አደጋ የደረሰበት አውሮፕላን

ከ 3 ሰአት በፊት

እሑድ ጠዋት ደቡብ ኮሪያ ሲያርፍ የነበረ አውሮፕላን ተከስክሶ ከ170 በላይ ሰዎች ሞተዋል።

ንብረትነቱ የጄጁ አየር መንገድ የሆነው አውሮፕላን በአገሪቱ ደቡብ ምዕራብ በሚገኘው ሙአን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከማኮብኮብያው ወጥቶ ከግድግዳ ጋር ተጋጭቷል።

ከታይላንድ ባንኮክ ሲመለስ የነበረው አውሮፕላኑ 181 ሰዎችን አሳፍሮ ነበር። 179ኙ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ሁለት የአውሮፕላኑ ሠራተኞችን ማትረፍ ተችሏል።

ባለስልጣናቱ የአደጋውን መንስኤ በማጣራት ላይ ይገኛሉ። የእሳት አደጋ መከላከያ ባለስልጣናት መንስኤው አእዋፍ እና ከባድ የአየር ሁኔታ ሊሆን ይችላል ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

የአእዋፍ ግጭት አደጋውን አደርሶት ይሆን?

አብዛኛው የአውሮፕላኑ ክፍል ለመለየት ያስቸግራል

የበረራ ቁጥሩ 7ሲ 2216 ሆነው ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን በጄጁ አየር መንገድ የሚተዳደር ሲሆን በኮሪያ በጣም ታዋቂ እና ርካሽ ከሚባሉት አየር መንገዶች አንዱ ነበር።

አውሮፕላኑ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ጠዋት 3፡00 ሰዓት ላይ ሙአን ደረሰ።

የደቡብ ኮሪያ የትራንስፖርት ባለስልጣን አውሮፕላኑ ለማረፍ ሲሞክር ነበር ብለዋል። የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የአእዋፍ ጥቃት ሊኖር እንደሚችል በማስጠንቀቃቸው ሳያርፍ ቀረ።

ከሁለት ደቂቃ በኋላ አብራሪው ሜይዴይ (አደጋ ያጋጠማቸው አብራሪዎች የሚያስተላልፉት መልዕክት) በማለት ጥያቄ አቅርቦ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያው አውሮፕላኑ ከተቃራኒ አቅጣጫ እንዲያርፍ ፍቃድ መስጠቱን ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።

በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበረ አንድ ተሳፋሪ ወፍ “ክንፉ ውስጥ በመግባቱ” አውሮፕላኑ ማረፍ አልቻለም ሲል ለአንድ ዘመዱ የጽሑፍ መልዕክት አስተላልፏል ሲሉ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በአንድ ቪዲዮ ላይ አውሮፕላኑ በጎማዎቹ ወይም በሌላ ማንኛውንም ማረፊያ መሳሪያ ሳይጠቀም መሬት ሲነካ የሚያሳይ ይመስላል። መንደርደሪያው ላይ ተንሸራቶ እሳት ከመነሳቱ በፊት ከግድግዳ ጋር ተጋጭቷል።

አንድ እማኝ ለደቡብ ኮሪያው የዜና ወኪል ዮንሃፕ እንደተናገሩት “ከፍተኛ ፍንዳታን” ተከትሎ “የተከታታይ ፍንዳታዎች” ሰምተዋል።

ከስፍራው የወጡ ቪዲዮዎች አውሮፕላኑ በእሳት ተያይዞ ጢስ ወደ ሰማይ ሲጨስ አሳይተዋል። በኋላም የእሳት አደጋ ሠራተኞች እሳቱን ማጥፋት ችለዋል።

የሙአን የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሊ ጁንግ-ህዩን በቴሌቭዥን በተላለፈ መግለጫቸው የአውሮፕላኑ የኋላ ክፍል የሚለይ ቢሆንም “የተቀረውን የአውሮፕላኑን አካል መለየት አይችልም” ብለዋል።

የአእዋፍ ጥቃትና ከባድ የአየር ሁኔታ ለአደጋው መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል። ትክክለኛው መንስኤ ግን በመጣራት ላይ ነው። የአውሮፕላኑ የበረራ እና የድምጽ መቅጃዎች ተገኝተዋል።

የጄጁ አየር መንገድ ኃላፊ አደጋው የተከሰተው “በጥገና ችግር አይደለም” ማለታቸውን ዮንሃፕ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የደቡብ ኮሪያ የትራንስፖርት ቢሮ በበኩሉ ዋና አብራሪው እአአ ከ 2019 ጀምሮ በሥራው መቆየቱን እና ከ6 ሺህ 800 ሰዓታት በላይ የበረራ ልምድ ያለው መሆኑን አሳውቋል።

የአእዋፍ ጥቃት ምንድን ነው?

