
ከ 11 ደቂቃዎች በፊት
በሲዳማ ክልል ምስራቃዊ ሲዳማ ዞን ሰርገኞች ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው ካለፈ 71 ሰዎች ውስጥ ከ50 በላይ የሚሆኑት የአንድ ቤተሰብ አባላት እና ዘመዳሞች መሆናቸው ተነግሯል።
አደጋው የደረሰው በዞኑ ቦና ዙሪያ ወረዳ ትናንት ዕሁድ ታኅሳስ 20/ 2017 ዓ.ም. ከሰዓት 11:00 አካባቢ ‘አይሱዚ’ በተባለ የጭነት ተሽከርካሪ “ወደ ሙሽራዋ ቤት” እየተጓዙ የነበሩ ሰርገኞች ላይ ነው።
ሰርገኞቹ ሚሪዴ ከተባለ ቀበሌ ቤተ ክርስቲያን ደርሰው ወራንቻ ወደ ተባለ አካባቢ ሲጓዙ ጋለና ወንዝ ድልድይ ላይ ተሽከርካሪው መስመር በመሳት “ተወርውሮ” ወደ ወንዙ መግባቱን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።
“በጣም ነው የተጎዱት” ሲሉ አደጋውን የገለፁት የቦና ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ሹመቴ ቱንቻ የአደጋው መንስኤ ተሽከርካሪው “ከአቅም በላይ በመጫኑ ነው” ብለዋል።
በአደጋው ሙሽራውን ጨምሮ የ71 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የተናገሩት ኃላፊው፤ አስከሬን እስከ ሌሊቱ 9፡00 ድረስ እንደተነሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ ትብብር 73 የአደጋው ተጎጂዎች ወደ ቦና አጠቃላይ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ለማ ለጊዴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“. . .ወንዙ ላይ ነው የወደቀው። መኪናው የወደቀው እላያቸው ላይ ነው። በአካባቢው ማኅበረሰብ ርብርብ ነው አስከሬኑ ወደ [ሆስፒታል] እኛ መምጣት የቻለው” ብለዋል።
በአስከሬን ምርመራ በአደጋው 66 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን እንዳረጋገጡ ሜዲካል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
64ቱ የአደጋው ተጎጂዎች ሆስፒታል ከመድረሳቸው በፊት ወዲያው ሕይወታቸው ማለፉን የጠቆሙ ሲሆን፤ ሁለቱ ተጎጂዎች ደግሞ ሆስፒታል ደርሰው ህክምና እየተደረገላቸው እያለ ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።
“አንዱ ወደ ኦፕሬሽን ክፍል ገብቶ ህክምና እተደረገለት እያለ ነው ሕይወቱ ያለፈው። አንዷ ድንገተኛ የህክምና ክፍል ህክምና እተደረገላት ነው ሕይወቷ ያለፈው። ወንዙ ላይ ከወደቁበት ተጎጂዎችን አንስተው ሆስፒታል እስኪያመጡ ድረስ መንገድ ላይ [ሕይወታቸው ያለፈ አሉ]። 64ቱ [ሟቾች] በቦታው እና መንገድ ላይ እያሉ [ሕይወታቸው ያለፈ] ናቸው” ሲሉ ገልፀዋል።
ከሟቾቹ ውስጥ ሙሽራውን ጨምሮ 61 ወንዶች እና አራቱ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
- በሲዳማ ክልል በትራፊክ አደጋ ምክንያት የ71 ሰዎች ሕይወት አለፈ29 ታህሳስ 2024
- “ባርነት እንደሆነ ነው የሚሰማህ” – በምያንማር ውስብስብ የወንጀል መረብ የተጠለፉት ኢትዮጵያውያንከ 8 ሰአት በፊት
- ለደቡብ ኮሪያ አውሮፕላን አደጋ ወፎች ተጠያቂ ናቸው? እስካሁንስ ምን እናውቃለን?ከ 3 ሰአት በፊት
ሰባት ሰዎች ቆስለው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ የተናገሩት ዶ/ር ለማ አምስቱ ተጊጂዎች መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ሁለቱ ተጎጂዎች ደግሞ የዳሌ፣ የእጅ እና እግር ስብራት እንዳጋጠማቸው ገልፀው፤ ወደ ሀዋሳ ለሪፈር ህክምና መወሰዳቸውንም አክለው ተናግረዋል።
ከ50 በላይ የሚሆኑት ሟቾች የሚሪዴ ቀበሌ ነዋሪዎች የሆኑ የአንድ ቤተሰብ አባላት እና ዘመዳሞች መሆናቸውን ምክትል ኢንስፔክተር ሹመቴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የወንድም፣ የእህት [ልጅ]፣ አጎት” የሆኑ አንድ ቤተሰብ አባለትን ጨምሮ ሰርጉን ለማጀብ የወጡ ጎረቤቶችም የአደጋው ተጎጅዎች እንደሆኑ ገልጸዋል።
“አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው” ሲሉ ስለ ተጎጂዎች ማንነት የተናገሩት የቦና አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር፤ ተጎጂዎቹ ከ15 ዓመት እስከ 30 ዓመት የሚሆኑ ወጣቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
“አይደለም ቤተሰብ ብቻ ለሲዳማ ህዝብም፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብም በጣም ነው የተጎዳው። ቤተሰብም፤ አካባቢው ነዋሪም ሀዘኑን እየገለፀ ነው” ሲሉ አካባቢው ስላለበት ሁኔታ ተናግረዋል።
የሟቾቹ ስርዓተ ቀብር ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ያልተፈፀመ ሲሆን፤ ቀብሩ ነገ ማክሰኞን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናት ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት እንደሚፈጸም ይጠበቃል።