
December 29, 2024

መንግሥት ታክስ የመሰብሰብ አድማሱን ለማስፋት መወሰኑን ተከትሎ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያየ ይዘት ያላቸው ቅሬታዎች በገቢ ሰብሳቢ የመንግሥት ተቋማት ላይ እየቀረበ ይገኛል፡፡ በተለይም የግንዛቤና የማስተዋወቅ ሥራ ሳይሠራ በቀጥታ በሚወርዱ መመርያዎችና ትዕዛዞች የተጋነነ የታክስ ክፍያ እንዲከፍሉ እየተጠየቁ መሆናቸውንና በዚህም መቋቋም ከሚችሉት በላይ ዕዳ እየተከናነቡ መሆናቸውን የሚገልጹ የንግድ አንቀሳቃሾች የቅሬታ ድምፆች ካለፉት ጥቂት ወራቶች ወዲህ እየጨመሩ መጥተዋል።
ከሰሞኑም የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ በአዲስ ተሽከርካሪዎች ግብይት ላይ የሚከፈል ታክስን ለመወሰን ካወጣው የዋጋ ሥሌትና የአሠራር ሥርዓት አተገባበር ጋር በተገናኘ የተፈጠረ አለመግባባት መኖሩን ሪፖርተር ባዳረገው ምልከታ አረጋግጧል፡፡
ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ የመኪና አስመጪዎች ለሪፖርተር በግንባር ቀርበው እንዳስረዱት፣ ከዚህ ቀደም በነበሩት የግብር መክፈያ ዓመታት ግብር ወደ አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ሄደው ተሽከርካሪዎችን በሸጡበት ደረሰኝና የጉምሩክ ኮሚሽን በሚያወጣው የዲክላራሲዮን ዋጋ መሠረት ግብር ይከፍሉ እንደነበር አስረድተዋል።
ጉምሩክ ኮሚሽንም ወደ አገር ለሚያስገቡት የሽያጭ መኪኖች የዓለምን ገበያንና ሁሉንም ስታንዳርድና መለኪያዎች መሠረት አድርጎ የተሽከርካሪዎችን የዋጋ ተመን እንደሚያወጣ የሚያስረዱት አስመጪዎቹ፣ ቀረጥም የሚከፍሉትም ሆነ የተሽከርካሪዎቹን ለተጠቃሚዎች የሚሸጡት፣ እንዲሁም ትርፋቸውንም የሚያሳውቁት በዚህ በጉምሩክ ኮሚሽን ተመን ላይ በመመሥረት እንደሆነ ተናግረዋል።
ከላይ በተገለጸው መሠረት በገቢዎች ቢሮ ሲስተናገዱ መቆየታቸውን ያስረዱት አስመጪዎቹ፣ የ2016 የበጀት ዓመት ግብር ለማሳወቅ ሲሄዱ ግን አዲስ ወጣ በተባለ መመርያ መሠረት እንደሚስተናገዱ እንደተገለጸላቸው ጠቁመዋል።
‹‹መመርያው ወጣ በተባለበት ወቅት አልተሰጠንም፣ በገቢዎች ቢሮው ድረ ገጽ ላይ የማይገኝ፣ ፍትሕ ሚኒስቴርም ቢጠየቅ ያልመዘገበው፣ በቢሮው ውስጣዊ አሠራር የወጣ ነው፤›› የሚሉት ነጋዴዎቹ፣ መመርያው ላይ የቀረበው የሽያጭ ሥሌት እርስ በርስ ተቃርኖ ያለው፣ የግዥና ሽያጭ ሥሌትን የማያካትት፣ ሽያጭ ላይ ብቻ ያተኮረ ነው ይላሉ፡፡ የግዥና የዚያን ተያያዥ ወጪዎች ያላካተተ፣ ነገር ግን ተሽከርካሪዎቹ ከተሸጡበት በላይ በእጅጉ የተጋነነ ዋጋ እንደተሸጡ ታሳቢ በማድረግ አስመጪዎች በዚህ ዋጋ መሠረት ታክስ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል ‹‹ዘጠኝ ሚሊዮን ብር መክፈል ሲጠበቅብኝ ወደ 28 ሚሊዮን ብር እንድከፍል ታዝዣለሁ፤›› ሲሉ የገለጹ አንድ አስመጪ፣ ‹‹ይህ እንዴት ይሆናል ብለው ቅሬታ ለማስገባት ሲሄዱ መኪናን በተመለከተ ቅሬታ ማስገባት አይቻልም፤›› የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እስከ ላይኛው የቢሮው መዋቅር ቅሬታ ለማቅረብ ያደረጉት ጥረት ‹‹አይቻልም›› በሚል ምላሽ ውድቅ እንደተደረገባቸውም እኚህ ግለሰብን ጨምሮ ሌሎች በርከት ያሉ መኪና አስመጪዎች ተናግረዋል።
