ኢላን መስክ እና ዶናልድ ትራምፕ
የምስሉ መግለጫ,የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለሀብቱ መስክ የትራምፕ ቀኝ እጅ ነው

ከ 6 ሰአት በፊት

የዓለማችን ቱጃሩ ሰው ኢላን መስክ የማኅበራዊ ሚድያ ስሙን ቀየረ።

መስክ ገዝቶ ንብረቱ ባደረገው የቀድሞው ትዊተር የአሁኑ ኤክስ ማኅበራዊ ገፅ ስሙን ወደ “ኬኪየስ ማክሲመስ” መቀየሩን አስታውቋል።

ጉምቱው የቴክኖሎጂ ሰው መስክ የተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የቅርብ ሰው ነው።

ኢላን መስክ የማኅበራዊ ሚድያ ስሙን ለምን እንደቀየረ እስካሁን ማብራሪያ አልሰጠም።

መስክ ስሙን ብቻ ሳይሆን ‘ፕሮፋይል’ ፎቶውንም ቀይሯል።

ፎቶው ‘ፔፔ ዘ ፍሮግ’ የተባለ ገፀ-ባሕሪ ሲሆን በአብዛኛው በአክራሪ ቀኝ-ዘመም ፖለቲካ አቀንቃኞች ጥቅም ላይ የሚውል ነው።

ኢላን መስክ ስሙንና ፎቶውን መቀየሩን ተከትሎ የክሪፕቶከረንሲው ዓለም የተነቃነቀ ሲሆን ሚምኮይን የተባለው ዲጂታል መገበያያ ዋጋ ጣራ ነክቷል።

መስክ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ በሚሰጣቸው አስተያየቶች ምክንያት የክሪፕቶከረንሲ ዋጋ ከፍ ሲል ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ነገር ግን መስክ በሚምኮይን ዋጋ መጨመር ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ይኑረው አይኑረው ግልፅ አይደለም።

“ኬኪየስ” የሚለው ቃል “ኬክ” ከተሰኘው የላቲን ቃል የተመዘዘ ሲሆን በግርድፍ ትርጉሙ “ጮክ ብሎ መሳቅ” ነው። ይህ ቃል መጀመሪያ አካባቢ ኦንላይን ጌም በሚጫወቱ ሰዎች ዘንድ ይዘወተር ነበር። አሁን ከቀኝ-ዘመም ፖለቲካ አቀንቃኞች ጋር ተያይዟል።

“ኬክ” የሚለው ቃል የጥንታዊው የግብፅ የጨለማ አማላክትም ይውላል። አማላክቱ በእንቁራሪት ጭንቅላት ይመሰላሉ።

“ማክሲመስ” ደግሞ ግላዲየተር ከተባለው ፊልም የተወሰደ ይመስላል። በዚህ ፊልም ላይ ዋናው ገፀ-ባሕሪ ስሙ ማክሲመስ ዴሲሚየስ ሜሪዲየስ ነው።

የኤክስ፣ ቴስላ የኤሌትሪክ መኪና አምራች ኩባንያ እና የስፔስኤክስ የጠፈር ምርምር ተቋም ባለቤት ኢላን መስክ በዓለም ቁጥር አንድ ሀብታም ነው።

በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ የተወለደው መስክ ፔይፓል የተባለውን የገንዘብ መላላኪያ በአውሮፓውያኑ 2002 ለኢቤይ በ1.5 ቢሊዮን ዶላር መሸጡ ይታወሳል።

በጥቅምት 2022 ደግሞ ትዊተር በመባል ይጠራ የነበረውን ማኅበራዊ ሚድያ ገዝቶ ኤክስ ሲል ሰይሞታል።

ብሉምበርግ ጋዜጣ እንደሚለው የኢላን መስክ የተጣራ ሀብት 350 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል።