ኤልያስ ተገኝ

January 5, 2025

በኢትዮጵያ የአገልግሎት ዘርፍ ከውጭ አገሮች በተለይም በቅርብ ካሉት የጎረቤት አገሮች ጋር ጭምር ሲነፃፀርና በብዙ መለኪያ ሲታይ፣ ብዙ ሊሠራበት የሚገባውን የአገሪቱ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ጥሩ ሥዕል እንዲኖረው፣ በብርቱ ከሚተጉ ኢንቨስተሮች መካከል አንዱ የሆነውና በ15 ዓመታት ውስጥ የሆቴልና ሪዞርት አሥረኛ ቅርንጫፉን በጂማ ከተማ ‹‹ኃይሌ ሪዞርት ጂማ›› በሚል ስያሜ ታኅሳስ 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ሥራ ያስጀመረው ‹‹የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርቶች ግሩፕ›› ቀጣይ ትኩረቱን ምስራቅ አፍሪካ ላይ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ባለባት የሰላም ችግር ምክንያት ለጊዜው ከሶማሊያ በስተቀር ግሩፑ ትኩረቱን በተለይ በኬንያና ዛምቢያ ማድረጉንና ኡጋንዳና ሩዋንዳም ለሥራ ጥሩ አማራጮች መሆናቸውን በተለይ ለሪፖርተር የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አትሌት ኃይሌ ሻለቃ ኃይሌ ተናግሯል፡፡

ከሐዋሳ እስከ አሥረኛዋ መዳረሻ ጂማ የዘለቀው የኢንቨስትመንት ግሩፑ እንቅስቃሴ አሥር የተለያዩ የአገሪቱን ከተሞች ከማዳረሱ ባሻገር በድምሩ ለ2,500 ዜጎች በዚህ ዘርፍ ብቻ ቋሚ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ማስቻሉ ይገለጻል፡፡

ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ስሟ ከፍ ብሎ እንዲጠራ ያስቻለው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ እንዴትና በምን ሁኔታ ወደ ሆቴል ኢንቨስትመንት እንደገባ ብዙም ሲገልጽ ባይሰማም ህልውናው አደጋ ላይ ይወድቃል ተብሎ በሚፈራው የሆቴል ኢንቨስትመንት ተሰማርቶ የሚገኘውና ሻለቃ ኃይሌና ቤተሰቡ የሆቴል ኢንቨስትመንት›› ድንበር ለመሻገር የሚያደርገው ጥረት ምን ደረጃ ደርሷል የሚሉትን ጥያቄዎች በመጪው ታኅሳስ 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ከሚከበረው የልደት (ገና) በዓል መልካም ምኞት ጋር በማያያዝ፣ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ለሪፖርተር ዘርዘር ያለ ሐሳቡን አካፍሏል፡፡

አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ እንደሚያስረዳው ከ15 ዓመት በፊት የመጀመሪያው ሆቴል በሐዋሳ ተከፍቶ ሥራ የጀመረበት ነው፡፡ ነገር ግን ሐሳቡ የመጣው ከዚያ ቀደም ብሎ ከሦስት ዓመት በፊት (ከ18 በፊት) ነው፡፡ ባህር ዳር ላይ አቶ መኰንን የሚባሉ ባለሀብት ሆቴል እንደነበራቸው፣ ሕይወታቸው ከማለፉ በፊት ወደ ባህር ዳር ወስደው ትምህርት ቤት ሕንፃ እንዲገነባ ያደረጉ መሆናቸውን፣ እሳቸው ካለፉም በኋላ ቤተ ዘመድ የእሳቸውን ሆቴል እንዲገዛ በዚያውም ቤተሰባቸውንም የማገዝ አጋጣሚ እንደሚሆንለት መጠየቁን ይገልጻል፡፡

‹‹ስለ ሆቴል ኢንቨሰስትመንት አላውቅም›› የሚል አስተያየት ቢሰጥም ኋላ ላይ ግን ልግባበት ብሎ ቢገባም በወቅቱ የአቶ መኰንን ሆቴል የልማት ባንክ ዕዳ እንደነበረበት በሰዋዊ ችግር ምክንያት አለመሳካቱን እንደሆነ ሻለቃ ኃይሌ ይናገራል፡፡

የግዢውን አለመሳካት ሲያስረዳም ‹‹እባክህን ሼሕ መሐመድ አላሙዲን የሰጡት ዋጋ 45 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ አንተ የሰጠኸው 40 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ የሆነ ነገር በል›› አሉኝ፡፡ ‹‹እኔ ከእሳቸው ጋር ልወዳደር ነው ወይ? ሁለተኛ እንዳትደውሉልኝ›› ብሎ ምላሽ መስጠቱንና ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲያቀርብ ቢጠየቅም ራሱን ማግለሉን ያስረዳል፡፡

