
ዜና ሕንፃና መሬት ለቴሌኮም መሠረተ ልማት ግንባታ እንዲውሉ የሚያስገድድ ረቂቅ ሕግ ተዘጋጀ
ቀን: January 5, 2025
- ኢትዮ ቴሌኮም በተያዘው ዓመት በ140 ቢሊዮን ብር ማስፋፊያ አካሂዳለሁ ብሏል
የቴሌኮም መሠረተ ልማት ግባታዎች ለማከናወን የሚፈቅድና የሚያስገድድ የሕግ ረቂቁ ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት መሆኑን የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን አስታወቀ፡
ባለሥልጣኑ የመሬት አቅርቦት በሕግና በፖሊሲ እንዲፈታ ምክር ቤቱን ዕገዛ የጠየቁት የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ (ኢንጂነር) ናቸው፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ የመሠረተ ልማት ከተገነባ በኋላ መጠበቅ ያለበት ቢሆንም፣ በመላ አገሪቱ ሰው ማስቀመጥ ስለማይቻል ሁሉም ሰው ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡
የመሬት አቅርቦት ችግር በፖሊሲ እንዲደገፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ ለዚህም የሚረዳ የሕግ ረቂቅ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለኢትዮ ቴሌኮም የቀረቡ የሕዝብ ጥያቄዎችን በተመለከተ ታኅሳስ 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ውይይት አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን በየምርጫ ጣቢያዎቻቸውና በወከላችው ማኅበረሰብ አካባቢ፣ የመሬት አቅርቦት እንዲኖራቸው ድጋፍ አድርጉ ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ችግሩን እንደ አገር ለማስተካከል ሕንፃና መሬትን ለቴሌኮም መሠረተ ልማት ግንባታ ስለመጠቀም የሚፈቅድ መመርያ ተዘጋጅቶ የመጨረሻ ረቂቅ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ ነገር ግን በመመርያው ሕግ ሁሉም ክልሎች እንዲሳተፉበት ለማድረግ ምክር ቤቱ ድጋፍ ያድርግልን ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የመሠረተ ልማት ደኅንነት ካልተጠበቀ አገልግሎት ማቅረብ አስቸጋሪ መሆኑን የገለጹት ባልቻ (ኢንጂነር)፣ የጋራ ንብረት የሆነውን ሀብት ሁሉም አካል እንዲጠብቀው ጥሪ መደረግ እንዳለበት አስረድተዋል፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው፣ ለቴሌኮም መሠረተ ልማት የሚሆን የመሬት አቅርቦት በተለይም አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹አዲስ ሳይት በመትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉና የተዘረጉ መስመሮች ጭምር ኢትዮ ቴሌኮም ሊዝ እንዲፈጽም እየተጠየቀ በመሆኑ አገልግሎት ማስፋፋቱ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳረፈብን ነው፤›› ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የፋይናንስ እጥረት፣ የመንገድ ዕጦት፣ የፀጥታ ችግር፣ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ስርቆት፣ የመሬት አቅርቦትና የካሳ ጥያቄ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ኢትዮ ቴሌኮም አጠቃላይ ሥራውን አዳጋች ስለማድረጉ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡ ተቋሙ በተያዘው ዓመት ለያዘው 1,296 የሚሆን የማስፋፊያ ፕሮጀክት ከ140 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልገው የገለጹት ሥራ አስፈጻሚዋ፣ የአገልግሎት ማስፋፊያው በገጠራማው አካባቢ በብዛት እንደሚያተኩር ተናግረዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር 80.8 ሚሊዮን መድረሱን የገለጹት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ በመላ አገሪቱ 1,033 የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችና 8,530 ሞባይል ሳይቶቸ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ተቋሙ ቴሌ ብር በተሰኘው አፕሊኬሽኑ ከ3.38 ትሪሊዮን ብር በላይ ማንቀሳቅቀሱን፣ 8.7 ሚሊዮን ብር ከዓለም አቀፍ ሪሚታንስ ማግኘቱን፣ 16.9 ቢሊዮን ብር ብድርና 17.5 ሚሊዮን ቁጠባ መመዝገቡን ወ/ሪት ፍሬሕይወት አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ ከምክር ቤቱ አባላት በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣ በተደጋጋሚ ተጠይቀው ያልተመለሱ የቴሌኮም አገልግሎት በተለይም በቤንሻንጉል፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እንዲሁም በሌሎች ክልሎች ያሉ የቴሌኮም አግልግሎት ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡
በሌላ በኩል ከአባላቱ መካከል በግጭትና ጦርነት አካባቢዎች ተከታታይ የኢንተርኔት መቆራረጥና መዘጋት መኖሩን በተመለከት፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዩ ደሳኝ ጫኔ (ዶ/ር) ባቀረቡት ጥያቄ፣ በግጭትና ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች ተከታታይ የሆ የኢንተርኔት መቆራረጥ በተለይም የሞባይል ስልክና ኢንትርኔት መዘጋት ስለመኖሩ ተናግረዋል፡፡ ባላፉት አምስት ዓመታት በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት፣ በአማራ ክልል ጦርነት ከተጀመረ ጀምሮ ለአንድ ዓመት፣ ጦርነት ባለባቸው የከፊል ኦሮሚያ እንዲሁ የኢንተርኔትና የስልክ መቆራርጥ መኖሩን ተናግረዋል፡፡
ኢንተርኔት ከውኃና መብራት ተለይቶ አይታይም ያሉት አባሉ፣ ግጭትና ጦርነት ባሉባቸው አካባቢዎች ሰዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቀስው ክፍያ መፈጸም በማይችሉባቸው ሁኔታ ኢንተርኔት ሲዘጋ ለግጭት ተጋላጭ እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አክለውም ጉዳዩ መሰረታዊ የዜጎችን መብት የሚጋፋ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹እስካሁን ሲቋረጥ የነበረው ለምንድነው? ኢትዮ ቴሌኮም ወደፊትስ እነዚህ ነገሮች ላለመቀጠላቸው ምን ዋስትና ይሰጣል?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የግለሰቦች ሲምካርድና ቀፎ እንዳይሠራ እንደሚደረግ የተናገሩት ደሳለኝ (ዶ/ር) ‹‹ይህ እኔን የገጠመኝ የግል ጉዳይ ነው፣ ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል ጦርነት ሲከስት ስልኬም ሲም ካርዱም እንዳይሠራ ተደረገ፣ በዚህ ምክንያት ኢትዮቴሌኮም ይህን በማድረጉ እኔን አደጋ ላይ ጥሎኛል፣ ከወዳጅ ዘመድ ጋር የመግናኘት መብቴን ነፍጎኛል፤›› ብለዋል፡፡
አንድ ሰው በወንጅል የሚጠርጠርበት ጉዳይ ካለ እሱን ተከታትሎ የሚያስፈጽም አካል ስላለ ኢትዮ ቴሌኮም ይህን ሥራ መሥራት የለበትም ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሰጡት ምላሽ ‹‹ጥራት ያለው አገልግሎት እንድትጠቀሙ ነው የምንፈልገው በምንም መልኩ የእርስዎም ሆነ የሌሎች ደንበኞች ደንበኝነት እንዲቆረጥ ከፈለጉ ወይም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ባለዎት ስምምነት ለምሳሌ ደረሰኝ ባይከፈል ይሄንንም አሳውቀን ካልሆነ ዝም ብለን አንዘጋም ብለዋል››፡፡
ከፀጥታ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ቦታዎች ግጭቶች ሲኖሩ ለሚቋረጠው የኢንተርኔት ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ በመሆኑ ይህን እንደማያደርግ ተናግረዋል፡፡
‹‹ከኢንተርኔት ጋር ተያይዞ ለሚፈጠር መቆራረጥ የሚመለከተው ሌላ ተቋም ነው፣ የሚመለከተው ተቋም ጋር ጥያቄዎትን ቢያቀርቡ ወይም ውይይት ቢያደርጉ የተሻለ ነው እላለሁ፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