ፈንጂዎች

ከ 8 ሰአት በፊት

ኤፍቢአይ ቨርጂኒያ በሚገኝ እርሻ ማሳ ባደረገው ፍተሻ ከ150 በላይ ቦምቦች ማግኘቱን አስታወቀ። ይህ ቁጥር በታሪኩ ከፍተኛው መሆኑን ተቋሙ ገልጿል።

ብራድ ስፓፎርድ የተባለ ግለሰብ ከዋሽንግተን ዲሲ በስተደቡብ 290 ኪሜ ርቀት ላይ በሚገኘው እና ከባለቤቱ እና ከሁለት ህጻናት ልጆቹ ጋር በሚኖርበት ዋይት ካውንቲ የጦር መሳሪያዎችን እያከማቸ እንደሆነ ጥቆማ ከተሰጠተበት በኋላ በታህሳስ 17 በቁጥጥር ስር ውሏል።

መርማሪዎቹ እንዳሉት አንዳንድ መሳሪያዎች መኝታ ክፍል ውስጥ “#ኖላይቭስማተር” የሚል ጽሑፍ ባረፈበት አነስተኛ ቦርሳ ውስጥ ደህንነቱ ባልተጠበቀ መልኩ ተገኝተዋል። ጽሑፉ የቀኝ ዘመም እና ፀረ-መንግስት እንቅስቃሴን የሚያመለክት ነው ተብሏል።

ደንበኛቸው ለማህበረሰቡ አደገኛ አለመሆኑን በመግለጽ ችሎት ፊት እስኪቀርብ ድረስ እንዲፈታ ሲሉ የስፓፎርድ ጠበቃ ጥያቄ አቅርበዋል።

ተጠርጣሪው እስካሁን የተከሰሰው ያልተመዘገቡ አነስተኛ መሣሪያዎችን በመያዝ ብቻ መሆኑን የጠቀሱት መርማሪዎች ተጨማሪ ክስ ሊመሰርቱ እንደሚችሉ አክለዋል።

መርማሪዎች ማክሰኞ እንዳስታወቁት ከሆነ ቦምቦቹ “በኤፍቢአይ ታሪክ ዝግጁ በሆኑ ፈንጂዎች ብዛት ከፍተኛው ነው።”

ስፓፎርድ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ፎቶዎች ለዒላማ ተኩስ ልምምድ ከመጠቀም ባለፈ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ እንደሚገደሉ ያለውን ተስፋ ገልጿል ተብሏል።

በቅርቡ በአካባቢው ከሚገኝ የተኩስ መለማመጃ የስናይፐር መተኮስ ብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት ፍላጎት እንደነበረው ከፍርድ ቤት የተገኙ ሰነዶች ጠቁመዋል።

በስም ያልተጠቀሰ ጎረቤት እንደጠቆመው ከሆነ ስፓፎርድ እአአ በ2021 “በቤት ውስጥ የሚዘጋጅ ፈንጂ ሲሠራ” የቀኝ እጁን ሦስት ጣቶች ካጣ በኋላም ቦምቦችን ማዘጋጀቱን መቀጠሉን የፍርድ ቤት ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።

በህግ አስከባሪነት ይሠራ የነበረው ጎረቤቱ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የስፓፎርድን 20 ሄክታር እርሻን በጎበኘበት ወቅት በድብቅ ቪዲዮ ቀርጾ ነበር ሲሉ መርማሪዎች ተናግረዋል።

በጎረቤቱ የተሰበሰበው ማስረጃ ተከትሎ ኤፍቢአይ ንብረቱ እንዲፈተሽ አድርጓል። በዚህም ፈንጂዎች በቤት ውስጥ ተበታትነው መገኘታቸውን የክስ ሰነዱ ያስረዳል።

