

በኢንጂነር አይሻ አህመድ የተመራው የልዑካን ቡድን በመቋዲሾ
ዜና ኢትዮጵያና ሶማሊያ አልሸባብን በጋራ ለመዋጋት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ
ቀን:January 5, 2025
ኢትዮጵያና ሶማሊያ ‹‹የጋራ ጠላት የሆነውን አሸባሪውን አልሸባብ›› በጋራ ለመዋጋት እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማጠናከር ከመግባባት ላይ ደርሰዋል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር አስታወቀ፡፡
የአገር መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ምስጋኑ አረጋ የተመራ ልዑክ የተካፈሉበት ስብሰባ ታኅሳስ 24 ቀን 2017 ዓ.ም. በሶማሊያ በመቋዲሾ መካሄዱ ተገልጿል፡፡
የአገሮቹ ከፍተኛ ልዑካን በአዲስ አበባና መቋዲሾ ባደረጉት ስብባባ፣ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮን (አትሚስ) በሚተካው የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ድጋፍና ማረጋጋት ተልዕኮ (AUSSOM) ተልዕኮን ውጤታማ ለማድረግ በትብብር ለመሥራት መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ነቢያት ጌታቸው (አምባሳደር) በሳምንታዊው ጋዜጣዊ መግለጫቸው፣ ከድኅረ አትሚስ በኋላ የሚኖረውን የኃይል ሥምሪት ኢትዮጵያ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲሆን ትፈልጋለች ብለዋል፡፡
በቱርክዬ አንካራ ሁለቱ አገሮች ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ እየተከናወኑ ስላሉ ዲፐሎማቲክ ግንኙነቶች፣ ከአንድ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ስለፈረመችው የባህር በር ስምምነት፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ጉዳይና የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ በሚሰማራው ሰላም አስከባሪ ኃይል የመሳተፍና አለመሳተፍ ሁኔታን በተመለከተ፣ የግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ ተደጋጋሚ መልዕክቶች በተመለከተ ሰፋ ያሉ ጥያቄዎች ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው ቃል አቀባዩ ምንም ዓይነት የተብራራ መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
ነቢያት (አምባሳደር) ሁለቱ አገሮች በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውንና በቀጣይ የመሪዎች ውይይት ለማድረግ ከስምምነት ደርሰዋል የሚል ድፍን ያለ ምለሽ በመስጠት መግለጫቸውን ቋጭተዋል፡፡
በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ፍሬያማና ውጤታማ ውይይቶች እየተካሄዱ መሆኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ የኤዩሶም ተልዕኮ የተሳካ እንዲሆነና በጋራ በመሆን የአልሸባብን የተደቀነ አደጋ ለመቀነስ በሚያስችል ደረጃ በጋራ መሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ የተስማሙበት ነው ብለዋል፡፡
ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ከሚሠሩ አካላት በጋራ ለመንቀሳቀስ ኢትዮጵያ ቁርጠኝነት እንዳላት ገልጻለች ያሉት ነቢያት (አምባሳደር)፣ ቀጣናውን ከሽብርተኝነት ለማፅዳት ከሶማሊያ መንግሥት ጋር አብሮ ለመሥራት ስምምነት ተደርሳል ብለዋል፡፡
በሶማሊያ በቀጣይ የሚኖረው የኢትዮጵያ ተሳትፎም በቀጣናው ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ማስረዳት ላይ ያተኮሩ እንቅስቃሴዎች ስለመደረጋቸውም አብራርተዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ኤዩሶም የመካተትና አለመካተት ጉዳይ ውይይት እየተካሄደበት ነው ብለዋል፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ከጥቂት ሳምንታት በፊት የነበረው መንፈስ ሌላ የነበረ ቢሆንም፣ ከአንካራው ስምምነት መልስ የሶማሊያ ሚኒስትር ዴኤታ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸውንና በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ታኅሳስ 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ወደ ሞቃዲሾ ተጉዘው ውይይት መካሄዱን የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ በቅርቡ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ በአዲስ አበባ ውይይት እንደሚካሄድና ዝርዝር መረጃዎች በዚያን ጊዜ የሚታዩ ይሆናል ብለዋል፡፡