አዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ በከተማዋ ከሚገኙ ከ20 ሺሕ በላይ የሚኾኑ ሕንጻዎች መካከል የአደጋ መከላከል መስፈርቶችን የሚያሟሉት 42ቱ ብቻ እንደኾኑ መናገሩን ሸገር ሬዲዮ ዘግቧል።
ሕጋዊ የሕንጻ መስርቶችን ባላሟሉ የተቋማትና የግለሰቦች ሕንጻዎች ላይ ሕጋዊ ርምጃ መውሰድ እጀምራለኹ በማለት ኮሚሽኑ ማስጠንቀቁን ዘገባው ጠቅሷል፡፡ የከተማዋ አስተዳደር፣ ከአራት ፎቅ በላይ ያላቸው ሕንጻዎች በሙሉ የአደጋ መከላከል መስፈርቶችን ማሟላት እንዳለባቸው የሚያስገድድ ደንብ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡
ኮሚሽኑ የአደጋ መከላከያ መስፈርቶች በማለት በደንቡ ከደነገጋቸው መካከል፣ የእሳት ማጥፊያ፣ አውቶማቲክ የእሳት አደጋ መከላከያ ማስገጠም፣ የአደጋ መከላከያ ምልክቶችን በግልጽ በሚታይ ቦታ ማስቀመጥ፣ አመቺ የአደጋ ጊዜ መውጫ መስራት እና ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ደሞ ባግባቡ የሠለጠኑ የአደጋ ጊዜ ባለሙያዎችን መቅጠር እንደሚገኙበት ከኮሚሽኑ መስማቱን ዘገባው አውስቷል።
ከአራት ፎቅ በላይ ሕንጻ ያላቸው ግለሰቦችና ተቋማት የደኅንነት መስፈርቶችን አሟልተው ማረጋገጫ እንዲወስዱ ኮሚሽኑ አሳስቧል ተብሏል።