ከሲድኒ ኦሎምፒክ መልስ የቀድሞው ደቡብ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት አቶ አባተ ኪሾ ለሁሉም አትሌቶች መሬት ሲሰጡ ኃይሌም 5,000 ካሬ ሜትር ቦታ እንደደረሰውና በተጨማሪ 6,000 ካሬ ሜትር መሬት በሊዝ በመግዛት ከ15 ዓመት በፊት በሐዋሳ ከተማ የመጀመሪያውን ሪዞርት ለመገንባት መብቃቱን አትሌት ኃይሌ ያስረዳል፡፡

‹‹እንደከፈትኩት አትርፎን ሳይሆን ኪሳራ ውስጥ ነው የከተተን፡፡ እንድ ወዳጄ አንድ ሆቴል ራስ ምታት ነው፣ ሁሉትና ሦስት ሲሆን ቢዝነስ ነው አለኝ፡፡ ከዚያም ሻሸመኔና ዝዋይ እያልን እያስፋፋን መጥተን ዛሬ የደረስንበት ደረስን፡፡ በወቅቱ አንዱንም ቢሆን ጨርሶ የመሥራት እንጂ በዚህ ደረጃ ተስፋፍቶ በሆቴል ኢንቨስትመንት ላይ መቆየት የማይታሰብ ነበር፤›› ሲል ኃይሌ ያክላል፡፡

የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርቶች ኢንቨስትመንት በተለያዩ ክልሎች ላይ መሆኑን፣ ምንም እንኳን ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ወላይታ፣ ሲዳማ እየተባለ ቢገለጽም፣ በውጭ አገሮች ወይም ነጮች በአንድ ነገር እንደሚያምኑ፣ ማንም ኢትዮጵያዊ በሌላ አገር ሄዶ ከየት ነው የመጣኸው ቢባል ሊመልሰው የሚችለው ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ እንደሆነ፣ ነገር ግን አሁን የጠፋው ይሄ መሆኑን ባለሀብቱ ይናገራል፡፡

‹‹ኢትዮጵያዊ ሀብታም ይሁን፣ ታዋቂ ይሁን፣ አዋቂ ይሁን በቃ ዕድል ነው›› ሲል የተናገረው ኃይሌ፣ እሱ አገሩን የሚያያት እንደዚያ  መሆኑን፣ ሰው ሌላ ነገር ሊመስለው ቢችልም እርሱ ግን ኢትዮጵያዊያን ቁጥር አንድ ሕዝቦች ነን ይላል፡፡

የሆቴል ኢንቨስትመንቱን ወደ ምሥራቃዊ ኢትዮጵያ የማስፋፋት ዕቅድ ላይ መሆኑን በማስረዳት፣ ከምንም በላይ እያጠና ያለው ከቢዝነሱም በላይ የሕዝቦች አመለካከትና አስተሳሰብ ብዙ ነገር እንደሚወስድ መሆኑን በመግለጽ ነው፡፡

‹‹ፖለቲከኞች በተወሰነ የጊዜ ቆይታ የሚቀያየሩ ናቸው፡፡ ዛሬ የነበረ በሁለትና ሦስት ዓመት ውስጥ ላታገኘው ትችላለህ፡፡ ብቻ ማወቅ ያለብን ከተቸገርኩባቸው ነገሮች ውስጥ እኛ ያው ኢትዮጵያኖች ነን፡፡ እኔ ለምሳሌ ኦሮሚያ ተወልጄ አማርኛ ቤት ውስጥ ስለሚነገር አማርኛ ለመድኩ፡፡ አንዳንዴ በቋንቋ ሰውን የምትፈርጀው ከሆነ ፈልጎት ነው እንዴ? ሃይማኖትን ፈልጎት ነው? በምርጫህ አይደለም? አሁን ይሄ ነው የጠፋን፤›› ሲል ያብራራው ሻለቃ ኃይሌ፣ ‹‹ይሄ አቅቶን ነው ችግር ውስጥ የገባነው›› ሲልም ያስረዳል፡፡ የሚያሳዝነው ከውጭ ያሉ ተመልካቾች ግን እንደ አንድ ነው የሚያዩን ሲልም ያክላል፡፡ ልዩነት አይኑር አይባልም፡፡ የተለያዩ ነገሮች አንድ ላይ ሲሆኑ እንደሚያምሩ ሻለቃ ኃይሌ ያስረዳል፡፡

