ጂሚ ካርተር በማዕከላቸው በኩል የኢትዮጵያን ምርጫ ለመታዘብ በመጡ ወቅት - በአውሮፓውያኑ 2005
የምስሉ መግለጫ,ካርተር የ1997 የኢትዮጵያ ምርጫን ለመታዘብ አዲስ አበባ ተገኝተው ነበር

ከ 9 ሰአት በፊት

“በቅርቡ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ግጭት አስመልክቶ በተናገርኩት ንግግር የተፈጠረው አለመግባባት እጅግ አስገርሞኛል” ይላል ጂሚ ካርተር ከ46 ዓመታት በፊት ለቀድሞው ፕሬዝደንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የላኩት ደብዳቤ።

ጥር 19/1978 ፕሬዝደንት ጂሚ ለሊቀ መንበር መንግሥቱ የላኩት ደብዳቤ አሜሪካ እና ኢትዮጵያ ግንኙነታቸው በሻከረበት ወቅት የተፃፈ ነው።

ደብዳቤው ‘ኦፊስ ኦፍ ዘ ሂስቶሪያን’ የተሰኘው የአሜሪካ መንግሥት ታሪክ የሚመዘግብበት ድረ ገፅ ላይ ይገኛል።

በዚህ ሳምንት በ100 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር ከአፍሪካ በተለይም ከአፍሪካ ቀንድ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ስኬታማ የሚባል አልነበረም።

“አሜሪካ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የግዛት አንድነታቸውን እንዲያስጠብቁ ድጋፍ ታደርጋለች። ሀገራት ግጭት ለመፍታት ሰላማዊ ያልሆነ አማራጭ መከተላቸውን እንወቅሳለን” ሲሉ ካርተር አቋማቸውን ይገልፃሉ።

ከጂሚ ካርተር በፊት የነበሩት ሁለቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች ኒክሰን እና ፎርድ “ትዊን ፒላር” የተሰኘ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ነበር የሚከተሉት።

ጂሚ ካርተር ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ማስፈናቸው ምናልባት አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋን ቀይራ ይሆናል የሚል ግምት አጭሮ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 1977 ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ቃለ መሐላ በፈፀሙ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የኢትዮጵያ መሪ ሆኑ።

ሚያዚያ 1977 ላይ አሜሪካ የቃኘው ጣቢያ መዘጋቱን እና በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል የተገባው ስምምነት ማብቃቱን አሳወቀች።

ከዚህ በኋላ ነው የመንግሥቱ ኃይላማርያም መንግሥት ሙሉ በሙሉ ፊቱን ወደ ሶቪየት ያዞረው፤ አሜሪካ ደግሞ ወደ ሶማሊያ በመዞር ወታደራዊ እርዳታ ማድረግ ጀመረች።

የግብፁ ፕሬዝደንት አንዋር ሳዳት እና የእስራኤሉ ጠ/ሚ ሜናኺም ቤጊን በጂሚ ካርተር አማካይነት የካማፕ ዴቪድ ስምምነት ሲፈርሙ
የምስሉ መግለጫ,የግብፁ ፕሬዝደንት አንዋር ሳዳት እና የእስራኤሉ ጠ/ሚ ሜናኺም ቤጊን በጂሚ ካርተር አማካይነት የካማፕ ዴቪድ ስምምነት ሲፈርሙ

ካርተር ለፕሬዝደንት መንግሥቱ የላኩት ደብዳቤ የሶማሊያ መሪ የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ሲያድ ባሬ ኢትዮጵያን በወረሩበት ወቅት የተፃፈ ነበር።

ጂሚ ካርተር በደብዳቤያቸው “እኛ ሶማሊያ ኦጋዴንን መውረሯን አንደግፍም። ለሶማሊያዎች የነገርናቸውም በኢትዮጵያ ምድር እስካሉ ድረስ ከእኛ ወታደራዊ ድጋፍ እንደማያገኙ ነው” ይላል።

በወቅቱ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል የነበረው ቁርሾ ከዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተሻገረ ነው።

