
ከ 9 ሰአት በፊት
የሀገራችን ሰው ‘ሸዋዚንገር’ እያለ የሚጠራው እውቁ ተዋናይ በጀርመኗ ሙኒክ ከተማ ለእንግልት የተዳረገው በእጅ ሰዓቱ ነው።
አርኖልድ ሽዋርዝኔገር እጁ ላይ ያሠረው ሰዓት 10 ሺህ ዩሮ የሚያወጣ ነው።
ነገር ግን ይህን ለአየር መንገዱ ሠራተኞች ባለማሳወቁ ምክንያት ለሁለት ሰዓታት ተንገላቷል።
የሆሊውዱ ተዋናይ እና የቀድሞው ፖለቲከኛ ምንም እንኳ በረራው ቢጓተትም በሁኔታው ቅር አልተሰኘም። እንደውም ከገቢዎች ጋር ፎቶ ሲነሳ ታይቷል።
የሸዋዚንገር ዕጣ ማናችንም ላይ ሊደርስ የሚችል ነው። ለጉዞ ስንዘጋጅ ሕጉን ብንዘነጋ አይፈረድብንም።
ነገር ግን ጉዟችን ሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ አየር መንገዶች የተለያዩ ሕግጋት እንዳሏቸው ልንዘነጋ አይገባም። ፀጥታ፣ ግብር፣ ጤና. . . ሌላም ሌላም።
አንዳንድ ጊዜ ሕግጋቱን አለማክበራችን በረራችን ሊያስተጓጉለው አሊያም ለሰዓታት በቁጥጥር ሥር እንድንውል ከፍ ካለም ልንታሰር እንችላለን።
ጉዞዎ ፈጣን እና መንገላታት የሌለው እንዲሆን ከፈለጉ እኒህን ስምንት ጉዳዮች ልብ ይበሏቸው።
1. የማይሠራ አሊያም የተበላሸ ዶኩመንት
አየር መንገዶች የሚጠይቁት መታወቂያ ካርድ እና ሌሎች ሰነዶች እንደሀገሩ እና አየር ማረፊያው ሊለያይ ይችላል። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ቦታዎች የጉዞ ሰነዱ መጠቀሚያ ጊዜው ያላበቃ እንዲሆን ያስገድዳሉ።
አልፎም የመጠቀሚያ ጊዜው ሊያበቃ የተቃረበ ዶኩመንት ችግር ሊያስትል ይችላል። ለምሳሌ ፓስፖርታችን ሊያበቃ 6 ወርና ከዚያ በታች ከቀረው በርካታ ሀገራት መግባት አይፈቅዱም።
ለዚህ ነው በተለይ ወደሌሎች ሀገራት ከመጓዛችን በፊት የሀገራቱን የፓስፖርትና ቪዛ መስፈርት ማጣራት ያለብን።
ታይላንድ፣ ኔፓል እና ቱርክን የመሳሰሉ ሀገራት የማብቂያ ጊዜው ስድስት ወር አሊያም ከዚያ በላይ የሆነ ፓስርፖት ይጠይቃሉ። በርካታ የአውሮፓ ሕብረት ሀገራት ደግሞ ሶስት ወር ይጠይቃሉ።
ፓስፖርትና ሌሎች የጉዞ ዶክመንታችን ላይ የሚታየው ፎቶና ፅሑፍ ደማቅ ቢሆን ይመረጣል።
ፈሳሽ ጠብ ያለበት አሊያም የተቀደደና የተበላሸ ዶክመንት ችግር ላይ ሊጥለን ይችላል። አንዳንድ ሀገራት ደግሞ የክትባት እና የምናርፍበትን ቦታ የሚያረጋግጥ ወረቀት ይጠይቃሉ።
2. ያልተፈቀዱ ቁሳቁሶች
በርካታ ተጓዦች ሕገ-ወጥ ቁሳቁሶችን እስካልያዙ ድረስ በነፃነት መዘዋወር እንደሚችሉ ያስባሉ። ይህ ስኅተት ነው።
እያንዳንዱ ሀገር የራሱ የሆነ መመሪያ አለው። አንዳንድ ሀገራት የሚከለክሏቸው ቁሳቀሶች ሊያስገርሟችሁ ይችላሉ።
ለምሳሌ ወደ ሕንድ ሲጓዙ ሕንድ በትክክል ያልተሳለችበት ካርታም ሆነ ፅሑፍ ይዞ መግባት ክልክል ነው። ጃፓን ደግሞ የሕዝቡን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ አሊያም ሞራል የሚነኩ ቁሳቁሶችን አትፈቅድም።
ወደ አውስትራሊያ የሚጓዙ ኢትዮጵያዊያን ሽሮና በርበሬ የመሳሰሉ የምግብ ዓይነቶችን ሲወስዱ የታሸገና ማሸጊያው ላይ መረጃ የሠፈረበት ቢሆን ይመከራል።
ዱባይ የበሰሉ እና ቤት ውስጥ የተዘጋጁ ምግቦችን እንዲሁም ሶስት ድርብ የሆነ ዓሳ ማጥመጃ መረብ እና የዝሆን ጥርስ ትከለክላለች።
