
ከ 9 ሰአት በፊት
እአአ በታኅሣሥ 31/1999 የአሜሪካ ሰንደቅ አላማ ወርዶ የፓናማ ተተካ። በፓናማ ካናል የፓናማ ሰንደቅ አላማ ለመጀመሪያ ጊዜ ተውለበለበ።
የፓናማ ዜጎች ደስታቸውን ገለጹ። ለዓመታት የነበረው ተቃውሞ፣ ውጥረትና ሞት ምላሽ አገኘ።
ለብዙ ዓመታት ፓናማ ካናልን ያስተዳደረው አልቤርቶ አልማን ዙቤይታ “የፓናማ ሰዎችን ስሜት ማየት አስደሳች ነበር” ይላል።
ከ25 ዓመታት በኋላ የአካባቢው ሉዓላዊነት ውዝግብ አስነስቷል። ይህም የተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግርን ተከትሎ የሆነ ነው።
አሜሪካ በካናሉ ዕቃ ለማጓጓዝ የምትከፍለውን አስመልክተው “ገንዘብ እየተወሰደብን ነው” ሲሉ ትራምፕ ተደምጠዋል።
“ፓናማ ካናል በአፋጣኝ፣ ሙሉ በሙሉና ያለ ምንም ጥያቄ ለአሜሪካ እንዲመለስ ነው የምንፈልገው” ብለዋል ትራምፕ።
የፓናማ ፕሬዝዳንት ሆዜ ራኡል ሙሊኖ “እያንዳንዱ የካናሉ ክፍል የፓናማ ሆኖ ይቀጥላል” ብለው ምላሽ ሰጥተዋል።
የፓናማ ካናል ታሪክ
አትላንቲክ ውቅያኖስን ከፓስፊክ ውቅያኖስ ጋር የሚያገናኝ መስመር መፈለግ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓውያን ዋነኛ ጥያቄ ነበር።
በወቅቱ ወደ ደቡባዊ የውቅያኖሱ አካባቢ ለመሄድ በደቡባዊ ቺሊ በኩል በማጄላን ሰርጥ ማለፍ የግድ ነበር።
አስቸጋሪ የአየር ሁኔታን ማለፍ የሚጠይቅ ጉዞ ነው። አካባቢው በኮሎምቢያ ግዛት ሥር ነበር።
ኮሎምቢያ ፈቃድ ከሰጠች በኋላ ነው ካናሉ የተሠራው። ፈረንሳዊው መኃንዲስ ፈርዲናንድ ደ ለስፔስ የግብፁን ካናል ከሠራ በኋላ የፓናማ ካናልንም እንዲሠራ ተወስኗል።
አብዛኞቹ በባርነት የተያዙ አፍሪካዊያን ሠራተኞች በሕመም ይሰቃዩ ነበር። የአካባቢው ሙቀትና የማያቋርጥ ዝናብ ፕሮጀክቱን አከሰረው።
- ትራምፕ ለገበያ ያልቀረቡትን ግሪንላንድ እና ፓናማ ካናል ለምን መቆጣጠር ፈለጉ?27 ታህሳስ 2024
- ዴንማርክ የትራምፕን ግሪላንድን “እቆጣጠራለሁ” ንግግር ተከትሎ የግዛቲቷን መከላከያ በጀት አሳደገች25 ታህሳስ 2024
- ኤለን መስክ “በንግግር ነጻነት” ስም ትራምፕ እንዲያሸንፉ አግዞ ይሆን?26 ታህሳስ 2024
አሜሪካ በአካባቢው ፍላጎት ያሳደረችው በዚህ ወቅት ነው።
ኮሎምቢያ ከእርስ በእርስ ጦርነት እየወጣች ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ ሞተዋል። የፖለቲካ ውጥረቱም ከፍተኛ ነበር።
ይህ ውጥረት ፓናማ ነጻ እንድትወጣ አግዟል።
አሜሪካ ፖርተ ሪኮ እና ኩባን ተቆጣጥራ በኮሎምቢያ ያለውን ውስጣዊ ቀውስ ለመጠቀም እየሞከረች ነበር።
የፓናማ ካናልን ግንባታ ለማጠናቀቅ 40 ሚሊዮን ዶላር ለመመደብ ስምምነት ላይ ተደረሰ።