አሜሪካ በኒክሰን ዘመነ መንግሥትም ሆነ በፎርድ አስተዳዳር ትከተለው የነበረው “ትዊን ፒላር” የተሰኘው ፖሊሲ “ትክክል አልነበረም” ብለው የሚከራከሩት ፖለቲካል ሳይንቲስቱ አዮዋኒስ ማንዚኮስ ናቸው።

ምሁሩ ‘አሜሪካን ዲፕሎማሲ’ በተሰኘው ድረ ገፅ ላይ አሜሪካ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ ላይ ታራምድ የነበረው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚል ጽሑፍ ለንባብ አብቅተዋል።

አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር የ25 ዓመታት የመከላከያ ስምምነት በአውሮፓውያኑ 1953 የገባቸው ምሥራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር በቀጣናው ቁልፍ ሚና አላት ብላ በማሰብ ነበር።

ኃይለሥላሴ በመጨረሻዎቹ የሥልጣን ዘመናቸው ከፕሬዝደንት ኒክሰን ጋር ያላቸው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ባይቋረጥም፣ እየሻከረ መጥቶ እንደነበር ይነገራል።

አሜሪካ ደርግን በተመለከተ የነበራት አስተሳሰብ የተዛባ ነበር የሚሉት ምሁሩ፤ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ፊታቸውን ወደ ሶቪየት ኅብረት ሲያዞሩ ነው ይህ እውን የሆነው ይላሉ።

ደብዳቤው ይቀጥላል።

“በኤርትራ አውራጃ ሰላም ሰፍኖ ማየት እንፈልጋለን። በሀገርዎ ሰላም ሰፍኖ ማየት እንፈልጋለን። በእርስዎ እና በኔ መንግሥት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት አሳስቦኛል። ከፍተኛ ልዑክ ልኬ ከእርስዎ አሊያም ከተወካይዎ ጋር እንዲወያይ እሻለሁ። ፈቃድዎ ከሆነ ልዑኩን መች እንደምልክ አሊያም እርስዎ መች እንደሚልኩ ይንገሩኝ።”

ጂሚ ካርተር እና ኔልሰን ማንዴላ
የምስሉ መግለጫ,ጂሚ ካርተር እና ኔልሰን ማንዴላ ዘ ኤልደርስ የተባለ ተቋም መሥርተዋል

አዮዋኒስ ማንቲዝኮስ፣ በአውሮፓውያኑ 2010 ‘የዩኤስኤ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ’ በሚል ስለ አሜሪካ ዲፕሎማሲ ባሳተሙት ጽሑፍ የካርተር መንግሥት በኦጋዴን ጦርነት ወቅት ባሳየው ወጥ ያልሆነ አቋም ምክንያት ከሪፐብሊካኖች ትችት ደርሶበታል ይላሉ።

በተለይ ደግሞ የካርተር መንግሥት ከሶማሊያ ጋር የገባው ስምምነት ብዙ ወቀሳ እንዳስነሳ ጸሐፊው ያወሳሉ።

ጂሚ ካርተር ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጥሰት ትፈጽማለች ማለታቸው ነው ከአዲስ አበባ ጋር ያለውን ግንኙነት ያሻከረው።

ካርተርን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚተቹ ሰዎች በሶማሊያም የሰብአዊ መብት ጥሰት መኖሩ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት የለዘበ እንዲሆን ገፋፍቷል ይላሉ።

ካርተር በደርግ ዘመነ መንግሥት ብቻ ሳይሆን በኢህአዴግ አገዛዝ ወቅትም ስማቸው ከኢትዮጵያ ጋር ይያያዛል።

በተለይ በ1997 ዓ. ም. የኢትዮጵያ ምርጫ “ከገዢው ፓርቲ በኩል ምንም እክል አላየሁም” ማለታቸው ብዙ ትችት አስተናግዶ ነበር።

ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ካርተር ማዕከል የተባለ ድርጅት አቋቁመው በሰብአዊ መብት፣ በጤና እና በምርጫ መታዘብ ሥራ ተሰማርተው ነበር።

ምንም እንኳን ካርተር ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ውጣ ውረድ የሞላው ቢሆንም፣ በተለይ ጊኒ ወርም የተሰኘውን በሽታ በመታገል ረገድ ድርጅታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ሥራዎች እንደሠሰራ ይታመናል።