
ከ 8 ሰአት በፊት
በግብፅ የቀይ ባሕር ዳርቻ አንድ ጎብኚ በሻርክ ጥቃት ሲገደል አንድ ሌላ ግለሰብ ጉዳት እንደደረሰበት የሀገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
የሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር የተፈጥሮ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እሑድ ዕለት አንድ ሻርክ ጎብኚዎች ላይ ሞት እና ጉዳት ያደረሰው ማርሳ አላም ተብላ በምትታወቀው ሥፍራ ነው።
ማርሳ አላም በውሀ ጠላቂዎች የምትወደድ የምስራቅ ግብፅ የባሕር ዳርቻ ከተማ ናት።
የተፈጥሮ ሚኒስቴሩ አክሎ ጥቃቱ የተከሰተው “ሰዎች እንዲዋኙ ከተፈቀደላቸው ክልል ውጭ ጥልቁ ባሕር አካባቢ ነው” ብሏል።
ሚኒስቴሩ ሁለት ጎብኚዎች ሞት እና ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሎ ነገር ግን የጎብኚዎች ዜግነት ከመናገር ተቆጥቧል።
ኤኤፍፒ የዜና ወኪል በበኩሉ ከጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ ግለሰቦቹ ጣሊያናዊያን መሆናቸው ዘግቧል።
በሻርክ የተገደለው የ48 ዓመቱ ግለሰብ የሮም ነዋሪ ሲሆን ሌላኛው ጉዳት የደረሰበት የ69 ዓመት ግለሰብ መሆኑን የዜና ወኪሉ አስነብቧል።
- “ባርነት እንደሆነ ነው የሚሰማህ” – በምያንማር ውስብስብ የወንጀል መረብ የተጠለፉት ኢትዮጵያውያንከ 8 ሰአት በፊት
- በሲዳማ ክልል በትራፊክ አደጋ ምክንያት የ71 ሰዎች ሕይወት አለፈ29 ታህሳስ 2024
- “ሥራዬ ቲክቶክ ላይ የሚለጠፉ ዘግናኝ እና አሰቃቂ ቪድዮዎችን ማፅዳት ነበር”ከ 8 ሰአት በፊት
የግብፅ ባለሥልጣናት ሁለት ጎብኚዎች ፖርት ጋሊብ ወደሚሰኘው ከማርሳ አለም 48 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ሆስፒታል መወሰዳቸውን አሳውቀው ነበር።
አክለው ማርሳ አለም የሚገኘው የመዋኛ ክልል ለጊዜው ዝግ እንደሚሆንና የክስተቱ መንስዔ እንደሚጣራ ገልፀዋል።
ባለፉት 10 ዓመታት በቀይ ባሕር ላይ አራት ሰዎች በሻርክ ጥቃት ተገድለዋል ይላል ሻርክ ሪሰርች ኢንስቲትዩት የተሰኘው የምርምር ተቋም።
በአውሮፓውያኑ ሰኔ 2023 አንድ የ24 ዓመት ሩሲያዊ ወጣት ሀርጉዳ ተብሎ በሚታወቀው ሥፍራ በሻርክ መበላቱ አይዘነጋም።