ጂሚ ካርተር

ከ 44 ደቂቃዎች በፊት

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር ማረፋቸውን ያቋቋሙት ፋውንዴሽን ይፋ አድርጓል።

ጂሚ ካርተር ለረዥም ዓመታት የኖሩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ነበሩ። 100ኛ ዓመት ልደታቸውን ያከበሩት ባለፈው ጥቅምት ነበር።

ዲሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠራው የካርተር ማዕከል እሑድ ከሰዓት ጆርጂያ ግዛት ፕሌንስ ከተማ በሚገኘው ቤታቸው በሰላም ማረፋቸውን አስታውቋል።

የዋተርጌት ቅሌት አሜሪካን ባመሰ ማግስት ነው ጂሚ ካርተር ሕዝባቸውን ላይዋሹ ቃል ገብተው በሰፊ ድምፅ ያሸነፉት።

በጆርጂያ ግዛት የኦቾሎኒ ገበሬ የነበሩት ካርተር ወደ ሥልጣን ሲመጡ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት የሰጡ የመጀመሪያው መሪ ናቸው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ እስራኤል እና ግብፅን በማስታረቅ ስማቸው ይነሳል። ነገር ግን በኢራን የታገቱ አሜሪካዊያንን ማስፈታት እና ሶቪየት ኅብረት አፍጋኒስታንን መውረሯ የሚወቀሱባቸው ጉዳዮች ናቸው።

በ1970ዎቹ ከቻይና ጋር የነበረውን የተሻሻለ ግንኙነት ተከትሎ በ1979 ዋሺንግተን እና ቤይጂንግ ይፋ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሠረቱ።

ይህ ማለት ዩናይትድ ስቴትስ ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት ይቋረጣል፤ በታይፔይ የሚገኘው ኤምባሲዋን ትዘጋለች ማለት ነው።

ካርተር አንድ የሥልጣን ዘመን ከመሩ በኋላ በ1980 በሮናልድ ሬገን በሰፊው ተሸነፉ። በወቅቱ ማሸነፍ የቻሉት 6 ግዛቶች ብቻ ነበር።

ጂሚ ካርተር ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ትኩረታቸውን ወደ ሰላም፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ሰብዓዊ መብት አደረጉ። ለዚህ ሥራቸው የኖቤል የሠላም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ካርተር እና ባለቤታቸው ሮዛሊን በትዳር ለ77 ዓመታት ቆይተዋል። ሮዛሊን ባለፈው ዓመት ኅዳር 2023 ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት። በወቅቱ “እሷ ማለት እኔ ባሳካኋቸው ነገሮች ሁሉ እኩል ተሳታፊ ነበረች” ሲሉ ዘክረዋቸዋል።

በአሜሪካ ታሪክ ረዥም ዓመት የኖሩት ካርተር ጆርጂያ በሚገኘው ቤታቸው ነበር ሕክምና ሲከታተሉ የቆዩት።

ቅርጫት ኳስ እና የባፕቲስት እምነት

ጄምስ ኧርል ካርተር ጁኒየር በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 1924 ነው ጆርጂያ ግዛት በምትገኘው ፕሌንስ ከተማ የተወለዱት። ከቤቱ አራት ልጆች የመጀመሪያው ነበሩ።

አባታቸው ኦቾሎኒ በማምረት ነበር የሚተዳደሩት። እናታቸው ሊሊያን ደግሞ ነርስ ነበሩ።

A younger Jimmy Carter shovelling peanuts
የምስሉ መግለጫ,ጂሚ ካርተር ኦቾሎኒ ሲያመርቱ

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ኮከብ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ነበሩ። ታላቁ የአሜሪካ የምጣኔ ሀብት ቀውስ (ዘ ግሬት ዲፕሬሽን) እና የባፕቲስት ኃይማኖት ተከታይ መሆናቸው ለፖለቲካ ፍልስፍናቸው አስተዋፅዖ አድርጓል።

ለሰባት ዓመታት በአሜሪካ ባሕር ኃይል አገልግለዋል። የጓደኛቸው እህት የሆኑትን ሮዛሊንን ያገቡት በዚህ ወቅት ነው። ነገር ግን አባታቸው መሞታቸውን ተከትሎ ከባሕር ኃይል ተመልሰው የቤተሰቡን እርሻ ማስተዳደር ጀመሩ።

በመጀመሪያው ዓመት በድርቅ ምክንያት ምርት ሳይሰበሰብ ቀረ። ካርተር ይህን ተቋቁመው የቤተሰቡን እርሻ ምርታማ በማድረግ ባለፀጋ መሆን ቻሉ።

