January 1, 2025 – Konjit Sitotaw
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በቡግና እና ላስታ ወረዳዎች በግጭትና ድርቅ ሳቢያ ጉዳት የደረሰበት ሕዝብ ብዛት 77 ሺሕ መኾኑን አዲስ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።
ቢሮው፣ ጉዳት ከደረሰበት ሕዝብ ውስጥ 10 ሺሕ ያህሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንደኾኑ ገልጧል። ታጣቂዎች ባካባቢው በጣሉት የእንቅስቃሴ ገደብ ሳቢያ ሕዝቡ ለአገልግሎቶች ተደራሽ ሊኾን እንዳልቻለ፣ የባንክና ቴሌኮምንኬሽን አገልግሎቶች እንደተቋረጡና ላለፉት ሦስት ወራት የመንግሥት መዋቅር እንደሌለ የቢሮው ሪፖርት ጠቅሷል።
ዝቅተኛ የሰብል ምርት፣ ከፍተኛ የምግብ ዋጋና የሰብዓዊ ዕርዳታና ማኅበራዊ ድጋፎች አለመኖር የሰብዓዊ ቀውሱን አባብሰውታል ተብሏል።
ሪፖርቱ፣ በወረዳዎቹ አገልግሎት የሚሰጥ አምቡላንስ እንደሌለ፣ 77 በመቶው ሕዝብ የመጠጥ ውሃ እንደማያገኝና 70 በመቶ የሚኾኑ ሕጻናት በከፍተኛ የምግብ እጥረት እንደተጎዱም አመልክቷል።