January 4, 2025 

በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ለ10 ሺህ ገደማ ሰዎች የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ስጋት እንደሆነ ተጠቆመ

(መሠረት ሚድያ)- ‘Gelology Hub’ በሚል የሚታወቀው እሳተ ገሞራዎችን እና የመሬት እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ትንታኔ የሚያቀርበው ድርጅት እንዳለው በአለም ዙርያ ትኩረት የተነፈገው ይህ አደገኛ ክስተት የእሳተ ገሞራ ፍንዳታን ሊያስከትል የመቻል እድሉ ከፍተኛ ነው።

በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች እና ጦርነቶች ይህ ተፈጥሮአዊ አደገኛ ክስተት ብዙ ትኩረት እንዳያገኝ አድርጎታል የሚለው Geology Hub ይህን መረጃ ለህዝብ ማድረስ የፈለገው የሰው ህይወት ለማትረፍ ነው ብሏል።

ከመስከረም ወር ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የቀለጠ አለት ክምችት እየታየ መሆኑን ገልጾ እስካሁን ከአደጋው አካባቢ 700 ገደማ ሰዎች እንዲነሱ መደረጉን ገልጿል።

በዚህ አደገኛ ስፍራ የሚገኙ 10 ሺህ ገደማ ሰዎች በአስቸኳይ ከስፍራው እንዲነሱ መደረግ እንዳለባቸው የሚገልፀው Gelology Hub ይህን ጉዳይ በዋሽንግተን ዲሲ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ለአሜሪካው የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ማሳወቁን ጨምሮ ጠቅሷል።

21 ኪ/ሜ ርዝመት ያለው ይህ የእሳተ ገሞራ ግፊት በመካከለኛ ኢትዮጵያ አዋሽ አካባቢ እንቅስቃሴው እንደቀጠለ የታወቀ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊት በአካባቢው ያልነበሩ አዳዲስ ሙቅ ውሀዎች መፍለቅ መጀመራቸውም ታውቋል።

በአዋሽ ፈንታሌ እስከ 5 ነጥብ 1 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ የተለያየ ደረጃ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ሠመራ ዩኒቨርሲቲ አስታውቆ ነበር።