ወደ ፖለቲካው ከመግባታቸው በፊት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች እና የቤተ-መፃሕፍት ቦርዶች ውስጥ አገልግለዋል። ቀጥሎ የጆርጂያ ሴኔት አባል ለመሆን ተወዳደሩ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተማሪዎች የቆዳ ቀለም ሳይለዩ እንዲያስተምሩ የሚያዝ ሕግ ማውጣቱን ተከትሎ የአሜሪካ ፖለቲካ ከፍተኛ ሙቀት ላይ ነበር።

ከደቡባዊ ግዛት የመጡት ገበሬው ካርተር ይህን ለውጥ ይቃወማሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ነገር ግን አስተሳሰባቸው ከአባታቸው ለየት ያለ ሆኖ ተገኘ።

በግዛቱ ሴኔት ሁለት ጊዜ ተመርጠው ሲያገለግሉ በተለይ ዲሞክራት ከሆኑ እና ለውጡን ከሚቃወሙ ሰዎች ጋር ላለመጣላት ብዙ ይጥሩ ነበር።

ካርተር በ1970 የጆርጂያ ግዛት ሀገረ-ገዥ ሆነው ተመረጡ። በዚህ ወቅት ለሰብዓዊ መብት ያላቸውን ድጋፍ በይፋ መግለፅ ጀመሩ።

ጂሚ ካርተር እና ማርቲን ሉተር ኪንግ ሲኒየር
የምስሉ መግለጫ,ጂሚ ካርተር እና የማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር አባት

“በግልፅ ልንገራችሁ” አሉ ቃለ-መሐላ በፈፀሙበት ወቅት፤ “የዘር መድልዎ ማብቂያው ጊዜ ደርሷል።”

የአክራሪ ነጮች ማኅበር የሆነው ኩ ክላክስ ክላን ደጋፊዎች ሰልፍ በወጡ ወቅት የጥቁሮች መብት ተሟጋች የሆኑት ማርቲን ሉተር ኪንግን ፎቶ ሰቅለዋል። ጥቁር አሜሪካዊያን እንዲሾሙ የበኩላቸው እንዳደረጉ ይነገርላቸዋል።

ነገር ግን ጠንካራ የክርስትና እምነታቸው እና ሊበራል የሆነው አስተሳሰባቸው በፅንስ ማስወረድ ጉዳይ ተፈተነ። ምንም እንኳ ሴቶች ፅንስ የማቋረጥ መብት አላቸው ቢሉም ይህ እንዲሆን የሚያግዝ በጀት መልቀቅ ተሳናቸው።

ካርተር የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ

ባለጂንሱ ፕሬዝደንት

አሜሪካዊያን ብዙም የማይታቀው ፕሬዝደንት በናፈቁበት ሰዓት ነው ካርተር ብቅ ያሉት።

መጀመሪያ አካባቢ ከሕዝብ የተሰበሰቡ ድምፆች እንደሚያሳዩት በዲሞክራቶች ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት 4 በመቶ ብቻ ነበር። ነገር ግን ከዘጠኝ ወራት በኋላ ተቀማጩ ፕሬዝደንት ጄራልድ ፎርድን ተክተው ተመረጡ።

ጂሚ ካርተር እና ቤተሰቦቻቸው
የምስሉ መግለጫ,ካርተር በ1976 ምርጫ ካሸነፉ በኋላ በቤተሰቦቻቸው ተከበው ንግግር አሰምተዋል

ሥልጣን በያዙ በመጀመሪያ ቀናቸው ወደ ቪየትናም ጦርነት አናቀናም ብለው የታሰሩ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች ምሕረት አደረጉ። ሴቶች በአስተዳደራቸው ቁልፍ ቦታ እንዲይዙም ማድረግ ችለዋል።

የአየር ፀባይ ለውጥን በቁም ነገር የያዙ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ መሪም ተደርገው ይቆጠራሉ። ካርተር ዋይት ሐውስ ሳሉ ጂንስ ሱሪ በሹራብ ማድረግ ያዘወትራሉ። ኃይል ለመቆጠብ ሲሉ የቤተ-መንግሥቱን ማሞቂያ ያጠፉ ነበርም ይባላል። ጣራ ላይ ከፀሐይ ኃይል የሚያመነጩ ቴክኖሎጂዎችን ዘርግተዋል።

