
ከ 9 ሰአት በፊት
በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የጥገና ባለሙያ ሆኖ የሚሰራ በፊዚክስ ሁለተኛ ዲግሪ ያለው፣ የጽዳት ሠራተኛዋ የአካባቢ ጥበቃ ምሩቅ፣ ዴሊቨሪ የሚሰራው ደግሞ ፍልስፍና ያጠና፣ ለረዳት የፖሊስ ባልደረባነት የሚያመለክተው ደግሞ ከሥመ ጥር ዩኒቨርስቲ የዶክተሬት ዲግሪውን የያዘ ሆኖ የምታገኙት በቻይና ብቻ ነው።
እነዚህ ለማሳያነት ተጠቀሱ እንጂ እየታገለ ባለ ኢኮኖሚ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ታሪኮች ስፍር ቁጥር የላቸውም።
በቅርቡ በፋይናንስ ሁለተኛ ዲግሪውን የያዘው የ25 ዓመት ወጣት ሱን ዛን፣ በደቡባዊ ናንጂንግ ከተማ በአንድ ሬስቶራንት ውስጥ የአስተናጋጅነት ፈረቃውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ እያለ “የእኔ ሕልም በኢንቨስትመንት ባንክ ውስጥ መስራት ነበር” ይላል።
ከፍተኛ ክፍያ በሚከፈልበት ቦታ “ገንዘብ ለማፈስ” ተስፋ ሰንቆ የነበረ ቢሆንም፣ “እንደዚያ ያለ ሥራ ብፈልግም በነበር ቀረ” በማለት ይናገራል።
ቻይና በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን ታመርታለች። ነገር ግን በአንዳንድ መስኮች ለእነሱ የሚሆን በቂ ሥራ የለም።
በቻይና ዋና ዋና በሚባሉት የምጣኔ ኃብት መስኮች ሪል እስቴት እና ማኑፋክቸሪንግን ጨምሮ ተቀዛቅዘዋል አልያም ቆመዋል።
የወጣቶች ሥራ አጥነት በ20 በመቶ ከፍ ብሏል።
በተመረቁበት መስክ ሥራ ለማግኘት የተቸገሩ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን አሁን ከብቃታቸው በታች የሆነ ሥራ እየሠሩ ሲሆን ይህም ከቤተሰብና ከጓደኞቻቸው ነቀፌታ እያደረሰባቸው ነው።
- ራሳቸውን እያጠፉ ያሉት የኬንያ ሰልጣኝ ዶክተሮች3 ጥር 2025
- ፓናማ የፓናማ ካናልን እንዴት ከአሜሪካ አስመለሰች?1 ጥር 2025
- አዲስ አበባ ከአፍሪካ ለኑሮ እጅግ ውድ ከተሞች መካከል ስንተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች?16 ታህሳስ 2024
ሱን ዛን በአስተናጋጅ ተቀጥሮ መሥራት ሲጀምር ወላጆቹ ተበሳጩ።
“የቤተሰቤ አስተያየት ለእኔ በጣም ያሳስበኛል፤ ጥሩ ትምህርት ቤት ነው ያስተማሩኝ፤ በርካታ ዓመታትንም በትምህርት ላይ አሳልፌያለሁ” ሲል ተናግሯል።
ቤተሰቦቹ በስራ ምርጫው ስለሚያፍሩ የመንግሥት ሰራተኛ ወይም ባለስልጣን ለመሆን ቢሞክር እንደሚመርጡ ተናግሯል፤ ነገር ግን “ይህ የኔ ምርጫ ነው” ይላል።
ሱን በልቡ ሌላ ሀሳብ አለው። በአስተናጋጅነት እየሰራ የሬስቶራንቱን ሥራ ለመማር እና በመጨረሻም የራሱን ለመክፈት ያስባል።
የሚያስበው ተሳክቶ የልቡ መሻት ሞልቶ ውጤታማ ንግድ ላይ ከተሰማራ የቤተሰቡ ትችት ቅኝቱ ይቀየራል ብሎ ያስባል።
