
ከ 7 ሰአት በፊት
እስራኤል በተለያዩ ግንባሮች የምታደርገው ጦርነት ጠላቶቿን ብቻ አላዳከመም።
በጋዛ እና ሊባኖስ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት ብቻ አልቀጠፈም።
የራሷን ሕዝቦችም ከባድ ዋጋ ማስከፈሉን ቀጥሏል።
በእስራኤል እየጨመረ የመጣ በጦርነት የመሰላቸት ስሜት አለ። በቅርቡ ከሊባኖስ ጋር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ለብዙዎች እፎይታ ሰጥቷል። ባለፈው ዓመት በውጊያ ቀጠናዎች በሕክምና ባለሙያነት ላገለገለው እና የመከላከያ ኃይሉ ተጠባባቂ ኃይል ለሆነው ኖአም ግሉኮቭስኪ ትንሽም ቢሆን እፎይታ እነዲሰማው አድርጓል።
ቢቢሲ የ33 ዓመቱን ኖአምንን በቴል አቪቭ ያነጋገረው የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከመገለጹ በፊት ነበር።
“ይህን ጦርነት ረዘም ላለ ጊዜ መቀጠል አንችልም። ያለ ግልጽ የመጨረሻ ቀን እና ግብ ለመቀጠል የሚያስችል የሰው ኃይል የለንም” ነበር ያለው በወቅቱ።
እንደ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ተጠባባቂ አባልነቱ ኖአም በመደበኛነት በዓመት ለጥቂት ሳምንታት የውትድርና አገልግሎት እንዲሰጥ ይጠበቃል። ባለፈው ዓመት ግን 250 ቀናትን በግዳጅ ላይ አሳልፏል። ጦርነቱ ከሚያውቀው ሕይወት እንደነጠለው ይናገራል። ዶክተር የመሆን እቅዱም በአንድ ዓመት ተገፍቷል።
ኖአምን ቢቢሲ ሲያገኘው ያመለጠውን ትምህርት ለመከታተል እየሞከረ ነበር።
በዚያው ልክ ደግሞ ዳግም ወደ ግዳጅ እጠራ ይሆናል በማለት ልቡ ተከፍሎ ነበር። ስሜቱ ተረብሿል።
“ከእንግዲህ በራሴ ሕይወት ላይ ማዘዝ አልችልም ” የሚለው ኖአምን በጦርነቱ አቅጣጫ ላይ ተአምራዊ ለውጥ እስካልተደረገ ድረስ ወደ ምድቡ የመመለስ ፍላጎቱ ተሟጧል። በቅቶታል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል እንደሚለው ከሆነ ከተጠባባቂ ኃይሉ መካከል ጥቂት ቁጥር ያላቸው ብቻ ናቸው ለግዳጅ ሲጠሩ የሚመጡት። ባለፈው ዓመት ጥቅምት 7፣ 1,200 ሰዎችን ከገደለው የሃማስ ጥቃት በኋላ ከ300,000 በላይ ተጠባባቂ ኃይሎች ለእስራኤል መከላከያ ጥሪ ምላሽ ሰጥተዋል።
በወቅቱ የነበረው ተሳትፎ ሲገመገም ከ100% አልፎ የነበረ ቢሆንም አሁን ወደ 85% ወርዷል። ኖአም በእሱ ክፍል ምላሹ ከዚህም ያነሰ እንደሆነ ይገምታል፤ ለግዳጅ ከተጠሩት ውስጥ 60% የሚሆኑት ብቻ ናቸው ምላሽ የሚሰጡት ሲል ያክላል።
- ሰሞኑን በዩኒቨርስቲዎች የተፈጠረው “ተቃውሞ” መነሻው ምንድን ነው?27 ታህሳስ 2024
- የናሳ መንኩራኩር 6.1 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ወደ ፀሐይ በመጠጋት ታሪክ ሠራች27 ታህሳስ 2024
- ሕንዳውያን ሕይወታቸው አደጋ ላይ እየጣሉ ወደ አሜሪካ የሚጎርፉት ለምን ይሆን?27 ታህሳስ 2024
ተጠባባቂዎች እና አዲስ ምልምል ወታደሮች የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት የደም ስር ናቸው።
የተጠባባቂ ኃእል አባል የሆኑት እና የወድሞው ዋና ተጠባባቂ መኮንን ብርጋዴር ጄኔራል አሪኤል ሃይማን እስራኤል ግዙፍ፣ ውድ፣ በሙያ የተካነ እና መደበኛ ጦር እንዳይኖራት በጣም ትንሽ አገር ነች ይላሉ። ያለ ተጠባባቂ ኃይል፣ መከላከያ ኃይሉ መዋጋትም ሆነ በሕይወት መቆየት እንደማይችል ጨምረው ያስረዳሉ።