ሮናልድ ሬገን ካርተርን ተክተው ሲመጡ ከጣራው ላይ እኒህ ከፀሐይ ኃይል የሚያመነጩ ‘ዲሾች’ እንዲነሱ አዘዙ።

የአሜሪካ ምጣኔ ሀብት መላሸቅ ሲጀምር ካርተር ተቀባይነታቸው እየቀነሰ መጣ። ነዳጅ በራሽን ማከፋፈል የሚሉ ሌሎች ምጣኔ ሀብቱን ለመታደግ የሚሆን ንግግሮች ሲያሰሙ የሚቃወማቸው በዛ።

ዩኒቨርሳል ሄልዝኬር መዘርጋት አለበት የሚል ሐሳብ ሲያነሱ ተቃውሞ ገጠማቸው። የሥራ አጦች ቁጥር ጨመረ። የወለድ መጠኑም አሻቀበ።

ነገር ግን በመካከለኛው ምስራቅ የነበራቸው ተቀባይነት መልካም ነበር። የግብፁ ፕሬዝደንት ሳዳት እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢገን የካምፕ ዴቪድ ስምምነት ተፈራረሙ።

ከባድ የሥልጣን ዘመን

ከሀገራቸው ውጭ የነበራቸው ስኬት ብዙ አልዘለቀም።

በኢራን በተነሳው አብዮት ምክንያት የታገቱ አሜሪካዊያን እና ሶቪየት ኅብረት አፍጋኒስታንን መውረሯ ይጠቀሳሉ።

ካርተር የታገቱትን አሜሪካዊያን ለማስለቀቅ ቴህራን ላይ የንግድ ማዕቀብ ጣሉ። የታገቱትን ለማስለቀቅ በተደረገ ሙከራ ስምንት አሜሪካዊያን ተገደሉ።

ይህ ክስተት ካርተር ድጋሚ እንዳይመረጡ ካደረጋቸው ክስተት ቁንጮው ነው።

ወደ ፖለቲካ ከመግባታቸው በፊት ተዋናይ የነበሩት ሮናልድ ሬገን በምርጫው ዋና ዋና የሚባሉ ግዛቶችን ብቻ ሳይሆን አብዛኛዎቹን ግዛቶች አሸንፈው ወደ ዋይት ሐውስ መጡ።

ካርተር ከሥልጣን ሲወርዱ እጅግ ዝቅ ያለ ተቀባይነት ያላቸው ከሚባሉ የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች መካከል ነበሩ። ነገር ግን ሥልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ ይህን ስማቸውን ለማደስ ብዙ ሠርተዋል።

ፕሬዝደንት ሳዳት፣ ጂሚ ካርተር እና ጠ/ሚ ቤጊን
የምስሉ መግለጫ,ካርተር የግብፅ እና የእስራኤል መሪዎችን ሲያጨባብጡ

ከሥልጣን ወርደው በሠሩት ሥራ የኖቤል ሽልማት ያገኙ ብቸኛው አሜሪካዊ ፕሬዝደንት ናቸው።

ከኔልሰን ማንዴላ ጋር በመሆን ዘ ኤልደርስ የተባለ ለሰላም እና ለሰብዓዊ መብት የሚሠራ የዓለም አቀፍ መሪዎች ኅብረት መሥርተዋል።

ካርተር ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ቀለል ያለ የሚባል ሕይወት ነው የመሩት። በየአዳራሹ እየዞሩ ጠርቀም ያለ ገንዘብ እያጋበሱ ንግግር ማሰማትን አልመረጡም።

ከሚስታቸው ሮዛሊን ጋር በመሆን በተወለዱባት መንደር መኖሩን ምርጫቸው አደረጉ። ከዋይት ሐውስ ወጥተው ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው የተመለሱ ብቸኛው ፕሬዝደንት ናቸው። ሥልጣን ሲለቁ ተመልሰው ሁለት መኝታ ቤት ወዳለው ቤታቸው ዘለቁ።

“ሀብታም የመሆን ህልም ኖሮኝ አያውቅም” ሲሉ በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር።

ዋሺንግተን ፖስት እንደሚለው የካርተር መኖሪያ ቤት ግምቱ 167 ሺህ ዶላር አካባቢ ነው። እሳቸውን ለመጠበቅ ከዳጃፋቸው የቆመው የሲክሬት ሰርቪስ መኪና ከዚያ በላይ ያወጣል።

በ2015 ካንሰር እንዳለባቸው እና እየታከሙ እንደሆነ ይፋ አደረጉ። እናት እና አባታቸው እንዲሁም ሶስት እህቶቻቸው በካንሰር ምክንያት ነው ሕይወታቸውን ያጡት።