ቅሬታቸው ተሰምቶ መክፈል የሚገባቸውን ታክስ እንዲከፍሉ ቢጠይቁም ምላሽ የሚሰጣቸው እንዳጡ፣ ከዚህም አለፍ ታክስ አልከፈላችሁም ተብለው የታክስ ነፃ ክሊራንስ እንዳያገኙ መከልከላቸውን ተናግረዋል።
‹‹ቢሮዎች አሉን፣ ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችም አሉን፡፡ ክሊራንስ አይሰጥም ማለት ከሕጋዊነት ወደ ሕገወጥነት ተቀየርን ማለት ነው፡፡ በመጓጓዝ ላይ የሚገኙ ሌሎች ንብረቶቻችንን እንዴት አስገብተን እንሸጣለን፣ በሥራችን ያሉት ሠራተኞችስ?›› ሲሉ ምሬታቸውን በጥያቄ መልክ አቅርቀዋል።
መኪና አስመጪዎቹ፣ ለምን ይህ አሠራር በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮና በአዲስ አበባ ብቻ ተግባራዊ ይሆናል? ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ‹‹በዚህ ወቅት ሒሳባችን ታግዶ፣ ቅሬታ አንቀበልም ተብለን፣ ክሊራንስ የለንም ተብለን እንገኛለን፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
እነዚህ የመኪና አስመጪዎቹ ጉዳያቸውን/አቤቱታቸውን ይዘው ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዳመሩ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የአዳዲስ ተሽከርካሪዎች የገበያ ዋጋ ሥሌት አሠራር በሚል የተዘጋጀውን መመርያ አስመልክቶ የዕግድ ውሳኔ እንዳስተላለፈ ለሪፖርተር በግንባር ቀርበው የገለጹ ሲሆን፣ የገቢዎች ቢሮ ይኼን የፍርድ ቤት ዕግድ ውሳኔ በዋና መሥሪያ ቤቱ ይዞ ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አለመላኩን አብራርተዋል፡፡
ሪፖርተር የተመለከተውና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሕ ብሔር ምድብ ችሎት በታኅሳስ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. የሰጠው ትዕዛዝ፣ በቁጥር 41 የሚሆኑ አመልካቾች/ከሳሾች የአዳዲስ ተሽከርካሪዎች የገበያ ዋጋ ሥሌት አሠራር ሥርዓት ቁጥር 001/2015 በሚል በተከሳሽ (የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ) የተዘጋጀው መመርያ ኢ-ፍትሐዊነትን የሚያመጣና በአዋጅ ቁጥር 1183/2012 መሠረት ያልተዘጋጀ በመሆኑ እንዲሰረዝ የሚል የክስ አቤቱታንና የዕግድ ትዕዛዝን የያዘ ነው።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው የትዕዛዝ ውሳኔ ላይ እንደተመለከተው፣ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በሰጠው አስተያየት ከሳሾች የክስ አቤቱታ አቅርበንበታል በሚሉት ጉዳይ ላይ ቢሮው ያወጣው መመርያ ሳይኖር፣ መመርያ አውጥቷል በሚል ያቀረቡት ክርክር አግባብነት የሌለው በመሆኑ የዕግድ ትዕዛዝ ሊሰጥ አይገባም ሲል ጠይቋል፡፡
በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በሳለፈው የታክስ ውሳኔ ላይ ቅሬታ ያለው አካል ውሳኔውን ለሰጠው አካል ቅሬታውን ማቅረብ እንደሚችል፣ ቅሬታው ተቀባይነት ካላገኘም በይግባኝ ለግብር ቅሬታ ሰሚና ለፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረብ እንደሚችል በአዋጅ መደንገጉን ጉዳዩን ለተመለከተው ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ የሰጠው ብይን፣ ከሳሾች ክስ ከማቅረባቸው ከታኅሳስ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በፊት የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የሰጠው የግብር ውሳኔ ማስታወቂያ ካለ ውሳኔው በፍርድ ቤቱ የሚታገድበት ሁኔታ እንደማይኖር ያመለክታል። ነገር ግን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከታኅሳስ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ የሰጠው የግብር ውሳኔ ካለ ከሳሾች በግብር ውሳኔው ሳይገደዱ ሊቆዩና የአዲስ ተሽከርካሪዎች የገበያ ዋጋ ሥሌትን ለመወሰን የወጣ የአሠራር ሥርዓት ቁጥር 001/2015 የግብር ውሳኔ ባልተሰጣቸው ከሳሾች ላይ ተፈጻሚ ሊሆን አይገባም በማለት የዕግድ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ሪፖርተር የተመለከተውና በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በሚያዝያ 2015 ዓ.ም. የቀረበው አመክንዮ፣ ተሽከርካሪዎችን አስመጥተው የሚሸጡ ግብር ከፋዮች ተሽከርካሪዎቹን ሸጠው ለገቢዎች ቢሮ በሚቀርቡት ደረሰኝ ላይ የተቀመጠው ዋጋ ከወቅታዊው ትክክለኛ የገበያ ዋጋው እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት፣ መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ገቢ እያጣ መሆኑን በጥናት ማረጋገጡን የሚገልጽ ነው።
የመኪና አስመጪዎቹ በበኩላቸው፣ የገቢዎች ቢሮ የመኪኖች የግብይት ዋጋ ይኼ ነው ብሎ ያወጣው ዋጋ እጅግ በጣም የተጋነነ ሲሉ ይኮንናሉ፣ ማንኛውም አካል ገበያው ላይ ሄዶ ከትንሽ እስከ ትልቅ ያሉ መኪናዎችን ዋጋ መመልከት እንደሚቻል አስረድተዋል።
ሪፖርተር ያነጋገራቸው አስመጪዎች እንደሚገልጹት ፣ ከእነሱ መካከል የተወሰኑት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መኪና ያቀረቡ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ለከንቲባ ጽፈት ቤት በ2015 ዓ.ም አይዲ 6 በመባል የሚታወቀውን ተሽከርካሪ በ5.5 ሚሊዮን ብር፣ በ2016 ዓ.ም. ደግሞ ይህንኑ ተሽከርካሪ በ6.5 ሚሊዮን ብር እንደሸጡ ገልጸዋል። አሁን ግን የከተማ አስተዳደሩ የገቢዎች ቢሮ ባወጣው የታክክ ሥሌት የመሸጫ ዋጋው 11 ሚሊዮን ብር እንደሆነ አድርጎ መወሰኑን አስረድተዋል።
‹‹በዚህም መሠረት ይህንን ተሽከርካሪ ከምንሸጥበት 6.5 ሚሊዮን ብር በላይ ሃምሳ በመቶ (4.5 ሚሊዮን ብር) ጭማሪ ተደርጎ ታክስ እንድንከፍል ተጠይቀናል፤›› የሚሉት ነጋዴዎቹ፣ እየተጠየቁት ያለው ክፍያ ከካፒታላቸው በላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የገቢዎች የግብር አሰባሰብ ሒደት መኖሩን፣ ትርፍ ህዳግ የሚሰጥበት አሠራር እንዳለ፣ የነጋዴው መሠረት የሚያቀርበው ዲክሳራሲዮን እንደሆነ፣ በዚያ መሠረት እንደሚሸጡ፣ ስለሆነም በዚያ አግባብ መሠረት መስተናገድ እንደሚገባቸው የመኪና አስመጪዎቹ ይገልጻሉ፡፡ አክለውም አዲስ አሠራር ካስፈለገም አስቀድሞ ተገልጾ ነጋዴው አዋጭነቱን ዓይቶ እንዲቀጥልና እንዲያቆም ዕድል መስጠት ሲቻል በድንገተኛ ውሳኔ መቅረቡ ተቀባይነት የለውም ይላሉ፡፡
