ሕዝብ

ከ 9 ሰአት በፊት

በተባበሩት መንግሥታት ግምት መሠረት ሕንድ ከቻይናን በመብለጥ በሕዝብ ብዛት በዓለም አንደኛ ሆናለች።

ሕንድ ወደ 1.45 ቢሊዮን ዜጎች አሏት። የሕዝብ ቁጥርን ከዚህ በላይ ላለመጨመር በሕንድ የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ይቀንሳል ብለው ሊያስቡ ይችላሉ።

እውነታው ግን ይህ አይደለም።

የአንድራ ፕራዴሽ እና ታሚል ናዱ ግዛቶች መሪዎች ልጆች በብዛት እንዲወለዱ ይጠይቃሉ።

በአንድራ ፕራዴሽ የወሊድ መጠን ቀንሷል፣ የአዛውንቶች ቁጥር ደግሞ ጨምሯል በሚል አስተዳዳሪዎች ብዙ ልጆች እንዲወለዱ ማበረታቻ ይሰጣሉ።

በታሚል ናዱ መውለድ የሚቻለው ሁለት ልጆች ብቻ ነው የሚለው ሕግ ተቀልብሷል። በቴላናግና ግዛትም ተመሳሳይ ሕግ ተሰርዟል።

እአአ በ1950ዎቹ ከነበረው አንጻር በሕንድ የወሊድ መጠን ከ5.7 ወደ 2 ቀንሷል።

ከ29 የሕንድ ግዛቶች በ17ቱ የወሊድ መጠን በአንድ ሴት ሁለት ልጆች ሆኗል።

ይህም ዘላቂነት ያለው የሕዝብ ቁጥር እንዲኖር ከሚያስፈልገው የወሊድ መጠን (replacement level) ያነሰ ነው።

አምስት የሕንድ ደቡባዊ ግዛቶች ዘላቂነት ያለው የሕዝብ ቁጥር እንዲኖር የሚያስፈልገውን የወሊድ መጠን አስመዝግበዋል።

እዚህ ነጥብ ላይ ካርላ ግዛት የደረሰችው በ1988 ሲሆን ታሚል ናዱ ግዛት ደግሞ በ1993 ደርሷል።

የተቀረው ሕንድ እዚህ ነጥብ ላይ የደረሰው በ2000 አጋማሽ ነው።

አምስት የደቡባዊ ሕንድ ግዛቶች አሁን ያላቸው የወሊድ መጠን ከ1.6 በታች ነው።

በካርናታካ ግዛት 1.6 እና በታሚል ናዱ 1.4 የወሊድ መጠን ተመዝግቧል።

ከአብዛኞቹ የአውሮፓ አገራት አንጻር ያነሰ ቁጥር ነው።

እነዚህ ግዛቶች በምርጫ ወቅት ድምጽ ሲሰጥና በምክር ቤት በሚሰጠው የመቀመጫ ቁጥር ልዩነት የሚያመጡ ናቸው።

በዓለም አቀፍ የሥነ ሕዝብ ሳይንስ ተቋም ውስጥ የሚሠራው ስሪኒቫስ ጎሊ “የሕዝብ ቁጥርን የሚቀንስ ፖሊሲ ካወጡ እንደሚቀጡ ያምናሉ። ይህ ፖሊሲ የተሻለ ምጣኔ ሃብት የሚያመጣና የፌደራል መንግሥትን ገቢ የሚጨምር ቢሆንም እንኳን እንደሚቀጡ ነው የሚያስቡት” ይላል።

ሕንድ እአአ በ2026 በምትዘረጋው አዲስ አሠራር መሠረት፣ የምርጫ ክልሎች ከሕዝብ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ ስለሚሆኑ በምክር ቤት የሚገኘው መቀመጫ ቁጥርም በዛ መንገድ ይወሰናል።

ለደቡባዊ ግዛት የምክር ቤት መቀመጫ ውስን መሆን ስጋት ነው።

የፌደራል በጀት የሚመደበውም በሕዝብ ቁጥር አማካይነት ነው። ይህ የበጀት እጥረት የሚፈጥርና ፖሊሲ የማውጣት ነጻነትን የሚገድብ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል።

ልጆች

የሥነ ሕዝብ ባለሙያዎቹ ኬኤስ ጄምስ እና ሹብራ ኪሪቲ እንደሚሉት፣ እንደ ኡታር ፕራዴሽ እና ቢሐር ያሉ የሕንድ ግዛቶች ተጨማሪ የምክር ቤት መቀመጫ ሲያገኙ እንደ ታሚል ናዱ፣ ካርላ እና አንድራ ፕራዴሽ ያሉ ግዛቶች ግን የምክር ቤት መቀመጫ ቁጥራቸው ሊቀንስ ይችላል።

ይህም የፖለቲካ ውክልና ለውጥ ያመጣል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ንሬንድራ ሞዲን ጨምሮ ሌሎችም የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዳሉት፣ የበጀት ክፍፍልና የምክር ቤት መቀመጫ ድልድል በአፋጣኝ የሚለወጥ አይሆንም።

