
ከ 7 ሰአት በፊት
የቢቢሲ የሩሲያ አርታኢ ስቲቭ ሮዘንበርግ በትውስታ ወደ 1999 ይጓዛል። ወቅቱ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ነበር። በሩሲያ አዲስ ፕሬዝዳንትም የተሾመበት ጊዜ ነበር። ስቲቭ ትዝታውን እንዲህ ያካፍላል።
በቢቢሲ የሞስኮው ቢሮ አዘጋጅ ሆኜ እየሠራሁ ነበር። ድንገት ሰበር ዜና መጣ። የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቦሪስ የልትሲን ሥልጣን ለቀቁ።
በመልቀቃቸው ሁሉም ተደነቀ። በሞስኮው ያለው የእንግሊዝ ሚዲያም ተገርሟል።
ዜናው ሲሰማ ቢሮ ውስጥ ማንም ስላልነበረ ዜናውን ጽፌ አስተላለፍኩ።
“ፕሬዝዳንት ቦሪስ የልትሲን የምርጫ ዘመናቸውን እንደሚጨርሱ ሲናገሩ ቢቆዩም አሁን ግን ሥልጣን ለቀቁ። ሐሳባቸውን መቀየራቸውን ለሩሲያውያን ተናገሩ” ብዬ ነበር የጻፍኩት።
ሥራ እየጀመርኩ የነበረበት ወቅት ነበር። ቭላድሚር ፑቲንም ፕሬዝዳንት ሆኑ።
ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ፑቲን በአገሪቱ ሕግ መሠረት መጀመሪያ ላይ ጊዜያዊ ፕሬዝዳት ነበር የሆኑት።
ከሦስት ወራት በኋላ ምርጫ አሸነፉ።
ቦሪስ የልትሲን ክሬምሊንን ሲለቁ ፑቲንን “ሩሲያን ጠብቃት!” ብለው ነበር።
የዩክሬን ጦርነት ሦስተኛ ዓመት ሊይዝ መሆኑን ሳስብ ፑቲን በ25 ዓመታት አመራራቸው ለሩሲያ ምን አደረጉ? ብዬ እጠይቃለሁ።
- ለሩሲያ የጦር መሳሪያ የሚያቀርቡት አገራት እነማን ናቸው?17 ጥቅምት 2024
- ዩክሬንን ቀደም ብዬ መውረር ነበረብኝ – ቭላድሚር ፑቲን20 ታህሳስ 2024
- ፑቲን የአዘርባጃን አውሮፕላን ለመከስከሱ ሩሲያ ተጠያቂ መሆኗን ባያምኑም ሀዘናቸውን ገለጹ29 ታህሳስ 2024
ጦርነቱ ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል። በተለይም በዩክሬን ላይ። 20% ግዛቶቿ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ሲውሉ 10 ሚሊዮን ዜጎች ተፈናቅለዋል።
ፑቲን “ልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን” ብለው በከፈቱት ዘመቻ ሩሲያ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል። ከተሞቿ በሰው አልባ አውሮፕላን ተደብድበዋል።
የሩስያ ኩርስክ ግዛት በዩክሬን ወታደሮች ተይዟል። ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች በሩስያ ላይ ከመጣላቸው ባሻገር በአገር ውስጥ ያለው ሁኔታም ፈታኝ ሆኗል።
ላለፉት ዓመታት ስለ ፑቲን ስዘግብ ነበር። ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ ማለት ነው።
ሥልጣን ሲይዙ 25 ዓመት እንደሚመሩና ዩክሬንን እንደሚወሩ ታስቦ ይሆን?
ምናልባት ቦሪስ የልትሲን ሌላ ሰው እንዲተካቸው ቢመርጡ ታሪክ ሌላ መልክ ይይዝ ይሆን? ብዬ አስባለሁ።

በ25 ዓመታት ውስጥ ብዙ ዓይነት ፑቲኖች አይቻለሁ። የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ኃላፊ ሎርድ ሮበርትሰንም ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥተውኛል።
“የተዋወቅኩት፣ አብሬው ጥሩ ቢዝነስ የሠራሁት፣ አብሬው የኔቶና ሩስያ ካውንስል የመሠረትኩት ፑቲን እና አሁን ያለው እብድ ፑቲን የተለያዩ ናቸው” ይላሉ።
“በ2002 ከጎኔ ቆሞ ዩክሬን ሉዓላዊ አገር ናት ያለው ሰው አሁን ዩክሬን አገር አይለችም ይላል። ፑቲን ስሱና ለአገሩ ትልቅ ሕልም ያለው ሰው ይመስለኛል። ሶቭየት ኅብረት በዓለም ሁለተኛ ልዕለ ኃያል ነበረች። ሩሲያ እንደዛ አትሆንም። ይሄም በራሱ የሚያበሳጨው ይመስለኛል” ሲሉም ያክላሉ።
ምናልባት ሩሲያን ‘ዳግመኛ ኃያል አገር የማድረግ’ ሕልም ይሆናል ፑቲንን የሚገፋፋቸው።
በቀዝቃዛው ጦርነት ሩሲያ ተሸንፋለች ብለው ብዙዎች ማመናቸውን ለመቀልበስም ይሆናል።
ፑቲን ሲናገሩ ግን በውስጣቸው ቂም ያለ ይመስላል።
ሩሲያ ለዓመታት እንደተዋሸችና እንደተናቀች ይሰማቸዋል። ከምዕራባውያን የደኅንነት ስጋትም አላቸው።
ቦሪስ የልትሲን ክሬምሊንን ሲለቁ ፑቲንን “ሩሲያን ጠብቃት!” ያሉትን ቃል ፑቲን እንዳከበሩ ይሰማቸዋል?

ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ሞክሬያለሁ።
ፑቲን በዓመቱ ማገባደጃ ጋዜጣዊ መግለጫ አዘጋጅተው ጋበዙኝ። አራት ሰዓት ተጉዤ ደረስኩ።
“ቦሪስ የልትሲን “ሩሲያን ጠብቃት!” ብለው ነበር” አልኳቸው።
“እርስዎ ‘ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ’ ባሉት ኦፕሬሽን ምክንያት የኩርስክ ግዛት በዩክሬን ወታደሮች መያዙ፣ በሩሲያ ማዕቀብ መጣሉና የኑሮ ውድነት ታዲያ ሩሲያን ከመጠበቅ ጋር አይጋጭም?” ስልም ጠየቅኩ።
“አዎ፤ ያንን ለውጫለሁ። ከውድቀት ጫፍ ተመልሰናል” ሲሉ ነው ፑቲን የመለሱልኝ።
ፑቲን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሩሲያን ሉዓላዊነቷን እንዳላስጠበቁ ተናግረዋል።
ምዕራባውያን “ሩሲያን ለራሳቸው ጥቅም ሲያውሉ ቦሪስን እያበረታቱ ነበር” ብለዋል።
እሳቸው ግን ሩሲያ “ሉዓላዊ አገር እንድትሆን” ሲሉ “የአቅሜን አድርጌያለሁ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ዩክሬን ላይ የከፈቱትን ወረራ በዚህ መንገድ ይሆን የሚያዩት? በወይስ በዘመናዊ የሩሲያ ታሪክ ያላቸው ምልከታ ይህ ይሆን?
እርግጠኛ አይደለሁም። ግን ቁልፍ ጥያቄ እንደሆነ ይሰማኛል።
የጥያቄው መልስ ጦርነቱ የሚያልቅበትን መንገድና የሩሲያን የወደፊት አካሄድ የሚወስን ይሆናል።