Saturday, 04 January 2025 20:57

Written by  Administrator

ወቅታዊው የጸጥታ መደፍረስና የኑሮ ውድነት ፈተና እንደሆኑበት  ዝግባ የሕጻናትና አረጋውያን መርጃ የበጎ አድራጎት ድርጅት አስታወቀ

ከተመሰረተ 16 ዓመታትን ያስቆጠረው ዝግባ የሕጻናትና አረጋውያን መርጃ የበጎ አድራጎት ድርጅት፤ በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስና የኑሮ ውድነት ፈተና እንደሆኑበት አስታውቋል። ድርጅቱ የምስረታ ክብረ በዓሉን ለማክበር በዝግጅት ላይ መሆኑንም ገልጿል።

ባለፈው ሐሙስ ታህሳስ 24 ቀን 2017 ዓ.ም. በጌትፋም ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የድርጅቱ ሃላፊዎችና የበጎ ፈቃድ አምባሳደሮች የተገኙ ሲሆን፣ ስለድርጅቱ ዝርዝር ማብራሪያ አቅርበዋል። በማብራሪያቸውም ላይ ድርጅቱ ዋና መቀመጫውን በባሕር ዳር ከተማ በማድረግ ከ2 ሺሕ 650 በላይ ወላጆቻቸውን በሞት ላጡና ለከፋ ችግር የተጋለጡ ሕፃናትና ጧሪ አልባ የሆኑ አረጋውያን በመደገፍ፣ እንዲሁም ችግረኛ ሴቶችን በገቢ ማስገኛ ስራ በማሰማራት ኑሯቸውን እንዲያደላድሉ ማስቻሉን የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ስለሺ ጌታቸው አመልክተዋል።

በ27 በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች የተቋቋመው ይህ የበጎ አድራጎት ድርጀት፣ የራሱ ተሽከረካሪዎች እንደሌሉት፤ የቦታ ጥበት እንዳለበት፤ የከርሰ ምድር ውሃ ችግር ስለመኖሩ በዚሁ መግለጫ ተነግሯል። ከዚህም ባለፈ በአማራ ክልል የተፈጠረውን የጸጥታ መደፍረስና የኑሮ ውድነቱን ተከትሎ፣ የተፈጠረው የፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት ዕጥረት “እየፈተነኝ ነው” ሲል ድርጅቱ አስረድቷል።

“ለአካል ጉዳተኞች እና ዕድሜያቸው ለገፋ ሰዎች የሚያገልግል ዊልቸር ዕጥረት ተፈጥሮብኛል” ያለው ድርጅቱ፣ በጎ ፈቃደኛ የሆኑ ግለሰቦች፤ በተለይም ከዚህ ቀደም ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ ባለሃብቶች ቃላቸውን ተግባር ላይ እንዲያውሉ ጠይቋል። የድርጅቱ የገቢ ምንጭ በአብዛኛው ከአባሎች በሚገኝ መዋጮ፣ በድርጅቱ ስር ካለው ትምሕርት ቤት እና በባሕር ዳር ከተማ ከከፈተው የፍራፍሬ ጭማቂ መሸጫ ቤት የሚመነጭ በመሆኑ፣ በስሩ ለሚገኙ 50 ቋሚ ሰራተኞች ደመወዝ ከመክፈል እና በማዕከሉ ላሉ ድጋፍ የሚሹ ወገኖች ድጋፍ ከማድረግ በዘለለ መጠነ ሰፊ ስራዎችን እንዳይሰራ ተግዳሮት እንደሆኑበት ጠቁሟል።

ዝግባ የሕጻናትና አረጋውያን መርጃ የበጎ አድራጎት ድርጅት 16ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓሉን ለማክበር መዘጋጀቱን በመጠቆም፣ ገቢ ከማሰባሰብ በተጨማሪ የመገናኛ ብዙሃን ትኩረታቸውን ለድርጅቱ እንዲያውሉ ዕንቅስቃሴ እንደሚያደርግ አብራርቷል።