ኮሎምቢያ እና አሜሪካ ሀረን-ሄይ የተባለ ስምምነት የፈረሙት በዚህ መንገድ ነበር።
እአአ ነሐሴ 5/1903 የኮሎምቢያ መንግሥት ስምምነቱ የአገሪቱን ሉዓላዊነት ስለማይጠብቅ እንደማይቀበለው አስታወቀ።
ፓናማ በወቅቱ በኮሎምቢያ ሥር ነበረች። ፓናማ ግን የኮሎምቢያን ተቃውሞ ችላ ብላ ከአሜሪካ ድጋፍ በመውሰድ ግንባታው እንዲቀጥል አድርጋ እአአ ኅዳር 3/1903 ነጻነቷን አወጀች።
የፓናማ ታሪክ ባለሙያ ማሪክሳ ላሶ “አሜሪካ ፓናማ ነጻ ስትወጣ ያለ ኮሎምቢያ ጣልቃ ገብነት ስምምነት መፈረም እንደምትችል ተገነዘበች” ይላሉ።

የውጥረቱ መነሻ
ፓናማ ነጻ ከወጣች በኋላ ሁለቱም አገራት ስምምነቱን ፈረሙ። በስምምነቱ መሠረት ፓናማ ነጻ አገርነቷ ሲረጋገጥ አሜሪካ ደግሞ በፓናማ ካናል አካባቢ ካናል ዞንን ለመቆጣጠር ወሰኑ።
ይህ ፓናማ ዞን ስምንት ኪሎ ሜትር ሲሆን ከውሃው አካል አንጻር ስትራቴጂያዊ ነው። ፓናማ በምላሹ 10 ሚሊዮን ዶላር ትቀበል ነበር።
እአአ በ1913 አንኮን የተባለ መርከብ ለመጀመሪያ ጊዜ ውሃውን አቋርጦ ተጓዘ።
አካባቢው ብዙም ሳይቆይ ውጥረት ውስጥ ገባ።
ፓናማ ለሁለት ተከፍላ በአንድ በኩል በሺዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን በራሳቸው ሕግ ይተዳደሩ ነበር።
ፓናማ ካናል በይፋ የተመረቀው እአአ በ1914 ነበር። አሜሪካውያን ከፓናማውያን ጋር ተዋህደው አልነበረም የሚኖሩት። ወደሌላ የፓናማ ግዛት የሚጓዙት ፈቃድ ሲሰጣቸው ነበር።
ፓናማውያን በጊዜ ሒደት ቂም ቋጥረው ነበር። በፓናማ ካናል አሜሪካውያን መኖራቸው በመቃወም ሰልፎች ተካሂደዋል።
እአአ በ1958 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ‘ኦፕሬሽን ሶቨርኒቲ’ በሚል ንቅናቄ ጀመሩ። የአሜሪካ ግዛት ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ 75 የፓናማ ሰንደቅ አላማ አኖሩ።
የተማሪዎች ንቅናቄ ከመሩት አንዱ ሪካርዶ ሪዮስ ቶረስ “እዚህ አካባቢ የፓናማ ዜጎች መንቀሳቀስ አይችሉም አሉን። ስምምነቱ እንዲሰረዝ በድፍረት ጠየቅን” ይላል።

እአአ በ1959 በተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የፓናማ ዜጎች ሰንደቅ አላማቸውን ይዘው ካናል ዞን እንዲገቡ ተደርጓል።
ሰልፉ በሰላማዊ መንገድ ቢጀመርም ተቃዋሚዎች መጓጓዝ ሲከለከሉ ከፖሊስ ጋር ግጭት ተነሳ። በግጭቱ በርካቶች ቆስለዋል።
‘ሰንደቅ አላማ የሚተክል ሉዓላዊነት ያገኛል’ በሚል በፓናማውያን ዘንድ ክስተቱ በታሪክ ይታወሳል።

የመታሰቢያ ቀን
በቀጣይ ዓመታትም ተቃውሞ ተጠናክሮ ቀጠለ።