ስሪኒቫስ ጎሊ እንደሚለው፣ ግዛቶች የሕዝብ ቁጥር ሊያስጨንቃቸው አይገባም።

“በገንቢ ውይይትና ከፌደራል መንግሥት ጋር በሚደረግ ድርድር ለውጥ ማምጣት ይቻላል” ይላል የሥነ ሕዝብ ባለሙያው።

ባለሙያዎች ስጋት የሆነባቸው የሕንድ የወሊድ መጠን ሲቀንስ የአዛውንቶች ቁጥር መጨመሩ ነው።

ፈረንሳይ የሕዝብ ቁጥሯን በእጥፍ ለማሳደግ 120 ዓመት ሲወስድባት ስዊድን ደግሞ 80 ዓመት ወስዶባታል።

ሕንድ ይህንን ለማሳካት 28 ዓመታት ነው የወሰደባት።

የአዛውንቶች ቁጥር መጨመር ከወሊድ ምጣኔ መቀነስ ጋር ይተሳሰራል።

የተሻለ ኑሮ፣ ትምህርት እና የከተማ መስፋፋት የወሊድ ምጣኔን ሲቀንስ የልጆች በሕይወት የመቆየት ዕድልን ይጨምራል።

አዛውንቶች

በሕንድ የምጣኔ ሃብት ዕድገትና ማኅበራዊ ለውጥ የወሊድ መጠን እንዲቀንስ ምክንያት ሆነዋል።

የቤተሰብ ምጣኔን የሚያበረታታ ፖሊሲም ለውጥ እንዲመጣ አስችሏል።

አንድራ ፕራዴሽ ግዛት ከስዊድን ጋር ሲነጻጸር የወሊድ መጠን 1.5 ሲሆን ጠቅላላ ገቢው ግን በ28 በመቶ ያንሳል።

ካለው ከፍተኛ ዕዳና የግብዓት ውስንነት አንጻር ግዛቶች ጡረታን የመሸፈን አቅማቸው ምን ያህል ነው? የሚለው ጥያቄም ይነሳል።

ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑ ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆነ ሕንዳውያን በድህነት ውስጥ ይኖራሉ።

በሃብት ክፍፍል ውስጥ ዝቅተኛው 20% ውስጥ ይመደባሉ ሲል የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።

በዓለም አቀፍ የሥነ ሕዝብ ሳይንስ ተቋም ውስጥ የሚሠራው ስሪኒቫስ ጎሊ እንደሚለው፣ ሕንድ ሃብታም ከመሆኗ በፊት የአዛውንቶች አገር እየሆነች ነው።

የልጆች ቁጥር ውስን መሆኑ እርዳታ የሚሹ አዛውንቶችን ቁጥር ጨምሯል። ለአዛውንቶች እንክብካቤ የሚሰጡ ሰዎችም ቁጥር ቀንሷል።

የሕንድ የጤና ሥርዓትና የአዛውንቶች ማቆያዎች በአገሪቱ እየታየ ላለው ለውጥ ዝግጁ አይደሉም ተብሏል።

“በአብዛኛው ሠራተኛ የሆነና አነስተኛ የወሊድ መጠን ያለው ዜጋ ይበራከታል። ይሄ ማኅበራዊ፣ ፓለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ ጫና ያስከትላል” ይላል ባለሙያው።

የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል ከወራት በፊት አገራቸው ከፍተኛ የወሊድ መጠን መቀነስ እንደገጠማት ገልጸው ነበር።

ለጉዳዩ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ለማቋቋምም አስበዋል።

የግሪክ የወሊድ መጠን 1.3 ሲደርስ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪሪያኮስ ሚሶታኪስ “አደገኛ የሕዝብ ቁጥር መቀነስ” ገጥሞናል ማለታቸው ይታወሳል።

ሆኖም ግን ዜጎች ብዙ ልጆች እንዲወልዱ ማሳሳብ ውጤት እንደማይኖረው የሥነ ሕዝብ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

“ሴቶች እንደ ወንዶች ይሠራሉ። ይህ ማኅበራዊ ለውጥ የማይቀለበስ ስለሆነ የመንግሥታት ማሳሰቢያ የወሊድ ምጣኔ ላይ ለውጥ አያመጣም” ይላል ባለሙያው።

በሕንድ የሕዝብ ቁጥር ውስንነት የገጠማቸው ግዛቶች ክፍተቱን ማን ይሞላል ብለው ይጨነቃሉ።

ያደጉ አገራት ክፍተቱን የሚሞሉት ጤናማ ወጣት ዜጋን በማፍራት ነው።

የሥራ ዘመንን በመጨመርም ለውጥ ለማምጣት ይሞክራሉ።

ሕንድ ጡረታ መውጫ ዕድሜን መጨመር እንዳለባት ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የተሻለ የምጣኔ ሃብት ክፍፍል መኖርም አለበት።

ስሪኒቫስ ጎሊ እንደሚለው፣ በሕንድ እስከ 2047 ድረስ ለወጣቶች የሥራ ዕድልን ማስፋትና ለአዛውንቶች ገንዘብ መመደብ ያስፈልጋል።

“አሁን ከአጠቃላይ ገቢው ከ15-20% ብቻ ነው እየሰበሰብን ያለው። ይሄ መሻሻል ይችላል” ሲል ያስረዳል።