December 31, 2024
በቤርሳቤህ ገብረ
በአፋር ክልል በትላንትናው ዕለት በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ በገቢ ረሱ ዞን፤ ዱለሳ ወረዳ፣ ድሩፉሊ ቀበሌ የሚገኙ ከ20 በላይ ቤቶች እና ሱቆች መፍረሳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የወረዳው አስተዳዳሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የመሬት መንቀጥቀጡ ዛሬም አለመቆሙን የገለጹት ነዋሪዎች፤ “ከፍተኛ ስጋት” ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመላው ዓለም የደረሱ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶችን የሚመዘግቡ ተቋማት፤ በአዋሽ አካባቢ ትላንት ሰኞ ታህሳስ 21፤ 2017 ስምንት የመሬት መንቀጥቀጦች መድረሳቸውን አስታውቀዋል። ከእነዚህ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው፤ ከለሊቱ 7 ሰዓት ገደማ የተከሰተው እና በሬክተር ስኬል 5.1 የተለካው የመሬት መንቀጥቀጥ እንደሆነ ከጀርመን የጂኦሳይንስ የምርምር ማዕከል የተገኘው መረጃ ያሳያል።
በአፋር ክልል በዱለሳ ወረዳ፣ ድሩፉሊ ቀበሌ በተለምዶ ቀበና ተብሎ በሚጠራው አነስተኛ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዳውድ አደም፤ ትላንት ለሊት ሰባት ሰዓት ገደማ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ለሰከንዶች የቆየ ቢሆንም፤ በቤታቸው ያለውን ቴሌቪዥን፣ ቁምሳጥን እና ብፌ መሰባበሩን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በመሬት መንቀጥቀጡ ሳቢያ እርሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ ሰባት ያህል ቤቶች “ሙሉ ለሙሉ መውደቃቸውን” እና ፍየሎች ሞተው መመልከታቸውንም አስረድተዋል።
ቤታቸው ከፈረሰባቸው የቀበና ከተማ ነዋሪዎች መካከል አንዱ አቶ ዳንኤል ደርሳ ናቸው። በትላንቱ የመሬት መንቀጥቀጥ ስምንት ክፍል ያለው ቤታቸው እንደፈረሰባቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በትላንትናው ዕለት በተደጋጋሚ ሲከሰት የነበረውን የመሬት መንቀጥቀጥ የሚያደርሰውን ጉዳት በመፍራት፤ ከልጆቻቸው እና ከባለቤታቸው ጋር የአስፓልት መንገድ ዳር ማደራቸውንም አክለዋል።
የዱለሳ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አሊ ደስታ፤ በአካባቢው በተከታታይ እየተከሰተ ያለውን የመሬት መንቀጥቀጥ የገለጹት “እረፍት የለውም” በሚሉ ቃላት ነው። ባለፉት ቀናት በተከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦች የአስፓልት መንገድ መሰንጠቅ ማጋጠሙን እና በተወሰኑ መንደሮች ውሃ መፍለቁን አቶ አሊ ገልጸዋል።
በትላንት ለሊቱ ርዕደ መሬት፤ በድሩፉሊ ቀበሌ የሚገኙ ከ20 በላይ ቤቶች እና ሱቆች እንደፈረሱም የወረዳው አስተዳዳሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። በዛሬው ዕለት የዞን እና የወረዳ ባለስልጣናት ከአደጋ መከላከል ቡድን ጋር በመሆን በቀበሌው የደረሰውን ጉዳት በስፍራው ተገኝተው መመልከታቸውንም አስረድተዋል።
ከ6,000 በላይ ሰዎች የሚኖሩባት የድሩፍሊ ቀበሌ፤ ከከሰም ስኳር ፋብሪካ አቅራቢያ የምትገኝ ናት። ከትላንቱ አደጋ በኋላ የአካባቢው ነዋሪዎች በአቅራቢያው ወዳሉ ከተማዎች እየሸሹ መሆኑን የወረዳው አስተዳዳሪ እና ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የቀበና ከተማ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው እየወጡ ያሉት በአይሱዚ የጭነት መኪና እና በሌሎች የትራንስፖርት አማራጮች እንደሆነ አቶ ዳውድ ተናግረዋል። ከድሩፉሊ ቀበሌ በአቅራቢያው ወዳለው የአዋሽ አርባ ከተማ እየሸሹ ከሚገኙት ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውን የቀበና ከተማ ነዋሪው አመልክተዋል።
በተመሳሳይ መልኩ ባለቤታቸውን እና ልጆቻቸውን ወደ አዋሽ ሰባት ከተማ መላካቸውን የሚገልጹት አቶ ዳውድ፤ እርሳቸው በቀበና ከተማ የቀሩት ንብረቶቻቸውን ለመጠበቅ እንደሆነ አብራርተዋል። “ከፍተኛ ነገር ከመከሰቱ በፊት መላ ልንባል ይገባል። መውጣት አልቻልንም። የትራንስፖርት ገንዘብ ያለው አለ፤ የሌለው አለ። ያለንን ለልጆቻንን ሰጥተን ነው የሸኘነው” ሲሉ አቶ ዳውድ የችግሩን አሳሳቢነት ጠቁመዋል።
“ከፍተኛ ነገር ከመከሰቱ በፊት መላ ልንባል ይገባል። መውጣት አልቻልንም። የትራንስፖርት ገንዘብ ያለው አለ፤ የሌለው አለ። ያለንን ለልጆቻንን ሰጥተን ነው የሸኘነው”– አቶ ዳውድ አደም፤ የቀበና ከተማ ነዋሪ
አቶ ዳውድ ያነሱት ችግር በሌላኛው የቀበና ከተማ ነዋሪ አቶ ዳንኤልም ተስተጋብቷል። አቶ ዳንኤል በ32 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ አዋሽ ሰባት ከተማ ለመሄድ የትራንስፖርት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ እዚያው ከቤተሰቦቹ ጋር ለመቆየት መገደዳቸውን ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎችን በሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ ለማድረግ በመንግስት በኩል እየተደረገ ያለ ጥረት ምን እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የዱለሳ ወረዳ አስተዳዳሪ፤ “ዛሬ ወደ ቦታው የሄድነው የማረጋጋት ስራም ለመስራት፤ ያንን ነገርም ለመወሰን ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የፌደራል እና የአፋር ክልል የአደጋ መከላከል ቡድን ወደ አካባቢው እየመጣ መሆኑን የገለጹት አቶ አሊ፤ የማስፈሩን ጉዳይ በተመለከተ ውሳኔ የሚጠበቀው ከእዚህ ቡድን መሆኑን አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)