በሬክተር ስኬል 5.5 የተመዘገበ እና በቅርብ ቀናት ከነበሩት ከፍተኛው የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ
(መሠረት ሚድያ)- ምሽት 2:01 ላይ የተከሰተው ይህ ርዕደ መሬት 5.5 ሆኖ በሬክተር ስኬል እንደተመዘገበ የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ አስታውቋል፣ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ንዝረቱ እንደተሰማቸው እየጠቆሙ ይገኛሉ።
ይህ በቅርብ ቀናት ውስጥ በአብዛኛው አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ከተከሰቱት ርዕደ መሬቶች በመጠኑ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል። ከርዕደ መሬቱም በተጨማሪ አነስተኛ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ በአፋር ክልል ዱለሳ ወረዳ ዛሬ መከሰቱ ታውቋል።
‘Gelology Hub’ በሚል የሚታወቀው እሳተ ገሞራዎችን እና የመሬት እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ትንታኔ የሚያቀርበው ድርጅት እንዳለው በአለም ዙርያ ትኩረት የተነፈገው ይህ አደገኛ ክስተት የእሳተ ገሞራ ፍንዳታን ሊያስከትል የመቻል እድሉ ከፍተኛ ነው።
ከመስከረም ወር ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የቀለጠ አለት ክምችት እየታየ መሆኑን ገልጾ እስካሁን ከአደጋው አካባቢ 700 ገደማ ሰዎች እንዲነሱ መደረጉን ገልጿል።
በዚህ አደገኛ ስፍራ የሚገኙ 10 ሺህ ገደማ ሰዎች በአስቸኳይ ከስፍራው እንዲነሱ መደረግ እንዳለባቸው የሚገልፀው Gelology Hub ይህን ጉዳይ በዋሽንግተን ዲሲ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ለአሜሪካው የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ማሳወቁን ጨምሮ ጠቅሷል።
የሰሞኑን ተደጋጋሚ ክስተት ተከትሎ በርካታ የጥንቃቄ መልእክቶች እየተላለፉ ይገኛሉ።