ወደ አሜሪካ የማይገቡ ዕቃዎችን ለማወቅ ‘Transportation Security Administration’ የተባለውን ድረ-ገፅ መጎብኘት ጠቃሚ ነው።
የየሀገራቱን ድረ-ገፅ በየጊዜው መጎብኘት ጥቅሙ ያመዝናል። ሀገርዎ ሕጋዊ የሆኑ ቁሶች፣ የሚሄዱበት ሀገር የሚያስጠይቁ ሊሆኑ ይችላሉ።
የአየር ማረፊያ ሠራተኞች የመፈተሽና በቁጥጥር ሥር የማዋል አልፎም ቪዛ የመከልከል መብት አላቸው።
- በሕይወት ትርጉም ማግኘት ለአእምሮ ጤና የሚሰጠው ጥቅም9 መስከረም 2024
- የታዳጊዎች አደገኛ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው – ጥናት26 መስከረም 2024
- ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎችን የሚያበረታታው እና የሞት አጋር የሚያፈላልገው ድረ-ገፅ ተጋለጠ26 መስከረም 2024
3. ጥሬ ገንዘብ እና ውድ ዕቃ
‘ሸዋዚንገር’ በፊልሞቹ ግዙፎችን ሲገነድስ ተመልክተን ይሆናል። ነገር ግን ወደ አወሮፓ ለመግባት 2 ሰዓታት መግባት ግድ ሆኖበት ነበር።
አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ሲገቡ በተለይ የያዙት ገንዘብ ከ10 ሺህ ዶላር በላይ ከሆነ አሊያም ውድ የሚባሉ ቁሶች ከያዙ ማሳወቅ ይጠበቅብዎታል።
ጌጣጌጦች፣ ብዙ የፈሰሰባቸው አልባሳትና አንዳንድ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እዚህ ጎራ ውስጥ ይመደባሉ።
ደቡብ አፍሪካ እና ካናዳን በመሳሰሉ ሀገራት ከመጓዝዎ በፊት የያዙትን ውድ ዕቃም ሆነ ጥሬ ገንዘብ ማሳወቅ የሚችሉበት ‘ፎርም’ አለ።

4. የሚታዘዙ መድኃኒቶች
ናርኮቲክስ ኮንትሮል ቦርድ የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት በአውሮፓውያኑ 2022 ባወጣው ዘገባ አየር መንገዶች የማይፈቅዷቸውን መድኃኒቶች ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል። ነገር ግን ይህ ብቻ አይደለም።
ከአንድ ሀገር ወደሌላ መድኃኒት ይዘው የሚጓዙ ከሆነ የሚሄዱበትን ሀገር ሕግ ማወቅ አለብዎ። መድኃኒቱ ብቻ ሳይሆን በውስጡ ያሉ ንጥረ-ነገሮችም ላይፈቀዱ ይችላሉ።
ለምሳሌ በየፋርሚሲው የሚሸጠው ሱዳፌድ የተባለው መድኃኒት ውስጥ ያለው ሲውዶፌድሪን የተባለ ንጥረ ነገር ሜክሲኮ ውስጥ አይፈቀድም።
የሚሄዱበት ሀገር የሚወስዱትን መድኃኒት ይፈቅድ ይሆን የሚለውን ለማወቅ ኤምባሲዎን ቢጠይቁ ይመከራል።
በተለይ ደግሞ ሕይወት ማራዘሚያ የሚባሉ አሊያም ለሳያክትሪክ እና ሳይኮቴራፒ የሚሰጡ መድኃኒቶች ዓይን ውስጥ ይገባሉ።
5. ዕፅዋት፣ የቤት እና የዱር እንስሳት
የትኛውንም በሕይወት ያለ ነገር ይዞ ወደሌላ ሀገር መሄድ ቀላል ላይሆን ይችላል። ዕፅዋት፣ የቤት እና ሌሎች እንስሳት እዚህ ውስጥ ይመደባሉ። ዕፅዋት፣ ፍሬዎች እና አበባዎችን ወደአሜሪካ ይዞ መግባት ቀላል አይደለም።
የአሜሪካው የዓሳ እና ዱር እንስሳት ጥበቃ ቱሪስቶች ይዘው መምጣት የማይችሏቸውን እንስሳት ዝርዝር በድረ-ገፁ ይፋ ያደረገ ሲሆን ዝርዝሩ በጣም ሰፊ ነው።
አእዋፍ፣ ከእንስሳት የሚሠሩ አንዳንድ መድኃኒቶች፣ ከርከሮና ነብር፣ የባሕር ኤሊ (ሲ ተርትል) ሌሎች ከባሕርና የዱር እንስሳት የሚገኙ ግብዐቶች ተካተውበታል።
