቸው ዕርምጃዎች ብዙ መረጃ ይዟል፡፡ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታዬ ካሳ የምግብ አቅርቦቱ፣ ‹‹የሕፃናት አልሚ ምግቦች ጭምር እንዳይገቡ የተደረገው ዘረፋ ይካሄድበታል ተብሎ ስለታሰበ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ፀደይ ባንክ ቅርንጫፎች በወረዳው መዘረፋቸው ደግሞ ሌላው ገፊ ምክንያት ነበር፡፡ ምርታማነት ዋና ችግሩ የሆነና ዘንድሮም በቂ ምርት ያላመረተ፣ በአብዛኛው በዕርዳታ የሚተዳደር ወረዳ እንደመሆኑ ችግሩ ከፍቷል፡፡ በዚህ የተነሳም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለመከሰት የማይመጥን እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ በወረዳው ተከስቷል፤›› በማለት ነበር አስተዳዳሪው የተናገሩት፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በበኩላቸው፣ ምግብ ማከፋፈሉ በተጠናከረ ሁኔታ እየተካሄደ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ የሰብዓዊ ረድኤት አቅርቦቱ የዘገየው በፀጥታ ችግር ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ዋግ ህምራ፣ ሰሜን ወሎ በከፊልና ደቡብ ወሎ በከፊል፣ እንዲሁም ሰሜን ጎንደር በዕርዳታ ድርጅቶች አማካይነት ነው የረድኤት አቅርቦቱ የሚሸፈነው፡፡ ከዚህ ውጪ ባሉ አካባቢዎች ግን በፌደራልና በክልሉ የዕርዳታ ማስተባበሪያ ተቋማት በኩል ነው አቅርቦቱ የሚካሄደው፤›› ብለዋል፡፡ ዲያቆን ተስፋው፣ ‹‹የቡግና ወረዳ ዕርዳታ አቅርቦትም በእኛ በኩል እየተካሄደ ነው፤›› ብለው፣ አስተማማኝ የምግብ አቅርቦትም እንዳለ ነው ያስረዱት፡፡