ባይደን

ከ 8 ሰአት በፊት

አሜሪካ ለእስራኤል የስምንት ቢሊዮን ዶላር የመሣሪያ ሽያጭ ልታደርግ መሆኑ ተገለጸ።

የሽያጭ ዕቅዱ በኮንግረስ መቅረቡን አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የመሣሪያ ሽያጩ ውስጥ ሚሳዔሎችን ጨምሮ ሌሎችም መሣሪያዎች የተካተቱ ሲሆን ከሁለቱም ምክር ቤቶች ይሁንታ ማግኘት አለበት።

ውሳኔው የተላለፈው ጆ ባይደን ሥልጣን ሊያስረክቡ በተቃረቡበት ወቅት ነው።

በጋዛ ጦርነት የተገደሉ ንጹኃን ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ አሜሪካ ለእስራኤል ወታደራዊ ድጋፍ መስጠት እንድታቆም ቢጠየቅም ፈቃደኛ አልሆነችም።

ያለፈው ነሐሴ አሜሪካ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የተዋጊ ጀቶችና ሌሎችም መሣሪያዎች ሽያጭን ፈቅዳለች።

የአሜሪካው ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደገለጹት የአየር ሚሳዔል፣ ቦምብ፣ የአየር መቃወሚያና ሌሎችም መሣሪያዎች ለእስራኤል ይሸጣሉ።

ሌላ ለሽያጩ ቅርብ የሆኑ ምንጭ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ “እስራኤል ራሷንና ዜጎቿን ዓለም አቀፍ ሕግንና ሰብአዊ ሕግን ተከትላ የመከላከል እንዲሁም የኢራንና አጋሮቿን ጥቃት የመመከት መብት እንዳላት ፕሬዝዳንቱ በግልጽ ተናግረዋል።”

“ለእስራኤል መከላከያ ድጋፍ መስጠት እንቀጥላለን” ሲሉም አክለዋል።

ባይደን አሜሪካ ለእስራኤል የምታደርገው ድጋፍ የማይናወጥ ነው ብለዋል።

በጦር መሣሪያ ዋነኛ የእስራኤል ደጋፊ አሜሪካ ስትሆን፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ መከላከያ እንድትገነባ አስችላታለች።

ስቶክሆልም ኢንተርናሽናል ፒስ ሪሰርች ኢንስቲትዩት እንዳለው፣ አሜሪካ ለእስራኤል ከ2019 እስከ 2023 ከተላከ መሣሪያ መካከል 69 በመቶውን ትሸፍናለች።

በ2024 አሜሪካ ለእስራኤል ከምትልከው መሣሪያ መካከል የተወሰኑ ቦምቦችን ለማስቆም ወስና ነበር። ይህም እስራኤል በጋዛና ራፋህ የእግረኛ ጦር ልታሰማራ ማሰቧን ተከትሎ ነው።

ባይደን ይህን ውሳኔ ተከትሎ ከሪፐብሊካኖችና ቤንያሚን ኔታንያሁ ወቀሳ ቀርቦባቸዋል።

ባይደን ዕገዳው በከፊል እንዲነሳ ወስነው ከዚያ በኋላ ሌላ ዕገዳ አልጣሉም።

ባይደን በበጎ እንዲታወሱ በሚል ትራምፕ ሥልጣን ከመያዛቸው ቀድሞ ለመጨረሻ ጊዜ የሚልኩት መሣሪያ ይሆናል።

ትራምፕ ጦርነቶችን የማስቆምና የአሜሪካ ተሳትፎ የመቀነስ ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ትራምፕ የእስራኤል ደጋፊ እንደሆኑ ቢገልጹም አሜሪካ በጋዛ ያላት ተሳትፎ እንዲያከትም ይሻሉ።