በአምስተርዳም አዲሱ ዓመት 2025 ሲከበር
የምስሉ መግለጫ,አምስተርዳም

ከ 8 ሰአት በፊት

አዲሱ የፈረንጆች ዓመት 2025 በመላው ዓለም በድምቀት ተከብሯል።

ኪሪባቲ የተባለችው ደሴት 2025ን በመቀበል ከዓለም ቀዳሚዋ ስትሆን ማክሰኞ ከሰዓት ነው አዲሱን ዓመት ያከበረችው። ቀጥሎ ኒው ዚላንድ እና የተወሰኑ የአውስትራሊያ ክፍሎች በዓሉን አክብረዋል።

አዲስ አበባ አዲሱን ዓመት 2025 በድምቀት ስትቀበል
የምስሉ መግለጫ,አዲስ አበባ አዲሱን ዓመት 2025 በድምቀት ተቀብላለች

ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሕንድ እና ስሪ ላንካ በሰዓት አቆጣጠራቸው ቅደም ተከትል ከሌሎች ሀገራት ቀደም ብለው በዓሉን ያከበሩ ሀገራት ናቸው።

አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ በዩናይትድ ስቴትስ እና ዩናይትድ ኪንግደም እንዲሁም በበርካታ የዓለማችን ከተሞች ‘ርችት’ ተተኩሷል።

ሶሪያዊያን ከአሳድ መገርሰስ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲሱን ዓመት አክብረዋል
የምስሉ መግለጫ,ሶሪያዊያን ከአሳድ መገርሰስ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲሱን ዓመት አክብረዋል

ከበርካታ አስርታት በኋላ ከበሽር ቤተሰብ አገዛዝ የተላቀቀችው ሶሪያ አዲሱን ዓመት በድምቀት አክብራለች። የኢራቋ መዲና ባግዳድም በመብራት ታጅባ አዲሱን ዓመት ተቀብላለች።

ግሪንላንድ አዲሱን ዓመት ሁለት ጊዜ ነው የምታከብረው። መጀመሪያ በዴንማርክ አቆጣጠር ሲሆን ቀጥሎ ደግሞ ከአራት ሰዓታት በኋላ በራሷ አቆጣጠር እኩለ ለሊት ላይ የአዲሱን ዓመት መባቻ አክብራለች።

25 ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ለሕዝባቸው ባሰሙት ንግግር በ2025 “ሁሉም ነገር መልካም ይሆናል” ብለዋል።

የኬንያዋ መዲና ናይሮቢ በደማቅ ‘ርችት’ አዲሱን ዓመት ተቀብላለች። ሌሎች የአፍሪካ ከተሞችም አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ በዋና ከተማዎቻቸው መብራት ደምቆ አምሽቷል።

የዓለማችን ረዥሙ ሕንፃ ቡርጀ ኻሊፋ
የምስሉ መግለጫ,የዓለማችን ረዥሙ ሕንፃ ቡርጀ ኻሊፋ በመብራት ደምቆ አምሽቷል

በርካታ የሀገራት መሪዎች 2025 መግባቱን አስመልክቶ ለሕዝቦቻቸው በቴሌቪዥን የተላለፈ ንግግር አሰምተዋል።

አዲስ አበባ፣ ደማስቆ፣ ሚንስክ፣ ሞስኮው እና ሪያድ በተመሳሳይ ሰዓት የፈረንጆቹን አዲስ ዓመት ካከበሩ ከተማዎች መካከል ናቸው።

ለንደን፣ ፓሪስ፣ ማድሪድ እና ሌሎች የአውሮፓ ከተሞች እንዲሁ በቀለማት ደምቀው አዲሱን ዓመት ተቀብለውታል።

የእንግሊዝ ንጉሣዊ ቤተሰብ ለመጀመሪያ ለሶስተኛ ጊዜ ያለንግሥት ኤልሳቤጥ አዲሱን ዓመት አክብሯል። ንጉሥ ቻርልስ በአዲሱ ዓመት ሳንድሪንግሀም ወደ ምትገኘው ቅድስት መቅደላዊት ቤተ-ክርስትያን አቅንተው ቅዳሴ ይታደማሉ።