ጃኒና ሊማ

ከ 7 ሰአት በፊት

በብራዚል የቀድሞ የከተማ ምክር ቤት አባል በድጋሚ አለመመረጧን ተከትሎ የወሰደችውን የሽንት ቤት መቀመጫና እጅ መታጠቢያ መለሰች።

በድጋሚ ምርጫ ድምጽ ሳታገኝ ስትቀር የሽንት ቤት መቀመጫና ሁለት እጅ መታጠቢያዎችን ወስዳ ነበር።

ጃኒና ሊማ የተባለችው የምክር ቤት ኃላፊ የሳዎ ፓውሎ ምክር ቤት አባል ሆና በድጋሚ አለመመረጧን ተከትሎ ሠራተኞቿ ንብረቶቹን ሲወስዱ የሚያሳይ ቪድዮ ወጥቷል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ድርጊቱ ወቀሳ ሲያስከትልባት “በራሴ ተነሳሽነት ያገኘሁትን እቃ በልገሳ ለመስጠት ወስኛለሁ። እኔም ሆንኩ ሠራተኞቼ የሽንት ቤት መቀመጫው አያስፈልገንም” ብላለች።

የምክር ቤት አባል ሆና ከስምንት ዓመት በፊት ስትመረጥ በቢሮዋ የተተከሉ የእጅ መታጠቢያዎችና የሽንት ቤት መቀመጫን ሠራተኞቿ ነቅለው ሲወስዱ በሲሲቲቪ ታይተዋል።

መጸዳጃ ቤቱን ስትመረጥ ያስተካከለችው በራሷ ገንዘብ እንደሆነ ገልጻ፣ ንብረትነቱ የምክር ቤቱ አይደለም ስትል ተናግራለች።

ማንኛውም በግል ወጪ የተካሄደ ግንባታን መልሶ ማንሳት እንደሚቻል የሕግ ክፍል መመሪያ ማውጣቱን ጠቅሳለች።

ቢሮዋ ውስጥ በመስታወት ያሠራቸውን አካፋይ ግን ከሷ ቀጥሎ ለሚመጡት ተመራጭ ጥላው እንደምትሄድ ተናግራለች።

የ41 ዓመቷ የምክር ቤት አባል አምና በተካሄደ ምርጫ አንድሪልስ ጆርግ በተባለ ተወዳዳሪ ተሸንፈዋል።

አዲሱ ተመራጭ ለብራዚል መገናኛ ብዙኃን እንዳለው የሽንት ቤቱ ጉዳይ መፍትሔ እስከሚያገኝ “የጋራ መጸዳጃ” የሚጠቀም ይሆናል።

“ቢሮዋ በጥሩ ሁኔታ የተሠራ ነበር። አሁን ግን ሁሉንም ነገር መልሳ ወስዳዋለች” ብሏል አዲሱ ተመራጭ።

የምክር ቤቱ አዲስ መሪ ሪካርዶ ታክሲራ “ተመጣጣኝ እርምጃ” እንደሚወሰድ ተናግረዋል።