አንድ ቱሪስት ወደ አንድ አገር ሲመጣ መጀመሪያ የሚጠይቀው ‹‹ደኅንነቱ የተጠበቀ አገር ነው ወይ? እኔ ምንም የደኅንነት ችግር አይገጥመኝ ወይ? በደንብ ወጥቼ፣ ገብቼ፣ ነድቼ፣ ተዝናንቼ፣ ወጥቼ፣ ወርጄ ጎብኝቼ እመጣለሁ ወይ?›› የሚለውን ሲሆን፣ ይህን መጀመሪያውኑ ካልቻለ ከጅምሩም እንደማይመጣ ባለሀበቱ ይጠቅሳል፡፡

‹‹ከዚህ በፊት ተናግሬዋለሁ የፈለገ ብትለው ላንተው ይሁንህ ነው የሚልህ፡፡ ይህን አትክድም፡፡ አስቸጋሪ ነው ለምን መሰለህ ቱሪስትን ለመሳብ የምንወጣው የምንወርደው ነገር ይኼንን ካልፈታኸው ትርጉም የለውም፡፡ ይኼን ደግሞ መዋጥ መቻል አለብን፡፡ ማወቅ መቻል አለብን፤›› ያለው ኃይሌ ‹‹ቱሪስቶችን የሚስቡ ነገሮች ብለን ብዙ እንወጣለን፣ እንወርዳለን፣ እናሳምራለን ነገር ግን ቱሪስቱ ደኅንነቴ የተጠበቀ ነው ወይ አንድ ነገር ቢመጣ ይልና ያንተ ዋና ገነት ቢሆን አልመጣም ነው የሚለው፤›› ሲል ያስረዳል፡፡

ሰው ለምንድነው ከአዲስ አበባ ጂማ በአውሮፕላን የሚመጣው? በጣም የሚያምር መንገድ እኮ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ጂማ በመኪና መምጣት በጣም የምወደው ነገር ነው፡፡ ምርጫህን ንገረኝ ብትል ከአዲስ አበባ ወደ ጂማ እኔ መምጣት የምፈልገው በመኪና ነው፡፡ የጊቤን ዳገት ስትነዳ ዝንጀሮዎቹን እያየህ በጣም ደስ የሚል ዕይታና ውበት ነው፡፡ ማን ነው 700 ብር የሚያስወጣውን መንገድ 7,000 እየከፈለ የሚመጣው? ደስ ስላለው፣ ብር ስላለው፣ ሀብታም ስለሆነ አይደለም፣ ደኅንነቱ አስተማማኝ (Safe) አይደለም ብሎ ስለሚያስብ ነው፡፡ የሚል ሐሳብ የሚያቀርበው ሻለቃ ኃይሌ፣ ይህ ማለት ግን ሁሉም ነገር ጦርነት ብቻ ነው ለማለት አይደለም ሲል ያስረዳል፡፡

ምንድነው መሆን ያለበት? በተቻለ መጠን በጋራ ሆነን ችግሮቻችንን ቁጭ ብለን መፍታት አለብን፣ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ሽንፈትን አይፈልግም፡፡ እኔ ስናገር አንዱ/ሌላው አካል ዋው ያደረከው በጣም ጥሩ ነገር ነው ብሎ ይናገራል፣ ሌላው ደግሞ ለምን እንደዚያ አልክ ይላል፡፡ እባካችሁ ያለው እውነታ እንደዚያ አይደለም፡፡ እውነታውን እናውራ፣ እውነቱ ምንድነው? ጂማ፣ ሐዋሳ እንዴት በአውሮፕላን እንሂድ? መሆን የለበትም፡፡ እየነዳን፣ እየተደሰትን፣ ልጆቻችንን እያዝናናን እኛም እየተዝናን መሄድ አለብን፡፡ አገራችንንንም እያወቅን መሄድ አለብን፤›› ሲል ሐሳቤ ነው ያለውን አስተያየት ሰጥቷል፡፡

የኃይሌ ሆቴልና ረዞርቶች ግሩፕ ኢንቨስትመንት ወደ ምሥራቅ አፍሪካ የማስፋፋትን ዕቀድን በተመለከተ ሐሳቡን የገለጸው ሻለቃ ኃይሌ፣ ኢንቨስት ከሚያደርግባቸው አገሮች ውስጥ የመጀመሪያ ምርጫው ሶማሊያ ልትሆን እንደማትችል፣ የሌላ አገር ስለሆነች ሳይሆን ትልቅ የሰላም ችግር ያለባት አገር ከመሆኗ ጋር በተያያዘ እንደሆነ፣ ኢንቨስትመንት የሚፈልገው ነገር ሰላምን በመሆኑ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