በፓናማው ፕሬዝዳንት ሮቤርቶ ቻይሪ እና በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ መካከል እአአ በ1962 ስምምነት ላይ ተደርሶ፣ የሁለቱም አገራት ሰንደቅ አላማ በካናል ዞን እንዲውለበለብ ተደረገ።
ከሁለት ዓመት ስምምነቱ ተግባራዊ በሚደረግበት ቀን ግን በካናል ዞን የሚኖሩ ሰዎች ትዕዛዝ በመጣስ የፓናማን ሰንደቅ አላማ አንሰቅልም አሉ።
የፓናማ ናሽናል ኢንስቲትዩት ተማሪዎች ከቀናት በኋላ የትምህርት ቤት ሰንደቅ አላማ ይዘው ወደ ካናል ዞን አቀኑ።
የአሜሪካ ፖሊሶች ተማሪዎቹን ሲያስቆሟቸው በተነሳ ተቃውሞ 20 ተማሪዎች ሲሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጎዱ።
ይህ ቀን የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን ተብሎ ይታወሳል።
የፓናማው ፕሬዝዳንት ከአሜሪካ ጋር ዲፕሎማሲያው ግንኙነት አቋረጡ። ስምምነቱ እስከሚተገበር ድረስ ግንኙነቱ እንደማይታደስ ገለጹ።
ከ35 ዓመታት በኋላ የፓናማ ካናል ለፓናማ የተመለሰው በዚህ ክስተት ምክንያት እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።

የሁለቱ አገራት ስምምነት
እአአ በ1964 በአሜሪካ እና ፓናማ መካከል ውይይት ተጀመረ። ልዩ አምባሳደር በመሾም ድርድር እንዲካሄድ ወሰኑ።
በፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን አስተዳደር ሥር ስምምነት እስከሚፈረም ድረስ ግን 10 ዓመታት ወሰደ።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄንሪ ኪሲንጀር እና የፓናማ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ሁዋን አንቶኒዮ ታክ ናቸው።
የፓናማ ካናልን በተመለከተ በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ያለው አሠራር ለመዘርጋት ስምምነቱ ይረዳል ተብሎ ነበር።
በዚህ መሠረት አሜሪካ በሄይ-ቡናቡ-ቫሪላ ስምምነት የተሰጣት መብት በፓናማ ሥር የሚተዳደር ሆነ።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር እና የፓናማ ብሔራዊ ዘብ ኮማንደር ኦማር ቶርጆንስ በ1977 የተስማሙትም ይህንን ነበር።
ጂሚ ካርተር ካናሉን አሜሪካውያን ለፓናማውያን መመለሳቸው “እንደ ትልቅና ኃያል አገር ፍትሐዊ፣ ኩሩና ሉዓላዊነት የምናከብር መሆናችንን ያሳያል” ብለዋል።
ከሽግግር ጊዜ በኋላ ካርተርን ጨምሮ የዓለም መሪዎች የፓናማን ድል ለማክበር በአገሪቱ ተገኙ።
የፓናማው ፕሬዝዳንት ሚሬያ ሞስኮሶ የፓናማን ሰንደቅ አላማ በይፋ በፓናማ ካናል አስተዳደር ሕንጻ ሰቀሉ።
ፕሬዝዳንቱ “ፓናማና ፓናማ ካናል የፓናማውያን ነው። ፓናማ ሙሉ በሙሉ ሉዓላዊ አገር ሆናለች” ብለው ተናገሩ።