
January 1, 2025

ዘውድነሽ ወልዴ (ሲስተር) የጽናት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሕክምና ኮሌጅ የካንሰር ታካሚዎች ድጋፍ ማኅበር መሥራችና ፕሬዚዳንት እንዲሁም የሕክምና ኮሌጁ የሕፃናት ሕክምና ክፍል ነርስ ናቸው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኢትዮጵያ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኩባ የተከታተሉት ዘውድነሽ (ሲስተር)፣ በኩባ ሳንታ ክላራ የነርስ ማሠልጠኛ ተቋም በመግባት በነርሰነት ሙያ ተመርቀዋል፡፡ በአገር ውስጥ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በነርሲንግ የመጀመርያ ዲግሪም አግኝተዋል፡፡ በማኅበሩ እንቅስቃሴና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ ኩባ ያቀኑበት ምክንያት ምንድነው?
ሲስተር ዘውድነሽ፡- ወደ ኩባ ያቀናሁት 1969 ዓ.ም. ነው፡፡ ወቅቱ የአድሃሪው የሶማሊያ ሞቃዲሾ መንግሥት መደበኛና ሠርጎ ገብ ወታደሮች በኢትዮጵያ ላይ ወረራቸውን ያጧጧፉበት ነበር፡፡ አባቴ የሦስተኛ (አንበሳው) ክፍለ ጦር አባል ነበር፡፡ ይህንኑ ሕገወጥና ወረራ በመከላከል ላይ እንዳለ ተሰዋ፡፡ በዚህም የተነሳ መንግሥት ታናሽ ወንድሜን ሕፃናት አምባ ሲያስገባው፣ እኔና ተከታይ እህቴን ደግሞ ወደ ኩባ ላክን፡፡ ኩባ እንደደረስንም ትምህርታችንን መከታተል ጀመርን፡፡
ሪፖርተር፡- በኩባ ቆይታዎ ከተከታተሉት የቀለም ትምህርት ሌላ ምን ልምድና ተሞክሮ ቀስመዋል?
ሲሲተር ዘውድነሽ፡- የሥራ ክቡርነትን፣ ምርታማነትን፣ አገር መውደድን፣ ጠንካራና በዲሲፒሊን የታነፀ ዜጋ መሆንን፣ ከራስ አልፎ ለተጎዱና ለተቸገሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አቅም በፈቀደ መጠን ድጋፍ ማድረግን፣ በሽታን ለመከላከል የግልና የአካባቢ ንጽሕና መጠበቅን፣ ሐኪሞች በብዛት ማፍራትን፣ ጤና ተቋማት ማስፋፋትና ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግን በኩባ ለማየትና ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ፅናት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሕክምና ኮሌጅ የካንሰር ታማሚዎች ድጋፍ ማኅበርን ለማቋቋም ያነሳሳዎት ምንድነው?
ሲስተር ዘውድነሽ፡- በአንድ ወቅት ገላዬን ስታጠብ በጡቴ ላይ አበጥ ያለ ነገር ተሰማኝ፡፡ እንደገና በሁለት እጆቼ ጠንከር አድርጌ ስነካካው መጠጠሩ ታወቀኝ፡፡ ወዲያውኑ በጣም ድንጋጤ ተሰማኝ፡፡ ትንሽ ከተረጋጋሁ በኋላ ተገቢውን ምርመራ አደረግሁ፡፡ ቀዶ ሕክምና፣ ኬሞና ጨረር እንድወስድ ከሐኪም ተነገረኝ፡፡ የተጠቀሰውን ሕክምና ለማድረግ መዘግየት እንደማያስፈልግ ተረዳሁ፡፡ ይህም ቢሆን የጨረሩን ሕክምና ለማግኘት አንድ ዓመት ወረፋ መጠበቅ እንዳለብኝ ተነገረኝ፡፡ ለኬሞ የታዘዘው መድኃኒት ደግሞ በወቅቱ በጣም ውድ ከመሆኑም በላይ በውጭ እንጂ በአገር ውስጥ አይገኝም ነበር፡፡ ከውጭ ለማስመጣት የኢኮኖማ አቅሜ አይፈቅድልኝም፡፡ በዚህም የተነሳ ችግር ውስጥ መግባቴን የተረዱ ከፍተኛ ሐኪሞችና አንዳንድ ወዳጆቼ መድኃኒቱን ገዝተው አቀረቡልኝ፡፡ መድኃኒቱን መጠቀም ጀመርኩ፡፡ በካንሰር የተጎዳውም አካሌ በቀዶ ሕክምና ተወገደ፡፡ ጨረሩን ግን ከአንድ ዓመት በኋላ መውሰዱ እንደማይጠቅመኝ ብረዳም ከመጠቀም አልቦዘንኩም፡፡ በኋላም ከበሽታው ተፈወስኩ፡፡
ሪፖርተር፡- ከራስዎ ተሞክሮ በመነሳት ተመሳሳይ የጤና እክል ላጋጠማቸው ሴቶች የሚያደርጉት ዕገዛ ምን ይመስላል?