ኬንያ ላይ ብዙ ቢዝነስ እንዳለ፣ ውድድሩና ፉክክሩ ከፍተኛ እንደሆነ በዚህም ብዙ ነገሮችን እያጠና እንደሚገኝ ያስታወቀ ሲሆን፣ ውድድርን እንደሚወድ፣ ከዚህ ባሻገር ዛምቢያ ሌላዋ ተመራጭ አገር እንደሆነች፣ ይህም የሆነው ሕዝቡ ሰላማዊ፣ አገሪቱ ያላት ኢንቨስትመንት ዕድል፣ የመሬት፣ የቱሪስት ፍሰቱ ሌሎች ጉዳዮችም ሲታዩ ካለው ምቹነት አኳያ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ኡጋንዳና ሩዋንዳም ተመራጮች መሆናቸው ኃይሌ አክሏል፡፡

‹‹የገና በዓል አከባበሬ ድሮ ቢሆን ደስ ይል ነበር፣ አሁን አስከባሪ ነኝ›› የሚለው አንጋፋው አትሌት፣ ገና በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በእርሱ አካባቢ ሲከበር ቅርጫ፣ ዶሮ ወጥ፣ ዳቦ፣ የገና ጨዋታ፣ ጠላ ለምሳሌ አሁን ላይ አንዳንድ ጊዜ አሰላ እንደሚሄድ፣ በተለይ ከገና አልፎ ለሚመጣው የጥምቀት በዓል ላይ ምርጥ ጠላ መጠጣት የፈለገ አሰላ መሄድ እንዳለበት ይመክራል፡፡ የዛሬ ዓመት ትንሹ ልጁን ይዞ አሰላ እንደሄደ ይገልጻል፡፡

የገና በዓል በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በደንብ የምታከብረው በዓል እንደሆነና በዚሁም ለዕምነቱ ተከታዮች የመልካም ገና በዓል ምኞቱን አስተላልፏል፡፡

በዓላት በመጣ ቁጥር አብሮ የሚመጣው የኑሮ ውድነት ነው፡፡ የኑሮ ውድነትን አንዱ የምንከላከልበት ነገር የማያስፈልገንን ነገር ባለመግዛት ነው፡፡ ኬክ የማይበላ ሰው ቤት ኬክ ይዞ መሄድ፣ እንደው ኢትዮጵያኖች ትንሽ ባህላችንን ቀየር ብናደርገው በይሉኝታ ምን ይዤ ልሂድ የሚለው ግንኙነታችንን እንዳይሰብር መጠንቀቅ አለብን፡፡ ሄዶ ቤተሰብን፣ እናት አባትን ጠይቆ፣ በቤት ውስጥ ያለችውን ትንሽ ነገር አዘጋጅቶ፣ ተጠያይቆ የምንመጣበት ጊዜ እንዲሆን ነው የምፈልገው ይላል፡፡ አክሎም ምክንያቱም ከውጭ የሚመጡ መጠጦችም ሊሆኑ ይችላሉ ወይም ሌሎች ዕቃዎች በጣም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ አገር ውስጥ ያሉ ነገሮችም ጭምር፡፡ እነዚህ ነገሮች ግንኙነታችንን እንዳያራርቁ፣ ኅብረተሰቡ ይኼን ነገር እንዲያስወግድ ነው አደራ የምለው ባይ ነው ኃይሌ፡፡ ሊገባን ይገባል አሁን እየተፋፈርን ስለሆነ ነው እንጂ ማንም እየተቋቋመው (Afford) እያደረገ አይደለም፡፡ ከሁለትና ሦስት ዓመት በፊት 10 እና 15 ሺሕ ደመወዝ የሚያገኙት ሠራተኞች ጥሩ ነበሩ፡፡ አሁን ግን 30 እና 40 ሺሕ ብር ደመወዝ የሚያገኙት ጥሩ ደረጃ ላይ ናቸው አልልም፡፡ የቤት ኪራይ፣ የትምህርት ቤት ክፍያው፣ የኑሮ ውድነት ሰማይ ወጥቷል፣ ስለዚህ ይህንን ተገንዝበን በዓል በመጣ ቁጥር የምናከብራቸውን ሰዎች ስንጠይቅ ከራሳችን ጋር ያለውን አገናዝበን የማይሆንና ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ማድረግ እንደሌለብን በመገንዘብ በስምምነትና በበጋራ ማስቆም አለብን ሲል አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ተናግሯል፡፡