
Saturday, 04 January 2025 20:52
Written by Administrator
ከአንድ ሳምንት በፊት በሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የታገደው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ሃይለማርያም፤ “ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የጣለብንን ዕግድ እንደሚያነሳ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ለአዲስ አድማስ ተናገሩ፡፡ የሚመሩት ማዕከል ከሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በዕግዱ ዙሪያ እየተመካከረ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ከታገደ አንድ ሳምንቱ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አዲስ አበባ የሚገኘው የማዕከሉ ዋና ጽሕፈት ቤት ስራ አቁሞ መዘጋቱን ገልጸዋል። የማዕከሉ የባንክ ሂሳብ መታገዱንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ያስረዱት አቶ ያሬድ፤ ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ባሳለፋቸው አራት ዓመታት ከመንግስት ጫና ደርሶበት እንደማያውቅ አስታውቀዋል። ይሁንና በሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን አስመልክቶ መግለጫዎችን ሲያወጣ መቆየቱን አልሸሸጉም፡፡
በማያያዝም፣ ማዕከሉ ትኩረቱን በጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ላይ በማድረግ፣ ከተለያዩ ወገኖች የሚደርስባቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚያጋልጥ ዋና ዳይሬክተሩ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል።
ታህሳስ 16 ቀን 2017 ዓ.ም. የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ለማዕከሉ ደብዳቤ ከመጻፉ አስቀድሞ ምንም ዓይነት የማስጠንቀቂያም ሆነ የምርመራ ሂደት እንዳልተከናወነ አቶ ያሬድ አስረድተዋል። ይህንን አስመልክቶም ማዕከሉ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ደብዳቤ እንደጻፈና በዕግዱ ዙሪያ ከመስሪያ ቤቱ ጋር እየመከረ መሆኑን ጠቁመው፤ “ባለስልጣኑ የጣለብንን ዕግድ እንደሚያነሳ ተስፋ አደርጋለሁ” ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል፣ በሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ዓዋጅ መሰረት በ2013 ዓ.ም. የተመሰረተ ተቋም ነው።