ኮቪድ በዉሃን ቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ ተከሰተ

ከ 6 ሰአት በፊት

ኮቪድ በዉሃን ከተማ ከጀመረ አምስት ዓመታት በኋላ የወረርሽኙን አመጣጥ በተመለከተ ቻይና መረጃ እንድታካፍል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አሳስቧል።

“ይህ የሞራል እና ሳይንሳዊ ግዴታ ነው” ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አምስተኛ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

“ግልጽነት፣ መጋራት እና ትብብር ከሌለ ዓለም ለወደፊትም ወረርሽኞችን በበቂ ሁኔታ መከላከል እና መዘጋጀት አትችልም” ሲል አክሏል።

ብዙ ሳይንቲስቶች ቫይረሱ በተፈጥሯዊ መንገድ ከእንስሳት ወደ ሰው ተላልፏል ብለው ቢያስቡም፤ አንዳንዶች ግን ከዉሃን ከተማ ቤተ-ሙከራ አምልጧል የሚል ግምት አላቸው።

ቻይና ሰኞ ዕለት ለወጣው የዓለም ጤና ድርጅት መግለጫ ምላሽ አልሰጠችም። ከዚህ በፊት ግን ከቤተ-ሙከራ አፈትልኳል የሚለውን አስተሳሰብ አጥብቃ ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች።

መስከረም ላይ አንድ የሳይንስ ሊቃውንት ቡድን የኮቪድ ወረርሽኙ ከቤተ-ሙከራ ያመለጠ ሳይሆን ቫይረሱ ያለባቸው እና በገበያ ላይ ከተሸጡ እንስሳት ስለመጀመሩ “ከጥርጣሬም በላይ” ስለመሆኑ ተናግሯል።

እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት እአአ ጥር 2020 ከዉሃን የተገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ናሙናዎችን ከመረመሩ በኋላ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት በመግለጫው ወደ ኮቪድ የመጀመሪያዎቹ ቀናት በመመለስ ከአካባቢያዊ ክስተት ወደ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝት የተለወጠበትን ሂደት በማስታወስ በዓለም ስለነበሩ የእንቅስቃሴ ገደቦች እና በመጨረሻም ክትባቶችን ለማግኘት የተደረገውን ሩጫ አሳይቷል።

ከአምስት ዓመት በፊት እአአ ታህሳስ 31 ቀን 2019 በቻይና የሚገኘው የዓለም ጤና ድርጅት ጽህፈት ቤት በዉሃን የሚገኝ ማዘጋጃ ቤት ድረ-ገጽ ላይ ‘በቫይረስ ስለሚከሰት የሳምባ ምች’ ጉዳይ ላይ የተሰጠውን መግለጫ መከታተሉን ድርጅቱ አስታውቋል።

“ከዚያ በኋላ ባሉት ሳምንታት፣ ወራት እና ዓመታት ኮቪድ-19 የሕይወታችንን እና ዓለማችንን ቅርጽ ቀይሯል።”

የዓለም ጤና ድርጅት እአአ 2020 መገባደጃ ጀምሮ “በፍጥነት ወደ ሥራ ገብቷል” ብሏል። ባልደረቦቹ ጥር 1 የአደጋ ጊዜ ስርዓቶችን እንዴት እንዳስተዋወቁ እና ከሦስት ቀናት በኋላ ለዓለም እንዳሳወቁ አስታውሷል።

“ከጥር 9-12 የዓለም ጤና ድርጅት የመጀመሪያውን አጠቃላይ መመሪያ ለአገሮች አሰራጭቷል። ጥር 13 ደግሞ የመጀመሪያውን የሳርስ-ኮቭ-2 የቤተ-ሙከራ ውጤትን አሳትመናል” ሲል አክሏል።

“በኮቪድ-19 ህይወታቸውን ላጡ እና የታመሙ ሰዎችን ከማሰብ ባለፈ እኛን ለመንከባከብ ብዙ መስዋዕትነት ለከፈሉት የጤና ባለሙያዎች ምስጋናችንን መግለጽ እና ነገን ጤናማ ለማድረግ ከኮቪድ-19 ለመማር ቁርጠኛ መሆን እንፈልጋለን” ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ተናግሯል።

እአአ ግንቦት 2023 ኮቪድ-19 ከአሁን በኋላ “ዓለም አቀፍ ድንገተኛ የጤና አደጋ” አይደለም ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ማስታወቁ አይዘነጋም።

ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በወቅቱ እንደተናገሩት በወረርሽኙ ምክንያት ቢያንስ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል።

እውነተኛው የሟቾች ቁጥር ወደ 20 ሚሊዮን “ሊሆን ይችላል” ሲሉም አክለዋል። ይህም ከኦፊሴላዊው ግምቱ በሦስት እጥፍ ገደማ ከፍ ያለ ነው።

ከዚያን ወዲህም ድርጅቱ ወደፊት ኮቪድ መሰል በሽታዎች ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ቸልተኝነትን እንዳይኖር ሲል ደጋግሞ አስጠንቅቋል።

ቀጣዩ ወረርሽኝ “በማንኛውም ጊዜ ሊመጣ ይችላል” በማለት ዓለም እንዲዘጋጅ ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስ አለም አሳስበዋል።