
ዜና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ እየተላለፈ ያለው ዕገዳ አሳሳቢ መሆኑ ተገለጸ
ቀን: December 29, 2024
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የተላለፈው ዕገዳ በመደራጀት መብት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርና የሲቪክ ምኅዳሩን እንደሚያጠብ ገልጾ፣ ድርጊቱ እንዳሳሰበው አስታወቀ፡፡ ኮሚሽኑ ዓርብ ታኅሳስ 18 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ተመሳሳይ ይዘት ያለውንና ፈጸሟቸው የተባለውን ከባድ የሕግ ጥሰት በዝርዝር ባላብራራ ደብዳቤ መታገዳቸው አሳሳቢ ሆኖ እንዳገኘው ገልጿል፡፡

ኢሰመኮ በመግለጫው፣ ‹‹በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የሚተላለፉ ዕገዳዎች የሲቪክ ምኅዳሩን እንዳያጠቡና በማኅበር የመደራጀት መብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይፈጥሩ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፤›› ብሏል፡፡
በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩት የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች፣ እንዲሁም ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች፣ የተሰኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በኅዳር ወር ታግደው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ዕግዱ በተነሳ ሳምንት ሳይሞላቸው የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከልና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች የተባሉት ድርጅቶች እንደገና ታግደዋል፡፡ በተጨማሪ የድርጅቶቹን መታገድ ሲያስተጋቡና ወደ ሥራ እንዲመለሱ ሲያሳስቡ የነበሩት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል (EHRDC) ከማንኛውም የሥራ እንቅስቃሴ መታገዳቸውን ድርጅቶቹ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ዕገዳው ከተጣለባቸው ድርጅቶች መካካል የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማጅከል የተሰኘው ድርጅት፣ ‹‹ድርጅታችን ማስጠንቀቂያው ከደረሰው በኋላ አሠራሩን ባለማስተካከሉና ለባለሥልጣኑ ሕግና ውሳኔ ተገዥ አልሆነም፤›› የሚል ዕገዳ ደብዳቤ እንደደረሰው አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል (EHRDC) የተባለው ድርጅት የታገደው፣ ‹‹ባለሥልጣኑ በድርጅቱ ላይ ባደረገው የክትትልና ግምገማ፣ ድርጅቱ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጭ መንቀሳቀሱ፣ ገለልተኛ አለመሆኑ፣ ግልጽ የሆነ የአደረጃጀት መዋቅር የሌለው መሆኑና ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የተንቀሳቀሰ መሆኑ በመረጋገጡ›› እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ከዕገዳው በተጨማሪ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶችና የመብት ተሟጋቾች በፀጥታ አካላት የሚደርስባቸው ወከባ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ ምክንያት በርካቶች አገር ጥለው እየተሰደዱ መሆናቸውን የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች፣ የሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞች፣ እንዲሁም የመብት ተሟጋቾች በፀጥታ አካላት ወከባዎች፣ ዛቻዎችና ማስፈራሪያዎች እየደረሱባቸው መሆኑን በመጥቀስ በኢትዮጵያ የሲቪክ ምኅዳሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀጨጨ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
አገር በቀልና ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾችና ድርጅቶች ይህንን ይበሉ እንጂ፣ ተቆጣጣሪው የመንግሥት ባለሥልጣን የቁጥጥር ሥራውን እያከናወነ እንደሆነ በመጥቀስ፣ የሲቨክ ምኅዳሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተሻሻለ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲናገር ይደመጣል፡፡
ባለፈው ወር ሲቪከስ በመባል የሚታወቀውና የዓለም የዜጎች ተሳትፎ ጥምረት የሆነው ተቋም ባወጣው የ92 ገጽ ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ የሲቨክ ምኅዳራቸው ወደ ከፋ ደረጃ እያሽቆለቆለ ካሉ አገሮች በተለይም ፍልስጤም፣ ኬንያ፣ ፔሩ፣ ኔዘርላንድስ፣ ቡርኪናፋሶና ኢስቲዋኒ ተርታ መሠለፏን መግለጹን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡
ኢሰመኮ በመግለጫው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የሚተላለፉ ተደጋጋሚ ዕገዳዎች የሲቪክ ምኅዳሩን በማጥበብ በማኅበር የመደራጀት መብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድሩ፣ ባለሥልጣኑ የድርጅቶቹን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አደጋ ላይ በማይጥል መንገድ፣ የምርመራ ሥራዎቹን በተቻለ ፍጥነት አጠናቆ ወደ ሥራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ጥሪ አስተላልፏል፡፡