የቤትና እና የተላመዱ እንስሳትንም ይዞ መግባት መዘዙ ብዙ ነው። ለምሳሌ ፒት ቡል ቴሪየርስ የተባሉትን የውሻ ዝርያዎች ይዞ ጃማይካ መግባት አይቻልም።
በርካታ የቤት እንስሳት በካርጎ ተጭነው የሚሄዱ ሲሆን መከተባቸው ተረጋግጦ እንዲሁም ለተወሰነ ጊዜ ተገልለው ተቀምጠው ነው የሚገቡት።
6. ተቀጣጣይ እና ፈንጂ
በርካታ አየር መንገዶች ትምባሆ፣ መለኮሻ ላይተር እና ቬፕ ፔን የተባሉ ኤሌክትሮኒክ ሲጋራዎችን አይፈቅዱም።
የሚያቃጥሉ እና ሊፈደነዱ የሚችሉ ቁሳቁሶችን ይዞ መጓጓዝ ሊያስቀጣ ይችላል። አነስተኛ ቢሆኑ እንኳ ‘ርችቶች’ ይዞ አውሮፕላን መሳፈር አይፈቀድም።
ይህ የሚሆነው በፍትጊያ ተቀጣጥለው በረራውን አደጋ ላይ ሊጥሉት ስለሚችሉ ነው። በአሜሪካ ይህን ሕግ የጣሱ ሰዎች እስከ 75 ሺህ ዶላር ሊቀጡ ይችላሉ።
እኒህን ተቀጣጣይ እና ፈንጂ ዕቃዎችን ለሽያጭ ማምጣት ደግሞ በወንጀል ሊያስጠይቅ ይችላል።
ለልደትም ይሁን የሚጓዙት አዲስ ዓመት ለማክበር በፍፁም የሚቀጣጠሉ ቁሶችን ይዘው አይጓዙ።

7. ጠጥቶ መብረር
ከበረራዎ በፊት አንድ ሁለት ማለት አሰኝቶዎታል። ሁለት ጊዜ ያስቡበት። የበረራ አስተናጋጆችም ሆኑ ሌሎች የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ጠጥተው ከሆነ ለሌሎች አደጋ ነዎት በማለት ሊከለክልዎት ይችላሉ።
የአሜሪካው ፌዴራል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጠጥቶ መብረር የፌዴራል ሕግ መጣስ ነው ይላል።
ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በርካቶች በረራ ላይ ሳሉ ደግሞ የበረራ አስተናጋጆች ከሚሰጥዎት የአልኮል መጠጥ ውጭ መጠቀም ይከለክላሉ።
የአሜሪካው አቪዬሽን ባለሥልጣን ማንናውም መንገደኛ ያልተገባ ባሕሪ ማሳየት እንደሌለበት ያስጠነቅቃል።
በበረራ ወቅት ያልተገባ ባሕሪ ያሳዩ መንገደኞች ሊቀጡ፣ ድጋሚ እንዳይበሩ ሊደረጉ አሊያም ለፖሊስ ተላልፈው ሊሰጡ ይችላሉ።
አንዳንድ ሀገራት አልኮል መጠጥ ፈፅሞ አይፈቅዱም። ጠጥቶ አሊያም የአልኮም መጠጥ ይዞ መገኘት የሚያስቀጣባቸው ሀገራት አሉ።
8. ያልተወራረደ ሒሳብ
ምንም እንኳ ይህ ሕግ ከሥፍራ ሥፍራ የተለያየ ሊሆን ቢችልም ያልተቋጨ የሕግ ሒሳብ ያለባቸው ሰዎች ችግር ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ።
የበርካታ ሀገራት አየር መንገዶች የመንገደኞችን የወንጀል ታሪክ አሊያም ያልተወራረደ መግዘብ የያዘ የመረጃ ቋት አላቸው።
ለምሳሌ ወደ ኒው ዚላንድ ሲገቡ ያልከፈሉት ቅጣት ካለብዎ አሊያም ሳይከፍሉ ሊወጡ ከሞከሩ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ሊያውልዎት ይችላል።
አውሮፕላን ከመሳፈርዎ በፊት ሕጉን ማክበርዎን ያረጋግጡ። የወንጀል ታሪክ ካለብዎ ወይም ያለብዎትን ሒሳብ ካልከፈሉ የሕግ አዋቂዎችን ያማክሩ።
ቅጣትዎን ይክፈሉ። የከፈሉበትን ደረሰኝ ይያዙ።
በረራ ከማድረግዎ በፊት የአየር መንገዶችን እና የሀገራትን ሕግጋት ያንብቡ። የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በርካታ አየር መንገዶች ፖሊሲያቸውን በግልፅ ድረ-ገፃቸው ላይ አስቀምጠዋል።