የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ሽመልስ አዱኛ

ኪንና ባህል የሰብዓዊነት ምልክቱ የቀድሞው ኢሕዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሽመልስ አዱኛ (1928-2017)

ሔኖክ ያሬድ

ቀን: December 29, 2024

‹‹ሰው ስትሆን ለሌሎች መኖርና መሥራት እንዳለብህ ለአፍታም መዘንጋት የለብህም፡፡››

ይህን ታላቅ ኃይለ ቃል ከዓመታት በፊት ለአንድ ሚዲያ የተናገሩት ሁለገቡ ባለሙያ፣ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ በመንግሥት ሹምነት፣ በሌሎች አገራዊና ዓለማዊ ተቋማት ያገለገሉት አቶ ሽመልስ አዱኛ ናቸው፡፡

የሰብዓዊነት ምልክቱ የቀድሞው ኢሕዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሽመልስ አዱኛ (1928-2017) | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ነፍስ ኄር ሽመልስ አዱኛ የሕይወት ዘመን የላቀ አገልግሎት ሽልማትን ከዓለም አቀፉ ተቋም በተቀበሉበት ጊዜ

‹‹ሽመልስ›› የሚለው የመጠሪያ ስም ከግማሽ ምዕት ዓመት በፊት በኢትዮጵያም ሆነ በውጩ ዓለም ጎልቶ የሚሰማ፣ የሚታወቅ ነበር፡፡

በ1960ዎቹም ሆነ በ1970ዎቹ አጋማሽ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ደርሶ የነበረውንና የብዙዎች ሕይወትን የቀጠፈው ድርቅና ረሃብ ለመግታት፣ ብዙኃኑን ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ከሞተ ሕይወት ለመታደግ ተቋቁሞ የነበረውን የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽንን ባጭሩ ዕማማኮን በዋና ኮሚሽነርነት የመሩ አቶ ሽመልስ አዱኛ ነበሩ፡፡

ለ1966ቱ አብዮት መፈንዳት አንዱ መንሥኤ የነበረው በ1965 ዓ.ም. በወሎ ጠቅላይ ግዛት የደረሰው ድርቅና ረሃብ ለመግታት፣ የንጉሠ ነገሥት መንግሥቱ ብሔራዊ የዕርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ሲያቋቁም በመሪነት የተሰየሙት የአገር ግዛት ምክትል ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሽመልስ አዱኛ ነበሩ፡፡ ድኅረ አብዮት ኮሚቴው ወደ ኮሚሽንነት ሲያድግ መሪነቱን ይዘው ቀጥለውበታል፡፡

በኮሚሽነርነታቸው በዓለም አቀፍ መድረኮች በየአገሮቹ እየዞሩ ዓለም ድጋፉን እንዲሰጥ በዕንባ ጭምር በመታጀብ የድረሱልን ጥሪ ማሰማታቸው ተቀባይነትም አግኝተው ለወገኖች ዕርዳታው እንዲደርስ ማድረጋቸው ገጸ ታሪካቸው ያሳያል፡፡

ዕማማኮን ለ10 ዓመት ያህል እስከ 1975 ዓ.ም. የመሩትና በ1976 ለሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ያስረከቡት አቶ ሽመልስ ዳግም በወሎ፣ በትግራይ፣ በኦጋዴንና አፋር የተከሰተው ድርቅ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ ለረሃብ መጋለጡንና አስቸኳይ ዕርዳታ የሚያስፈልገው መሆኑን በ1975 ዓ.ም. ይፋ አድርገው ነበር፡፡

‹‹ተራበ አሉ ያ ገበሬ

ምሰሶዋ የአገሬ›› እየተባለ በሚነገርበት በዚያው ዘመን አፋጣኝ ምላሽ በአብዮታዊው መንግሥት ባለመገኘቱ ሚሊዮን የሚደርስ ሕይወትን ማሳጣቱ ይታወሳል፡፡

የዕማማኮ ኮሚሽነርነታቸውን ካስረከቡ በኋላ ለሁለት ዓመት ያህል የሕፃናት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ሠርተዋል፡፡

ባህር ማዶ በመሻገርም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ባገኙባት ህንድ ለሁለት ዓመት ያህል በአምባሳደርነት አገልግለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) በተመሠረተበት ዋዜማ በ1979 ዓ.ም. በዘውዳዊው ሥርዓት በመምሪያ ኃላፊነት በሠሩበት የሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር (በደርግ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተባለው) ሚኒስትር ሆነው ሠርተዋል፡፡

‹‹በመልካም አስተዳደር ምስጉን ሰው›› እንደነበሩ፣ ‹‹ቢሯቸውን በዕለተ ረቡዕ ለሁሉም ክፍት አድርገው ችግር አለብኝ ለሚሉ የሚቀበሉ የሕዝብ አገልጋይ›› ነበሩ ብለው ምስክር የሰጡላቸው እንዳሉ በገጸ ታሪካቸው ተጠቅሷል፡፡