የሆንግ ኮንግ ከተማ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ዣንግ ጁን “በሜይንላንድ ቻይና ውስጥ ያለው የሥራ ሁኔታ በእውነቱ በጣም ፈታኝ ነው፤ ስለሆነም ብዙ ወጣቶች የሚጠብቁትን ነገር በትክክል ማስተካከል አለባቸው ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ይመክራሉ።
ብዙ ተማሪዎች የተሻለ ለማግኘት ተስፋ ሰንቀው የመጀመርያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይሰራሉ፤ እውነታው ግን ከዚያ የተገላቢጦሽ ሆኖ ያገኙታል ይላሉ።
በስፖርት ምክንያት ለሚደርሱ ጉዳቶች የማሳጅ አገልግሎት የሚሰጥ ክሊኒክ ውስጥ በልምምድ ላይ ያለችው የ29 ዓመቷ ዉ ዳን “የሥራ ገበያው በጣም ከባድ ነው” ትላለች።
“የማስተርስ ዲግሪ ስማር የነበሩኝ በርካታ የክፍል ጓደኞች ለመጀመርያ ጊዜ ሥራ ፍለጋ ቢወጡም የተሳካላቸው ግን ጥቂት ናቸው”
እሷም ብትሆን ከሆንግ ኮንግ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በፋይናንስ ዲግሪ አግኝታ መጨረሻዋ እንዲህ ይሆናል ብላ አላሰበችም።
ከዚህ በፊት ትኩረቱን በግብርና ምርቶች ላይ ባደረገ የንግድ ድርጅት ውስጥ ትሰራ ነበር።
በሆንግ ኮንግ ትምህርቷን እንደጨረሰች ወደ ሜይን ላንድ ቻይና ስትመለስ በግል ድርጅት ውስጥ ለመሥራት ያመለከተች ቢሆንም ያቀረቡላት ደሞዝ የትምህርት ዝግጅቷን የሚመጥን አልነበረም።
ሁሉንም እርግፍ አድርጋ በምትኩ በስፖርት ሕክምና ስልጠና መውሰድ ብትጀምርም ይህ ውሳኔዋ በቤተሰቧ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም።
“ከዚህ በፊት ጥሩ ሥራ እንደነበረኝ፣ ያለኝ የትምህርት ደረጃ ጥሩ ስራ ሊያስቀጥረኝ እንደሚችል ነው የሚያስቡት፤ ለምን አነስተኛ ክህሎት በሚጠይቅ እና ጥቂት ገንዘብ በሚገኝበት የጉልበት ሥራ መስራት ለምን እንደመረጥኩ አልገባቸውም።”
አሁን በምታገው የፍቅር አጋሯ ቤት ባይኖረው ኖሮ መኖር እንደማትችል ትናገራለች።
መጀመሪያ ላይ አሁን ያለችበትን የሙያ ጎዳና የሚደግፍ ሰው አላገኘችም ነበር። ነገር ግን እናቷ በቅርብ ጊዜ ያጋጠማቸው ከባድ የጀርባ ሕመምን ካከመቻቸው እና ከተሻላቸው በኋላ ለውጥ አይታለች።
በአንድ ወቅት የፋይናንስ ተማሪ የነበረችው እና አሁን የማሳጅ ባለሙያዋ በኢንቨስትመንት ዓለም ውስጥ መስራት እንደማይመጥናት ትናገራለች።
አሁንም በስፖርት ምክንያት የሚመጡ ጉዳቶች ላይ መስራት የበለጠ ይማርካታል። ሥራውንም እንደወደደች እና አንድ ቀን የራሷን ክሊኒክ መክፈት እንደምትፈልግ ትናገራለች።

ቻይናውያን ተመራቂዎች “ጥሩ ቦታ” ተብሎ ሊታሰብ በሚችለው ነገር ላይ ያላቸውን አመለካከት ለመለወጥ እየተገደዱ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ዣንግ።