የተቋሙ የመጀመሪያ ምርመራ እንደሚያሳየው መሳሪያዎቹ “የቧንቧ ቦምቦች” መሆናቸውን አረጋግጧል። አብዛኛዎቹ ተለይቶ በተሠራ ጋራዥ ውስጥ የነበሩ እና በየቀለማቸው የተደረደሩ ናቸው። አንዳንዶቹ “ገዳይ” የሚል ጽሑፍ ሰፍሮባቸዋል።

በርካታ ቦምቦች በልብሶች ላይ ተገጥመው መገኘታቸውን የፍርድ ቤቱ ሰነድ ገልጿል።

ደህንነታቸው ያልተጠበቀ ተጨማሪ ቦምቦች በቤት ውስጥ በሚገኝ አነስተኛ የጀርባ ቦርሳ ውስጥ ተገኝተዋል”። ቦርሳው ላይ “#ኖላይቭስማተር” የሚል ጽሑፍ እንዳረፈበት የፍርድ ቤት ሰነዶች ላይ ሰፍሯል።

የኒው ጀርሲ የአገር ውስጥ ደህንነት እና ዝግጁነት ቢሮ እንደገለጸው ከሆነ ኖላይፍስማተር አክራሪ ርዕዮተ ዓለምን የሚያስፋፋ፣ ጥቃቶችን፣ የጅምላ ግድያዎችን እና የወንጀል ድርጊቶችን የሚያበረታታ እንቅስቃሴ ሲሆን አባላቱ እራሳቸውን እንዲጎዱ እና በእንስሳት ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ የሚቀሰቅስ ነው።

ከቦምቦች በተጨማሪ መርማሪዎች ኤችኤምቲዲ የተባለ በቀላሉ የሚፈነዳ ፈንጂ የያዘ ዕቃ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። እንደኤፍቢአይ መረጃ ከሆነ በተለዋዋጭ የሙቀት ለውጥ ብቻ ሊፈነዳ የሚችል እና ማፈንጃ የማያስፈልገው ነው ብለዋል።

ኤችኤምቲዲ የያዘው ዕቃ “አደገኛ” እና “አትንኩት” የሚል ጽሑፍ ያረፈበት ሲሆን ምግብ በያዘ ማቀዝቀዣ ውስጥ የተከማቸ ነበር ሲል የፍርድ ቤት ሰነዱ ያስረዳል።

ስፓፎርድ በጦር መሳሪያ ንብረቱን ለመጠበቅ መወያየቱን ጎረቤቱ እንደገለጸ መርማሪዎች ተናግሯል።

በማሽን ሱቅ ውስጥ ይሠራ የነበረው ስፓፎርድ በዜና ላይ የጠፉ ህጻናት በፌደራል መንግስት ተወስደው በአልሞ ተኳሽነት እንዲሰለጥኑ መደረጉን መናገሩን የፍርድ ቤቱ ሰነዶች ገልጸዋል።

የስፓፎርድ ጠበቃ ማክሰኞ ዕለት እንዳሉት ከሆነ መንግስት ግለሰቡን አደገኛ ነኝ ማለቱ “መላምት እና ፍርሃትን መንዛት ብቻ ነው።” ምክንያቱም ተጠርጣሪው ቀደም ሲል ምንም አይነት የወንጀል ሪከርድ አልነበረውም።

“ስፓፎርድ በሰዎች ላይ ስለመዛቱም ሆነ በፖለቲካዊ አመለካከቱ እና በአስተያየቶቹ ምክንያት አደጋ ሊፈጥር ይችላል ስለመባሉ ምንም አይነት ማስረጃ የለም” ሲሉ ጠበቃው ጽፈዋል።

ጉዳዩን የሚከታተሉት የፌደራል ዳኛ ስፓፎርድ በኤሌክትሮኒክ ክትትል እየተደረገበት እንዲለቀቅ አዘዋል።

መንግስት ተጠርጣሪውን በቅድመ ችሎት ማሰር ስለሚፈልግ ውሳኔው እንዲዘገይ አድርጓል።