
ከ 9 ሰአት በፊት
ካማላ ሀሪስ በአሜሪካ የምክትል ፕሬዝዳንትነት ታሪካቸው ካደረጓቸው ጉዞዎች መካከል የአፍሪካ ጉብኝታቸው ይታወሳል።
ጋና፣ ታንዛኒያ እና ዛምቢያ ሲጓዙ ለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች መብት መሟገታቸው ትችት አስከትሎባቸው ነበር።
ጋና ሳሉ “ሁሉም ሰዎች እኩል መታየት አለባቸው” ሲሉ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትና የመብት ንቅናቄን ወንጀል የሚያደርገውን የአገሪቱን ረቂቅ ሕግ ተችተዋል።
የጋና ቃል አቀባይ አልባን ባጊን በበኩላቸው የካማላ ሀሪስን ንግግር “ኢ-ዴሞክራሲያዊ” ብለው፣ ሕግ አውጪዎች “ማንንም አትፍሩ” ሲሉ ተናግረዋል።
በታንዛኒያም የአገሪቱ የቀድሞ ሚኒስትር አሜሪካ ለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች የምታደርገውን ድጋፍ ነቅፈዋል።
የዛምቢያ ተቃዋሚዎች ደግሞ ሰልፍ እንደሚወጡ አስታውቀዋል።
ምን ያህል አገሮች የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን በሕግ ያግዳሉ?
የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን ወንጀል ያደረጉ 64 አገሮች ያሉ ሲሆን፣ ግማሹ አፍሪካ ውስጥ ይገኛሉ።
አንዳንድ የአፍሪካ አገራትና በሌሎች አህጉራት ያሉ አገራትም የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን በሕግ ፈቅደው የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች የመብት ጥበቃም እየተሻሻለ እንዲመጣ አድርገዋል።
ታኅሣሥ 2022 የሲንጋፖር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አወዛጋቢ የሆነውንና በሁለት ወንዶች መካከል ግንኙነትን ወንጀል የሚያደርገውን ሕግ ሰርዟል።
በዛው ወር ባርቤዶስ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን ወንጀል የሚያደርገውን ሕግ ሰርዛለች።
አንቲጓ ኤንድ ባርቢውዳ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን ወንጀል የሚያደርገውን አንቀጽ ሕገ ወጥ ስትል አውጃለች።
የተመሳሳይ ጾታ ግንኑነት በኢትዮጵያ ውስጥ ሕገ-ወጥ ሲሆን ከ10 ቀናት እስከ ሶስት ዓመታት በሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣ የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያሳያል።
- በቲክቶክ ከወንድ ጋር ሲደንስ መታየቱ ሕይወቱን ሊያሳጣው የነበረው ኢትዮጵያዊ7 ታህሳስ 2023
- ፖፕ ፍራንሲስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለተመሳሳይ ጾታ ጥንዶች ቡራኬ ልትሰጥ እንደምትችል ጠቆሙ3 ጥቅምት 2023
- የክሪስታል ፓላሱ አምበል የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ባንዲራ ላይ ‘እየሱስን እወደዋለሁ’ ብሎ መፃፉ አነጋጋሪ ሆነ4 ታህሳስ 2024
በ2021 የአንጎላ ፕሬዝዳንት ዣዎ ሎውሬንሶ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን የሚፈቅድ ሕግ አፅድቀዋል። ሰዎች በፆታ ግንኙነት ፍላጎታቸው የተነሳ መድልዎ እንዳይደረግባቸው የሚጠብቅ ሕግ ላይም ፊርማቸውን አኑረዋል።
በ2020 ጋቦን የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን የተመለከተውን ሕጓን አሻሽላለች። የተመሳሳይ ፆታ የወሲብ ግንኙነት በስድስት ወርና በገንዘብ የሚያስቀጣ ሆኗል።
የቦትስዋና ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ2019 የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን ሕጋዊ ለማድረግ ውሳኔ አሳልፏል።
ሞዛምቢክና ሲሸልስም የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን ወንጀል የሚያደርጉ ሕጎችን ሰርዘዋል።
ናይጄሪያ እና ኡጋንዳን ጨምሮ ሌሎችም አገራት የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን አሁንም ድረስ ወንጀል ብለው ፈርጀዋል።

የኡጋንዳ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ምክንያት ሆኗል።
በአንዳንድ አገራት የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን ወንጀል የሚያደርግ ሕግን ለማስሻር የተደረጉ ጥረቶች ውጤት አላሳዩም።
የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች የመብት ተሟጋቾች በተቋምነት እንዳይመዘገቡ ማድረግ እንደማይቻል የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢወስንም በአገሪቱ ሕግ ግን የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ሕገ ወጥ ተብሏል።
የቅኝ ግዛት ውጤት
አብዛኞቹ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን ወንጀል የሚያደርጉ ሕጎች የወጡት በቅኝ ግዛት ወቅት ነው።
ሕጉን መጣስ በብዙ አገራት ለረዥም ዓመታት እስራት ይዳርጋል።
በኮመንዌልዝ ውስጥ ካሉ 53 አገራት መካከል 23 የሚሆኑት የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን በሕግ ከልክለዋል። ይህ የአገራት ስብስብ በአብላጫው በእንግሊዝ ቅኝ የተገዙ አገራት ነው።
ለዚህ መነሻ የሆኑት የእንግሊዝ ሕጎች በተመሳሳይ ፆታ ግንኙንት ውስጥ ያሉ ወንዶችን ቢሆንም በጊዜ ሒደት በሴቶች ላይም ተግባራዊ ሆኗል።
ዓለም አቀፉ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች መብት ተሟጋች ኢልጋ በዓለም ላይ ያሉ ሕጎችን ይከታተላል።
በኢራን፣ ብሩንዲ፣ ሞሪሸስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የመን፣ ሰሜናዊ የናይጄሪያ ግዛቶች የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች በሞት እንዲቀጡ በሕግ መደንገጉን ተቋሙ ይገልጻል።
ሱዳን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች የሞት ቅጣትን በ2020 ሽራለች።
የመብት ተሟጋች ተቋሙ እንደሚለው ከሆነ አንዳንድ አገራት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ላይ የሚደርሰውን የሕግ ጫና እየቀነሰ ነው።
በ2017 የወጣ ሪፖርት እንደሚጠቁመው በጃማይካ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ጠል ማኅበረሰብ ቢኖርም የመንግሥት ባለሥልጣናት ግን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎችን በሕግ ለመጠየቅ እምብዛም ጫና ሲያደርጉ አይስተዋልም።
ሆኖም ግን የመብት ተሟጋች ተቋማት እንደሚሉት የንቅናቄ ሥራቸው እንዲገደብ የሚያደርጉ አገራት አሉ።

የለውጥ ጎዳና
የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን ወንጀል የሚያደርጉ ሕጎችን በመሻር ረገድ አገራት ለውጥ እያሳዩ ነው።
እስካሁን ድረስ 33 አገራት ለተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ዕውቅና ሲሰጡ 34 አገራት ደግሞ በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ላሉ ጥንዶች ዕውቅና ይሰጣሉ።
በአፍሪካ ለተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ዕውቅና የተሰጠው በደቡብ አፍሪካ እና በፈረንሳይ ደሴቶች ማዮቴና ሪዩኒዮን ነው።