
ከ 7 ሰአት በፊት
የቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ በምዕራብ አፍሪካ ያላት ተፅዕኖ እየቀነሰ በመጣበት ወቅት አይቮሪ ኮስት የፈረንሳይ ወታደሮች ከሀገሯ እንደሚወጡ አስታውቃለች።
የአይቮሪ ኮስት ፕሬዝደንት አላሳኔ ኡዋታራ አዲሱን የፈረንጆቹ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባሰሙት ንግግር ነው ይህን ያስታወቁት።
የሀገራቸው መከላከያ ሠራዊት መዘመኑን እና መጠናከሩን የጠቀሱተ ፕሬዝደንቱ የፈረንሳይ ወታደሮች እንደሚወጡ ገልፀዋል።
በተያያዘ ዜና ፈረንሳይ ወታደራዊ ካምፖቿን እንደምትዘጋ ያስታወቀችው ሴኔጋል ወታደሮች በአዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት መገባደጃ እንደሚወጡ ገልፃለች።
አይቮሪ ኮስት በምዕራብ አፍሪካ ትልቁ የፈረንሳይ ተጠባባቂ ጦር ያላት ሀገር ናት።
በአይቮሪ ኮስት 600 ገደማ የፈረንሳይ ወታደሮች አሉ። በሴኔጋል የሚገኙት የፈረንሳይ ወታደሮች ቁጥር 350 ነው።
“በጋራ ውሳኔ ላይ በደረስነው መሠረት የፈረንሳይ ወታደሮች አይቮሪ ኮስትን ለቀው ይወጣሉ” ሲሉ ፕሬዝደንት ኡዋታራ ተናግረዋል።
በፈረንሳይ ወታደሮች የሚመራው ፖርት ቦዌት ወታደራዊ ካምፕ ለአይቮሪ ኮስት ወታደሮች ተላልፎ እንደሚሰጥም አስታውቀዋል።
- ጂሚ ካርተር ለመንግሥቱ ኃይለማርያም የላኩት ደብዳቤከ 9 ሰአት በፊት
- የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት በመላው ዓለም በድምቀት ተከበረከ 8 ሰአት በፊት
- ኤፍቢአይ በታሪክ ከፍተኛው ነው ያለውን የፈንጂ ክምችት የእርሻ ማሳ ውስጥ አገኘከ 8 ሰአት በፊት
በአውሮፓውያኑ በ1960ዎቹ በምዕራብ አፍሪካ የነበራት የቅኝ ግዛት የተገባደደው ፈረንሳይ ወታደሮቿን ከማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኒጀር አስወጥታለች።
በሶስቱ ሀገራት በተካሄደው መፈንቅለ-መንግሥት ምክንያት ነው የፈረንሳይ ወታደሮች ለመውጣት የተገደዱት። አልፎም በምዕራብ አፍሪካ ፀረ-ፈረንሳይ የሆነ አስተሳሰብ እየተንሰራፋ መጥቷል።
በአካባቢው ያሉት ኢስላሚክ ሚሊሻዎችን በመዋጋት ረገድ የምዕራባዊያኑ አጋር የሚባለው የቻድ መንግሥት ባለፈው ኅዳር በድንገት ከፈረንሳይ ጋር የገባውን ወታደራዊ ስምምነት መሻሩ ይታወሳል።
የሴኔጋሉ ፕሬዝደንት ባሲሩ ፋየ “ከ2025 ጀምሮ በሴኔጋል የሚገኙ ሁሉም የውጭ ሀገር ወታደሮች እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ” ብለዋል።
ባለፈው መጋቢት የተመረጡት ፋየ ሥልጣን ከጨበጡ ሉዓላዊነት እንደሚያስከብሩ እና ሀገራቸውን ከውጭ ሀገራት ጥገኝነት እንደሚያላቅቁ ቃል-ገብተው ነበር።
ፈረንሳይ አሁን በጋቦን የተወሰኑ ወታደሮች ይኖሯታል ማለት ነው።
የኒጀር፣ ማሊ እና ቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ መሪዎች የፈረንሳይ ወታደሮችን ካባረሩ በኋላ ፊታቸውን ወደ ሩሲያ አዙረዋል።
ሩሲያ ጂሃዲስት ታጣቂዎችን ለመዋጋት ወደ ሳሕል በረሀ ወታደሮቿን ልካለች።
ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ፈረንሳይ በጂቡቲ እና በጋቦን ካሏት 2 ሺህ ገደማ ወታደሮች በቀር በአፍሪካ ያላት ተፅዕኖ እየቀነሰ መጥቷል።
የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ፈረንሳይ በአፍሪካ ያላትን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ተፅዕኖ ለማስቀጠል ጥረት እያደረገች ነው።
ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ከተላቀቀች ሶስት አስርታት ያለፏት አይቮሪ ኮስት (በፈረንሳይኛ ስሟ ኮት ዲቯር) በኃይማኖታዊ መቻቻል እና ሕብረ ብሔራዊነት እንዲሁም በምጣኔ ሀብት ዕድገት ትታወቅ ነበር። ነገር ግን በሀገሪቱ የታጣቂዎች መንሰራፋት አለመረጋጋት እንዲሰፍን አድርጓል።
አይቮሪ ኮስት በዓለማችን ቁጥር አንድ የካካዋ ፍሬ አምራች ስትሆን በቀጣናው ካሉ ሀገራት በተነፃፃሪ የተሻለ ምጣኔ ሀብት አላት።