ሲስተር ዘውድነሽ፡- እኔ በማገለግልበት ሕክምና ኮሌጅ ውስጥ የጡት ካንሰር ያደረባቸው ሴቶች ለሕክምናና ለምርመራ በሳምንት ሦስት ጊዜ ይመላለሳሉ፡፡ በዚህ ወቅት በሥነ ምግብ ባለሙያዎች፣ በካንሰር ሐኪሞች እንዲሁም በሥነ ልቦናና በአዕምሮ ሕክምና ባለሙያዎች ትምህርት ይሰጣቸዋል፡፡ አንድ ጊዜ እኔም ጣልቃ ገብቼ እንደ እነሱ የካንሰር ታማሚ እንደነበርኩ፣ ሕክምናውንም ተከታትዬ እንደዳንኩ ነገርኳቸው፡፡ የካንሰር በሽታ ምልክት እንደማያሳይ፣ በድንገትም እንደሚከሰት፣ ሰውነትን እንደሚያጠቁር፣ የምግብ ፍላጎትን እንደሚቀንስ፣ የጭንቅላት ፀጉርን እንደሚነቃቅል፣ በዓመት ሁለት ጊዜ የሕክምና ምርመራ አለማድረግ ደግሞ ለበሽታው መጠንከር ተጨማሪ መንስዔ መሆኑን በዝርዝር አስረዳኋቸው፡፡ እኔም ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ ችግሮች ደርሶብኝ አሁን ግን ሙሉ ለሙሉ ነፃ መሆኔን ገለጽኩላቸው፡፡ ካንሰር ይገድለናል እንዳይሉ፣ እንድናለን የሚል እምነትና አመለካከት እንዲኖራቸው መጣር እንዳለባቸው ነገርኳቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ልምድዎትን ካካፈሉ በኋላ ነው ማኅበሩ የተመሠረተው?
ሲስተር ዘውድነሽ፡- አዎ፡፡ ልምዴን ሳካፍል ተሰብሳቢው በሙሉ የመደሰትና አንዳንዱ ደግሞ የመደነቅ ባህሪ ይታይባቸው ጀመር፡፡ በኋላ ማኅበር እናቋቁም የሚል ሐሳብ ተነሳና ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አግኝቶ የአባልነት ምዝገባ ተጀመረ፡፡ በአሁኑ ጊዜም የጡት ካንሰር ያለባቸውና ታክመው የዳኑ ዘጠና ሴቶች በማኅበሩ በአባልነት ታቅፈዋል፡፡ ማኅበሩም ከተቋቋመ አንድ ዓመት ሆኖታል፡፡ የተመሠረተበትንም የመጀመርያውን ዓመት ታኅሳስ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. አክብረናል፡፡ ሕጋዊ ዕውቅና ለማግኘትም ጉዳዩ ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ተፅፎ መልሱን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡
ሪፖርተር፡- ከአባላት ጋር የምትወያዩበት መድረክ አለ?
ሲስተር ዘውድነሽ፡- ወር በገባ በመጀመርያው ዓርብ ስብሰባ እናካሂዳለን፡፡ በዚህም ስብሰባ ላይ የጡት ካንሰር ይዟቸው በልዩ ልዩ ምክንያት ወደ ጤና ተቋም የማይመጡትና ቤት ተደብቀው የቀሩት ለሕክምና የሚወጡበትን መንገድ እንቀይሳለን፡፡
ሪፖርተር፡- ሕክምና ኮሌጁ ለማኅበሩ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ እንዴት ያዩታል?
ሲስተር ዘውድነሽ፡- የመሰብሰቢያ አዳራሽ ይሰጠናል፡፡ በስብሰባችን የተላለፉትን ውሳኔዎች ተግባራዊና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ያመቻችልናል፡፡ ዕውቅና ለሚሰጠው አካል ደብዳቤ ይጻጻፍልናል፡፡ ጉዳይ ባጋጠመን ቁጥር ከጎናችን ይቆማል፡፡
ሪፖርተር፡- ለህሙማኑ ምን አይነት አገልግሎቶች ትሰጣላችሁ?
ሲስተር ዘውድነሽ፡- አንዲት ሴት ቀዶ ሕክምና ከተደረገላት በኋላ መድኃኒቱንና ጨረሩን ከወር በኋላ ማግኘት አለባት፡፡ ይህንን ማሳካት ደግሞ የኢኮኖሚ አቅምን የሚፈትን ነው፡፡ ወረፋ መጠበቅም ግድ ይላል፡፡ ራቅ ካለ ቦታ ወይም ከክፍለ አገር ለሚመጡ ታካሚዎች ምግብና ማደሪያ ሲቸግራቸው ይስተዋላሉ፡፡ በማኅበሩ የተዘረዘሩትን ችግሮች አቅም በፈቀደ መጠን ለመቅረፍና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡ አገልግሎት አሰጣጥና የመድኃኒት አቅርቦት ላይ ችግሮች ሲኖሩ ለመመካከርና መፍትሔ ለመሻትም እንሰራለን፡፡