‹‹ይባስ ብሎ አካውንታችን መዘጋቱ፣ ክሊራንስ አለመሰጠቱ የባሰ ለተጨማሪ ወጪ ዳርጎናል፡፡ ባንክ ላይ ኤልሲ ከፍቶ የተቀመጠ ሰው አለ፡፡ ጂቡቲ ላይ የተቀመጠ የብዙ ሰው ተሽከርካሪ አለ፡፡ ለዚያም ዲሜሬጅ እየከፈልን ነው፡፡ ጉምሩክ ኮሚሽንም በወቅቱ መሰብሰብ ያለበትን ግብር እንዳይሰበሰብ ነው ያደረገው፤›› ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አስመጪ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሰውነት አየለ ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ፣ የከተማው የገቢዎች ቢሮ በየጊዜው የተለያዩ ጥናቶችን እንደሚያደርግ ከ2015 ዓ.ም. የተለያዩ አካላት የተሳተፉበት (ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ከተማ ንግድና ቢሮና ከመሳሰሉት ተቋማት) ጥናት እንደተደረገ፣ ጥናቱ በዋነኛነት በአዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ዋና ዋና የታክስ ሥወራ ያለባቸውን ዘርፎች የለየ መሆኑን ገልጸዋል።
ከመኪና ጋር በተያያዘ ያለው ጉዳይ በጥናቱ እንደተካተተ፣ በወቅቱ በተጠናው ጥናት ከመኪና ሽያጭ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የታክስ ሥወራ መኖሩ እንደተረጋገጠ፣ መኪና ሻጮች ደረሰኝ የሚቆርጡበት ዋጋና የሚሸጥበት ዋጋ (የገበያ ዋጋ) ከፍተኛ ልዩነት ያለበት መሆኑ በወቅቱ እንደተለየ ተናግረዋል። ይህንንም መሠረት በማድረግ የከተማ አስተዳደሩ ከ2016 ዓ.ም. ሚያዝያ ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ አዲስ አሠራር ተግባራዊ እንዲሆን መወሰኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
‹‹ከመኪና ጋር በተያያዘ የውሳኔው አፈጻጸም ሁለት ተቋማትን የሚመለከት ነው፡፡ አንደኛው የገቢዎች ቢሮ፣ ሁለተኛው ደግሞ በትራንስፖርት ቢሮ ያለው የአሽከርካሪ ተሽከርከሪ ባለሥልጣን የሚባለው ነው፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ ሰውነት፣ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ባለሥልጣን ጥናቱን ተከትሎ ወዲያውኑ በወጣው አዲስ ቀመር መሠረት ክፍያውን ሲያስፈጽም እንደቆየ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ከገቢዎች ቢሮ ጋር በተያያዘ በ2016 ዓ.ም. እንዲተገበር የተደረገው ቢሮው በነበረበት የአመራር ክፍተት መሆኑን ገልጸዋል።
‹‹በ2017 ዓ.ም. አመራሩ የተጠናውን ጥናት ቀመሩን መነሻ በማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጎበታል፡፡ በተለይም አስመጪዎቹን በጋራ መድረክ የቢሮ ኃላፊው በተገኙበት የሒሳብ ባለሙያዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጓል፤›› ያሉት አቶ ሰውነት፣ አስመጪዎቹ በቀመሩ ላይ ያነሷቸው ችግሮች በተለይም ከውጭ ምንዛሪ ጋር ተያይዞ መኪናውን የሚያስመጡት ከትይዩ ገበያ በገዙት ዶላር መሆኑን ገልጸው፣ ችግር እንደሚፈጥርባቸው ማስረዳታቸውን በዚህም ላይ ውይይት ተደርጎ ቀመሩ ምንም ዓይነት አስመጪዎችን ለኪሳራ የሚዳርግ እንዳልሆነ መተማመን የተደረሰበት ነው ብለዋል፡፡ ስለሆነም አዲስ የወጣ አዋጅ፣ መመርያና አሠራር የለም ሲሉ አክለዋል፡፡
‹‹ነጋዴዎች የሚቆርጡት ደረሰኝ ከሚሸጡት የገበያ ዋጋ ጋር ያለው ልዩነት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ አሥር ሚሊዮን ብር የሚሸጥ መኪና ደረሰኝ ላይ ሲቀርብ ሦስት ሚሊዮን ብር ተብሎ ነው፤›› ያሉት አቶ ሰውነት፣ ቢሮው እንደ እዚህ ዓይነት ሐሰተኛ ደረሰኝ ሲቀርብ የሚቀበልበት አሠራር የለም በማለት ገልጸዋል፡፡
‹‹ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ በቢሮ ደረጃ ያቀረቡ አሉ፡፡ በማዕከል ደረጃ ያቀረቡ አሉ፡፡ ቅሬታ ያላቀረቡና አምነው ክፍያ የፈጸሙ አሉ፤›› ሲሉ ያስረዱ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው፣ ቅሬታ ያቀረቡት በቅሬታው መሠረት ታይቶ ውሳኔ እየተሰጣቸው ነው ብለዋል፡፡ በዛብን በሚል ቅሬታ ላቀረቡትም የጊዜ ስምምነት እየተሰጣቸው በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲፈጽሙ እየተደረገ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
‹‹የባንክ ዕዳ አለብን፣ ቋሚ ሠራተኞች አሉን፣ የቢሮ ኪራይ አለብን፤›› የሚሉት የመኪና አስመጪዎቹ፣ ‹‹ይኸንን ከየት አምጥተን እንድንከፍል ታስቦ ነው የባንክ አካውንታችን የተዘጋው፣ ክሊራንስ ያልተሰጠን፣ ላለፉት አሥርና 15 ዓመታት የቆየ ነጋዴ፣ በግብር አከፋፈል ሪከርዱም የወርቅና የፕላቲንየም ተሸላሚ የሆነ ዜጋ እንዴት እንደዚህ እንዲሆን ይደረጋል?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡
እርሳቸው ይህንን ይበሉ እንጂ ሪፖርተር ባደረገው ማጣራት ቢዋይዲ በመባል የሚታወቅ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ አዲስ የቤት አውቶሞቢል በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ገበያዎች በአማካኝ በ2.6 ሚሊዮን ብር እየተሸጠ መሆኑን አረጋግጧል። ይሁን እንጂ ይህንን ተሽከርካሪ ለሽያጭ ያቀረቡ አስመጪዎች ተሽከርካሪውን የሸጡት በ3.7 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ተሠልቶ ግብር እንዲከፍሉ እየጠየቁ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል።
ከዚህም ባለፈ ይህንኑ ተሽከርካሪ ከሰሞኑ የገዙ አንድ ግለሰብ የተሽከርካሪውን ስም ለማዞር ለትራስፖርት ቢሮ የገዙበትን ደረሰኝ አቅርበው ለመስተናገድ ቢጠይቁም የተሽከርካሪው ዋጋ 3.7 ሚሊዮን ብር ነው እንደተባሉ፣ ለመካራከር ቢሞክሩም ሁሉም ተስተናጋጅ የተጠየቀውን ነው የሚከፍለው ምንም አታመጣም የሚል ምክር ከሌሎች ተስተናጋጆች በመስማታቸው በተባለው ዋጋ የተጠየቁትን የአሹራ ክፍያ ለመክፍል እንደተገደዱ ገልጸዋል።