ሔለን ተስፋዬ

December 29, 2024

የትራፊክ ደኅንነት ስትራቴጂ ዕቅድ ዙሪያ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ባሰናዳው መድረክ ላይ

በንግድ ሥራ የተሰማሩ ተሽከርከሪዎችን የአደጋ ተጋላጭነታቸውን የሚቀንስ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ አስገዳጅ ስታንዳርድ እንደሚተገብር፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው ይህንን ያስታወቀው ለቀጣይ አምስት ዓመታት የኮሪደር ልማትና መሰል የመንገድ ደኅንነት ማሻሻዎች፣ ‹‹የትራፊክ ደኅንነት ስትራቴጂ ዕቅድ› ዙሪያ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ታኅሳስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ባሰናዳው መድረክ ላይ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ እንደተናገሩት፣ በከተማዋ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱት በንግድ ትራንስፖርት አገልግሎት የተሰማሩ ተሽከርከሪዎች ናቸው፡፡

ለትራፊክ አደጋና ለመንገድ ደኅንነት ተጋላጭነት የሚጨምሩ ሁኔታዎች ውስጥ በፍጥነት ማሽከርከር እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፣ ይህንን ለመቆጣጠርና ችግሩን ለመቀነስ በቅድሚያ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ተሽከርከሪዎችን ተጋላጭነት የሚቀንስ ቴክኖሎጂ እንዲገጥሙ ይደረጋል ብለዋል፡፡ 50 በመቶ የትራፊክ አደጋ የሚርሰውም በኮድ 3 ተሽከርካሪዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ የአደጋ ተጋላጭነትን የሚቀንስ ቴክኖሎጂ በአስገዳጅነት እንዲያስገጥሙ የሚደረጉ የንግድ ሥራ የተሰማሩ ተሽከርከሪዎች (ኮድ 3) ላይ ይጀመር እንጂ፣ በቀጣይ በሁሉም ተሽከርከሪዎች ላይ ይተገበራል ብለዋል፡፡

ፍጥነትን መገደብ የሚጠቅመው ለባለንብረቱ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ያብባል፣ በተለይ ኮድ 3 ባለንብረቶች ቀድመው በመጠቀማቸው እንደ ዕድል ሊወስዱት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አሮጌ ተሽከርካሪዎችን በአዲስ ለመቀየር ጥናት ከተደረገ በኋላ፣ በአዲስ የመተካትና የምርት ዘመናቸው ታይተው በከተማ እንዳይንቀሳቀሱ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

አቶ ያብባል፣ አሮጌ ተሽከርካሪዎችን በአዲስ ስለመቀየርና በተመረጡ ቦታዎች እንዳይሽከረከሩ ይደረጋል ስለተባለው ጉዳይ ለሪፖርተር እንዳሉት፣ አሮጌ መኪናን በተመለከተ ጉዳዩ አገር አቀፍ መሆኑን፣ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ብዙ አሮጌ መኪናዎች ስላሉ፣ እነዚህ መኪናዎች የጋዝ ልቀታቸው ከፍተኛ በመሆኑ ሥውር አደጋ እያስከተሉ ነው፡፡

በከተዋማ ሲንቀሳቀሱ ለትራፊክ መጨናነቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላላቸውና የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለሚያገኙት ኅብረተሰብ ምቾት የሌላቸው መሆናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ቢሮው ያስቀመጣቸው አምስት መሥፈርቶች ቢኖሩትም እነዚህ አሮጌ መኪናዎች ግን አንዱንም የማያሟሉና ተሽከርከሪዎችን በአዲስ ለመቀየር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሮጌ መኪናዎችን ለመቀየር ከባለንብረቶችና ከአስመጪዎች ጋር መሥራት እንደሚገባቸው ቢሮው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጹት ኃላፊው፣ ኃላፊነቱ ግን የባለንብረቶቹ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ቢሮው ለባለንብረቶቹ በፍጥነት እንዲቀየሩ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ገልጸው፣ ከአስመጪዎች ጋር ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸውና የብድር ድጋፍም እንዲያገኙ እንደሚያመቻች አስረድተዋል፡፡

ባለአሮጌ ተሽከርከሪዎች ባለቤቶች በቶሎ በአዲስ የማይቀየሩ ከሆነ ደግሞ ከተማዋ ተወዳዳሪና ዘመናዊ በመሆኗ የኮሪደር ልማት የተሠሩ መንገዶች እንዳይንቀሳቀሱ ክልከላ ሊደረግባቸው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን  እ.አ.አ. 2025 እስከ 2030 ተግባራዊ የሚደረገው የመንገድ ትራፊክ ስትራቴጂ ዕቅድ በከተማዋ የሚታየውን   ሞትንና የአካል ጉዳትን በ25 በመቶ ለመቀነስ ማቀዱ ተገልጿል፡፡

ባለሥልጣኑ ግቡን ለማሳካት እንዲችል ሰባት ዋና ዋና የትኩረት መስኮች የተለዩ መሆናቸውን፣ የመንገድ ደኅንነት አስተዳደር ሥርዓትን መዘርጋት፣ የመንገድ ትራፊክ ግጭት በሚበዛባቸው ዋና መንገዶች ላይ ማተኮር፣ በግንዛቤ ማስጨበጥ የተደገፉ ቁልፍ የደኅንነት ሕጎችን መተግበር፣ የመንገድ ትራፊክ ግጭትና ጉዳት መረጃ አስተዳደር ሥርዓትን ማዘመን፣ የድህረ አደጋ ምላሽ፣ እንዲሁም ምርጥ ተሞክሮዎችን መቀመር የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው  ተብሏል።

አቶ ያብባል እንደገለጹት፣  የከተማዋን የትራንስፖርት ሥርዓት አስተማማኝና ደኅንነቱ የተጠበቀ ተደራሽ፣ ምቹ፣ ወቅቱ በደረሰባቸው ቴክኖሎጂዎች የሚታገዝ ፈጣንና ዘመናዊ እንዲሆን ለማስቻል፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ማረጋገጥ እንዲቻል ይፋ የተደረገውን ስትራቴጂ ተግባራዊ እየተደረገ ካለው የከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራ ጋር ለማጣጣም ሞተር አልባ የትራንስፖርት ሥርዓትን ማስፋፋት፣ ፈጣንና ዘመናዊ የብዙኃን ትራንስፖርት አማራጮችን በሚፈለገው አግባብ ማስፋት በስትራቴጂው ከተቀመጡ ግቦች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ በበኩላቸው፣ በምክትል ከንቲባ የሚመራው በ2009 ዓ.ም. በከተማዋ የተቋቋመው የመንገድ ደኅንነት ምክር ቤት ለ13 ዓመታታ የሚዘልቅ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ አዘጋጅቶ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ ይፋ በተደረገው በተሻሻለው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ለቀጣይ አምስት ተከታታይ ዓመታት ሥራ ላይ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