ለመንግሥት ፈታኝ የነበረውና ሥልጣኑንም የነጠቀው ኢሕአዴግ በግንቦት 1983 ዓ.ም. መንበሩን ከመጨበጡ በፊት፣ ኢሕዲሪ ባደረገው ሹም ሽር ጠቅላይ ሚኒስትር የተደረጉት አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ከሾሟቸው የካቢኔ አባላት መካከል አቶ ሽመልስ አዱኛን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

አቶ ሽመልስ ከመንግሥታዊ ከፍተኛ ኃላፊነት ጡረታ ከወጡ በኋላ ድሮም በነበሩበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሰማራት በልማትና በሰላም፣ በሰብዓዊነት መስኮች የላቀ አገልግሎት መስጠታቸው ይነገርላቸዋል፡፡

በ1950ዎቹ መሥራች የነበሩት የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ፕሬዚዳንት፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ፕሬዚዳንት፣ ኤችአይቪ ኤድስን ለመግታት የተቋቋመው ‹‹ኦሳ›› የተባለ አገር በቀል ተቋም የቦርድ ሊቀመንበር፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ለማስጠበቅ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር መሥራች ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት፣ በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ አማካሪ እንዲሁም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኃላፊነት አገልግለዋል፡፡

በ2002 ዓ.ም. በተደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫም በግል ተወዳዳሪ ነበሩ፡፡

በምሥራቅ ኢትዮጵያ በቀድሞ አጠራር በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት በጅግጅጋ ከተማ እሑድ ጥቅምት 2 ቀን 1928 ዓ.ም. (13 ኦክቶበር 1935) የተወለዱት አቶ ሽመልስ አዱኛ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በሐረርጌ፣ ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በአዲስ አበባ ጄኔራል ዊንጌት ተምረዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በሥነ ትምህርት የመጀመርያ ዲግሪያቸውን፣ ድኅረ ምረቃም ከህንድ ቦምቤ (ሙምባይ) ታታ ዩኒቨርሲቲ በማኅበራዊ አገልግሎት አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

በ1950ዎቹ አጋማሽ በሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር እየሠሩ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሶሺዮሎጂ ያስተምሩ ነበር፡፡

በ1950ዎቹ መጨረሻና 60ዎቹ መጀመርያ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት በኃላፊነት የሠሩት አቶ ሽመልስ አዱኛ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስፈላጊነትን ሲያስተጋቡ ኖረዋል፡፡ እሳቸውም ማለት ብቻ ሳይሆን በተግባርም አሳይተውታል፡፡ ‹‹የገባነውን ቃልና መግለጫ በተግባር ካላሳየን፣ ማድረግ ያለብንን ባለማድረጋችን የራሳችን ቃላት በእኛ ላይ ይፈርዱብናል፤›› ማለታቸውም ተመዝግቧል፡፡

አቶ ሽመልስ በሕይወት ዘመናቸው ላበረከቱት የላቀ አገልግሎት ከተበረከቱላቸው ሽልማቶችና ዕውቅናዎች መካከል ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር የሄንሪ ዱናንት የላቀ የሰብዓዊ አገልግሎት ሜዳሊያና የጅማ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ይገኙበታል፡፡

ነፍስ ኄር አቶ ሽመልስ አዱኛ ዘመን ገትቷቸው በተወለዱ በ89 ዓመታቸው ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም. አርፈው በማግሥቱ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡

በሳቸው የሚኒስትርነት ዘመን ከእሳቸው ጋር  የሠሩት አቶ ተስፋዬ ድረሴ ባንድ ወቅት በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ እንዲህ ከትበው ነበር፡፡

‹‹ድሆች ናችሁ ያሉን

ድሆች ነን ወይ እኛ   

በእጃችን እያለ ሺመልስ አዱኛ››

(አዱኛ – ሀብት በሚለው ፍቺ)

በአንድ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ አንዱእንደተጻፈው፣ ‹‹አቶ ሽመልስ አዱኛን በጡረታ ዘመናቸው አግኝቶ ስለሠሩት ሁሉ መልካም አመስግኖ ሲጨዋወቱ የሰጡት ቃል እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሰው ስትሆን ለሌሎች መኖርና መሥራት እንዳለብህ ለአፍታም መዘንጋት የለብህም፡፡ እኔም ያን ከማድረግ ውጪ የተለየ ነገር አላደረግሁም፡፡ የገዛ ቤተሰቤ እንደሆኑ አድርጌ መመልከቴ ይመስለኛል ከስሜት ውጪ ያደርገኝ የነበረው፡፡››