እንደ ዓለም አቀፉ የስትራቴጂ ጥናት ተቋም ገለጻ፣ የእስራኤል ጦር አዲስ ምልምሎችን ጨምሮ 170,000 መደበኛ ወታደር፣ እንዲሁም 465,000 ተጠባባቂ ኃይል አሉት።
ብርጋዴር ጄኔራል ሃይማን የእስራኤል መከላከያ ኃይል ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር በመጠባበቂያ ኃይሉ ላይ ያለው ጥገኝነት የበለጠ ፈታኝ እንደሚሆን ይናገራሉ።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል አሁን ባለው ውጥረት የተነሳ አዲስ ምልምል ወንዶች ግዳጅ አገልግሎት ከ32 እስከ 36 ወራት እንዲሆን ይፈልጋል።
ወታደራዊ አገልግሎቱን ሁሉም በእኩል የሚጋራው አለመሆኑ ደግሞ ቅሬታዎች እንዲባባሱ እያደረገ ነው። ሀሬዲ አይሁዳውያን ለብዙ አሥርተ ዓመታት ከወታደራዊ አገልግሎት ነፃ ሆነው ቆይተዋል በሚል ቅሬታ ከሚቀርብባቸው መካከል ናቸው።
እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወጣት ወንዶቻቸው ለውትድርና አገልግሎት ሳይሆን ለሃይማኖታዊ ጥናቶች ሕይወታቸውን መስጠት አለባቸው ብለው ያምናሉ።
ጉዳዩ የእስራኤልን ጥምር መንግሥት ከፋፍሎታል። ነገር ግን የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጣልቃ መግባቱን ተከትሎ ለ7,000 ሀሬዲ አይሁዳውያን የጥሪ ደብዳቤዎች ተልከዋል።
ይህንንም ተከትሎ በተቃውሞ የተሞላ ምላሽ ሰጥተዋል። ነገር ግን ብርጋዴር ጄነራል ሃይማን ልክ ከስልጣን እንደተነሱት የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት “የማገልገል የሞራል ግዴታ አለባቸው” ብለዋል።

የሚያስፈልገው የግል መስዋዕትነት ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊም ጭምር ነው።
የእስራኤል ባንክ በግንቦት ወር ላይ እንደገለጸው አገሪቱ እያካሄደች ያለችው ጦርነት ዋጋ በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ 70 ቢሊዮን ዶላር (£ 55bn) ሊደርስ ይችላል፤ ይህም አገሪቱ ሊባኖስ ላይ ወረራ ከመፈጸሟ በፊት የተደረገ ግምት ነው፤
ትንንሽ ንግዶች በጣም ከተጎዱት መካከል ናቸው።
የምግብ ቴክኖሎጂ ላይ የሚያተኩረው የሼሊ ሎታን ጅምር ስራ እንደ በርካቶች ሁሉ ላለመክሰም ከሚውተረተሩት መካከል ነው። ሼሊ የሔዝቦላ ሮኬቶችን ጥቃት በመሸሽ ንግዷን ከሰሜን እስራኤል ቀይራለች። ከሰባት ሰራተኞቿ መካከል ሁለቱ ለውትድርና አገልግሎት ተጠርተዋል።
ቢቢሲ ሼሊን በቴል አቪቭ በሚገኘው ቤቷ ማለዳ ላይ ሲያገኛት፣ ተጨማሪ መጥፎ ዜናዎችን ሰማች። ይህም ከሰራተኞቿ መካከል አንዱ የውትድርና አገልግሎቱ መራዘሙን የሚገልጽ የጽሑፍ መልዕክት ነበር።
ሼሊ “ሌላ ሠራተኛ ለተጨማሪ ወር ማጣት ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ መግለጽ አልችልም” ትላለች።
“ሌላ ሰው መቅጠር ወይም ይህን ክፍተት መሙላት እንኳን አልችልም።”
ሼሊ ባለቤቷ የተጠባባቂ ኃይል አባል በመሆኑ ከቤት ርቆ ስለሚያሳልፍ ከሦስት ትንንሽ ልጆቿ ሥራ ደርቦ መስራት ፈተና ሆኖባታል።
በሊባኖስ ጋር የተደረሰው የተኩስ አቁም የተወሰነውን ጫና ሊቀንስ ይችላል። ነገር ግን አሁንም በጋዛ ውጊያ አለ። ሼሊ ሎታን ግጭቱን ለማስቆም ከእስራኤል መንግሥት ግልጽ ስትራቴጂ ከሌለ ስለ ወደፊቱ ትፈራለች።
“ጦርነቱ አሁን ማብቃት የነበረበት ይመስለኛል” ትላለች።