ለወጣቶች “የማስጠንቀቂያ ምልክት” ተብሎ ሊታሰብ በሚችል ደረጃ “ብዙ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ጨምሮ በቻይና ያሉ ብዙ ድርጅቶች በርካታ ሠራተኞቻቸውን አሰናብተዋል” ሲሉ ያክላሉ።
በአንድ ወቅት አዳዲስ ተመራቂዎችን በብዛት ይቀጥሩ የነበሩ፣ ዛሬ ለእነዚህ ተመራቂዎች ከደረጃ በታች የሆኑ ሥራዎችን እያቀረቡ ሲሆን አብሮም በእነዚህ መስኮች የነበሩ ጥሩ ዕድሎች እየጠፉ መሆናቸውን ፕሮፌሰሯ ይናገራሉ።
ወደፊት ምን መሥራት እንደሚችሉ በቅጡ እስኪለዩ ድረስ፣ ስራ አጥ ተመራቂዎች ወደ ፊልም እና የቴሌቪዥን ኢንዱስትሪ ፊታቸውን መልሰዋል።
በትላልቅ በጀት የሚሰሩ ፊልሞች ትዕይንቶቻቸውን ለመሙላት ብዙ አጃቢ ተዋንያን ያስፈልጓቸዋል።
በቻይና ዝነኛ የፊልም ፕሮዳክሽን ከተማ ሄንግዲያን የትወና ሥራ ለማግኘት ደጅ የሚጠኑ በርካታ ወጣቶች አሉ።
የኤሌክትሮኒክስ ኢንፎርሜሽን ኢንጂነሪንግ የተማረው ዉ ዢንጋይ በሚሳተፍበት ፊልም ውስጥ የሚያወጣው ቃል እንኳ ባይኖር ከመሪ ገጸባህሪው ጎን እንደ ጠባቂው ሆኖ በመተወኑ ብቻ ደስተኛ ነው።
የ26 ዓመቱ ወጣት የትምህርት ደረጃው ሳይሆን መልከ መልካምነቱ አጃቢ ተዋናይ ሆኖ እንዲቀጠር ስለረዳው ይስቃል።
ብዙ ጊዜ ሰዎች ወደ ሄንግዲያን በመምጣት ለጥቂት ወራት ብቻ ይሰራሉ ይላል። ቋሚ ነገር እስኪገኝ ድረስ ይህ ለእሱ ጊዜያዊ መዳረሻው ነው። “ብዙ ገንዘብ አላገኘሁም ነገር ግን ዘና እንድል አድርጎኛል እና ነፃ ነኝ።”

በፊልም አዘጋጅነት እና ጸሀፊነት የተመረቀው እና በአጃቢ ተዋናይነት ለመሳተፍ ሥራ እየፈለገ የሚገኘው ሙሉ ስሙን መናገር ያልፈለገው ሊ “በቻይና ያለው ሁኔታ ይህ ነው አይደል? በተመረቅክበት ቅጽበት ሥራ አጥ ትሆናለህ” ብሏል።
” ገና አፍላ እያለሁ ሥራ ለመጀመር ስለመፈለግ ነው ወደዚህ የመጣሁት። ትልቅ ስሆን የተሻለ ሥራ ይኖረኛል።”
ነገር ግን በርካታ ሰዎች ጥሩ ስራ አላገኝም ሲሉ ይፈራሉ፤ እናም ከሀሳባቸው በተቃራኒ ለመዋል ይገደዳሉ።
የቻይና ኢኮኖሚ አቅጣጫ ላይ እምነት ያጡ ወጣቶች ብዙ ጊዜ የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ምን እንደሚሆን አያውቁም።
ዉ ዳን ተቀጥረው ያሉ ጓደኞቿ እንኳን የወደፊቱን ሲያስቡት ከተስፋ ፈንጠዝያ ይልቅ ስጋት ውስጣቸውን ይንጠዋል።
“በጣም ግራ ተጋብተዋል እና መጻዒው ጊዜ ግልጽ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። በሥራ ላይ ያሉት ደስተኛ አይደሉም። ያላቸውን ሥራ ይዘው ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩ እርግጠኛ አይደሉም። ይህንን ሥራቸውን ካጡ ደግሞ መውደቅያቸው ወዴት እንደሚሆን አያውቁም። ምን መሥራት ይችላሉ?”
አክላም “ጊዜው የሚያመጣውን ተቀብዬ ቀስ በቀስ ምን መስራት እንደምችል እፈልጋለሁ” ትላለች።