
ከ 6 ሰአት በፊት
ለቻይና መንግሥት የሚሠራ አንድ የኮምፒውተር ሰርሳሪ የአሜሪካ ግምዣ ቤትን ጠልፎ የሠራተኞችን ኮምፒውተር እና ምስጢራዊ መረጃዎችን እንደተመለከተ የአሜሪካ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ይህ የሆነው በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ገደማ መሆኑን ግምዣ ቤቱ ለሕግ አውጭዎች በላከው ደብዳቤ አስታውቋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ “በቀላሉ የማናየው” ያለው ጠለፋ ያስከተለውን ጥፋት ለመመርመር ከኤፍቢአይ ጋር እየሠራ እንደሆነ ገልጿል።
በዋሺንግተን የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ወቀሳው “በሐቅ ላይ ያልተመሠረተ” እና “ተራ ጥቃት” ነው።
ግምዣ ቤቱ ፊርማው ያረፈበትን ደብዳቤ ለሕግ አውጭዎች የላከ ሲሆን በደብዳቤው መቀመጫውን ቻይና ያደረገ አካል ለመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች እርዳታ የሚያደርግ ሶስተኛ ወገን ድርጅትን ‘ሲስተም’ ጥሶ መግባት ችሏል ሲል ወቅሷል።
ሶስተኛ ወገን የተባለው ቢዮንድትረስት የተባለ ድርጅት ከኮምፒውተር ጠለፋው በኋላ ‘ኦፍላይን’ እንዲሆን መደረጉንም ባለሥልጣናቱ ገልፀዋል።
አክለው የኮምፒውተር ጠላፊው አሁንም የግምዣ ቤቱን መረጃዎች ማግኘት ይችል እንደሁ የሚያሳይ መረጃ የለም ብለዋል።
ግምዣ ቤቱ ከኤፍቢአይ እና ሲአይኤስኤ እንዲሁም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር በኮምፒውተር ጠለፋው ምክንያት የተከሰተውን እየመረመረ ይገኛል።
- ፑቲን በ25 ዓመታት አመራራቸው ለሩሲያ ምን አደረጉ?ከ 7 ሰአት በፊት
- እርቃን ፎቶዎችን እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም ገንዘብ የማግኛ መመሪያዎችን የሚሸጡት ወንጀለኞችከ 7 ሰአት በፊት
- ከ17 ዓመት ሴት ጋር ወሲብ በመፈጸም የተከሰሰው የ18 ዓመት እንግሊዛዊ በዱባይ ታሰረ30 ታህሳስ 2024
እስካሁን በተሰበሰቡ ማስረጃዎች መሠረት ጠላፊው “መቀመጫውን ቻይና ያደረገ እና ‘አድቫንስድ ፐርሲስተንት ትሬት (ኤፒቲ)’ የተባለ መንገድ የተጠቀመ” ነው።
“በግምዣ ቤት ፖሊሲ መሠረት በኤፒቲ የሚፈፀሙ ጥቃቶች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም” ይላል ደብዳቤው።
ቢዮንድትረስት የተባለው ለግምዣ ቤት ተቀጥሮ የሚሠራው ድርጅት በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2 ቢጠለፍም፤ ተጠልፎ እንደሆነ ለማጣራት ሶስት ቀናት እንደወሰደበት አንድ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ እንዳሉት ጠላፊው የሠራተኞችን ኮምፒውተር እንዲሁም አንዳንድ ምስጢራዊ የሚባሉ መረጃዎችን መበርበር ችሏል።
ግምዣ ቤቱ ምስጢራዊ የተባሉት መረጃዎች ምን አይነት ናቸው የሚለውን ከማሳወቅ ተቆጥቧል። የኮምፒውተር ጠለፋው ለምን ያክል ጊዜ እንደቆየም አላሳወቀም።
የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ ሊዩ ፔንግዩ የግምዣ ቤቱን ወቀሳ አስተባብለው ጠላፊዎቹ ከየት መሆናቸውን ለማወቅ አዳጋች ሊሆን እንደሚችል በመግለጫ አሳውቀዋል።
“ዩናይትድ ስቴትስ በሳይበር ደኅንነት ጉዳይ ቻይና ላይ የምታደርሰውን ጥቃት ማቆም አለባት። ከቻይና የሚመነጩ ስለሚሏቸው ጠለፋዎች የሚያስተላልፉትን የተሳሳተ መረጃም መግታት አለባቸው።”
ዩናይትድ ስቴትስ በኮምፒውተር ጠለፋ ጉዳይ የቻይና መንግሥት ላይ ወቀሳ ስትሰነዝር ይህ የመጀመሪያው አይደለም።