የአእዋፍ ትቃት የሚባለው በበረራ ላይ ባለ አውሮፕላን እና በወፍ መካከል የሚፈጠር ግጭት ነው።

ይህ በጣም የተለመደ ነገር ነው። እአአ በ 2022 በዩናይትድ ኪንግደም ከአንድ ሺህ 400 በላይ የአእዋፍ ጥቃቶች ሪፖርት ተደርገዋል። ከእነዚህ ውስጥ 100 ያህሉ ብቻ በአውሮፕላኑ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ ሲል የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን መረጃ ያሳያል።

ከአእዋፍ ጥቃት ጋር በተያያዘ ታዋቂ የሚባለው አደጋ የደረሰው እአአ በ2009 ሲሆን የኤርባስ አውሮፕላን ከወፍ መንጋ ጋር በመጋጨቱ በኒውዮርኩ ሃድሰን ወንዝ ውስጥ ለመግባት ተገዷል። 155 ተሳፋሪዎች እና የበረራ ሠራተኞች በህይወት ተርፈዋል።

በአውስትራሊያ የአቪየሽን መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ዳግ ድሩሪ ለዘ ኮንቨርሴሽን እንደጻፉት ከሆነ የቦይንግ አውሮፕላኖች ቱርቦ ፋን ሞተሮች ስለተገጠመላቸው በወፍ ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል።

አዕዋፍ በብዛት በሚንቀሳቀሱበት በተለይም ጠዋት እና ማታ ላይ አብራሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንደሚሰለጥኑ ተናግረዋል።

አውሮፕላኑ እነማንን አሳፍሮ ነበር?

አውሮፕላኑ 175 መንገደኞችን እና 6 የበረራ ሠራተኞችን አሳፍሮ ነበር። ከተሳፋሪዎቹ ውስጥ ሁለቱ የታይዋን ዜጎች ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ደቡብ ኮሪያዊ መሆናቸውን ባለስልጣናት ተናግረዋል። አብዛኛዎቹም የገና በዓልን ታይላንድ አክብረው ሲመለሱ እንደነበር ይታሰባል።

ይፋ የሆነው የሟቾች ቁጥር 179 ደርሷል። ይህም በደቡብ ኮሪያ ታሪክ እጅግ አስከፊው የአውሮፕላን አደጋ ሆኖ ተመዝግቧል።

ሁሉም ተሳፋሪዎች እና አራት የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ህይወታቸው አልፏል።

እስካሁን የ88 አስከሬኖችን ማንነት ለመለየት ተችሏል።

ከሟቾቹ መካከል አምስቱ ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ናቸው። በዕድሜ ትንሹ ተሳፋሪ የሦስት ዓመት ልጅ ሲሆን ትልቁ ደግሞ 78 ዓመት ግለሰብ ነው ሲሉ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ የእሳት አደጋ መከላከያ ኤጀንሲ እንዳስታወቀው አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት የበረራ ሠራተኞች ከአደጋው ተርፈዋል። ከአደጋው በኋላ በአውሮፕላኑ ጅራት ላይ ተገኝተው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ነው የተገለጸው።

490 የእሳት አደጋ ሠራተኞች እና 455 የፖሊስ መኮንኖችን ጨምሮ ከአንድ ሺህ 500 በላይ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን በስፍራው ተሰማርተዋል። የአውሮፕላኑ አካላት እና በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ለመፈለግ በአውሮፕላን ማረፊያ ዙሪያ ያለው አካባቢ ላይ ፍለጋ ሲካሄድ ቆይቷል።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች