
እኔ የምለዉ የሐረሪን ክልል በኦሮሚያ የመጠቅለል ዕሳቤ ፌዴራላዊ ሥርዓትን ማፍረስ ወይስ መገንባት?
ቀን: January 5, 2025
በኑረዲን አብደላ
በቅርቡ ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽን የቀረበው የሐረሪን ክልል በኦሮሚያ የመጠቅለል አጀንዳ የነባር ሕዝቦችንና የብሔር ብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብትን የሚፃረር፣ በምሥራቅ አገራችን የነበረውን በአንድነት አብሮ የተጋመደ ማኅበረሰብን ማለያየት ነው።
ጥቂት የኦሮሞ ፖለቲከኞች ሕገ መንግሥቱን በመፃረር በአንድ በኩል ፌዴራላዊ ሥርዓት እንዲያብብና የብሔር ብሔረሰቦች መብት እንዲከበር እንፈልጋለን በማለት የፌዴራላዊ ሥርዓት አቀንቃኝ ሆነው ለመታየት ሲከጅሉ፣ በሌላው መልካቸው ደግሞ ሌላ አናሳና ነባር ሕዝቦችን የራስ በራስ የማስተዳደር ኅብረ ብሔራዊነትን በመደፍጠጥ የአንድ ብሔር የበላይነት በመገንባት ፀረ ሕገ መንግሥትታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ለበርካታ ዓመታት በኦሮሞና በሐረሪ የነበረውን የጋብቻ፣ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የሥነ ልቦና አንድነት በመበጣጠስ ሁከትና ጥላቻ በሕዝቦች መካከል አለመተማመን እንዲኖር ፀረ ሰላም በሆነ መንገድ ለመንቀሳቀስ ሲሞክሩ ይስተዋላል፡፡
ነገር ግን መሆን የነበረበት ሌሎቹን በመደገፍ አብሮ በመሥራትና አብሮ በአንድነት፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ በመተሳሰር የአገርንና የሕዝቦችን ችግር በመቅረፍ የበለጠ የተረጋጋ ማኅበረሰብ በመፍጠር የአገራችንን የሁከት ፖለቲካ መለወጥ በተቻለ ነበር። ሐረሪዎችና የሐረሪ ክልል ሌሎቹን አቅፈው ፍቅር በመለገስ ሐረሪዎች ሐረርን በሥልጣኔ በዓለም ቅርስ እንዳስመዘገቡት፣ የኦሮሞ የዘውግ ፖለቲከኞች ክልሎችን ለሌሎች ፍቅር መለገስና ሁሉን ዜጋ አቃፊ መሆን መልካምነት ሲሆን፣ በተቃራኒው የሌሎችን ሀብትና መሬት በሕገወጥነት መውረር መደፍጠጥና ማፈናቀል ክልሎችን መሰረዝና መደለዝ ታላቅ ሕገ መንግሥታዊ ጥሰትና ወንጀል ነው። ሰሞኑን ታኅሳስ 13 ቀን 2017 ዓ.ም. በእነ አቶ ብርሃኑ ቦሬሳ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቀረበ በተባለው አጀንዳ ሐረር ከተማ በኦሮሚያ ይጠቃለል ብለዋል፡፡
ጥያቄው የሐረሪ ክልልና የሐረር ከተማ ባለቤትነት የማነው? ሐረር ከተማ መቼ ተቆረቆረች? ሐረርን የቆረቁሩ በቀል ማኅበረሰብ (Indigenous) ማነው? የሐረር ከተማ ስያሜው ማን አወጣለት? የሐረር የሙስሊም ሡልጣኔት የሐረር አሚሮች መንግሥት ሲቆሮቁሩ ኦሮሞ የሚባል በአካባቢው ነበረ ወይስ? የኦሮሞ የታሪክ ጸሐፊዎችን ጨምሮ ኋላ ላይ በተለያዩ የታሪክ ምሁራን በ16ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ሐረር የመጣው የገዳ ጦር አድራጊዎች እንዴት በሐረር አካባቢ እንደሰፈሩ ከታች በማቀርበው መረጃ በዝርዝር እናየዋለን።
የሐረር ከተማና ዙሪያው የሐረሪ ማኅበረሰብ ከኋለኛው ማኅበረሰብ አብራክ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ አገር በቀል (Native Indigenous) ነው። የሐረሪ ማኅበረሰብ የሰፈረበትን መልክዓ ምድር ሐረር የሚለውን ስያሜ ከአብጀድ (200+200+5 = 405) 405 ዓመተ ሂጅሪያ በመሰየም አገሩን በራሱ ቋንቋ ደግሞ [ጌይ]፣ [ሐረር ጌይ] እንጂ ኦሮሚያ ብሎ ባልሰየመበትና የሐረሪ ማኅበረሰብ ሐረርን ከአንድ ሚሊኒየም በላይ ራሱን በራሱ ባስተዳደረበት፣ ታሪክና ቅርሶቻቸውን ከአገር አልፈው ለዓለም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስመዝግበው ባስተዋወቁበትና በገነቡት የሥልጣኔ ማዕከል ሐረርና የሐረሪ ክልል ለምንድነው በኦሮሚያ የሚጠቃለለው? የሐረሪ ማኅበረሰብ የሐረርን ከተማ በመቆርቆር ታላቅ እስላማዊ ሥልጣኔ፣ ትምህርት፣ ንግድና እርሻ በምሥራቅ አፍሪካና በመላው ኢትዮጵያ እስልምናን በማሠራጨት የአንበሳውን ድርሻ የተወጣ ማኅበረሰብ ነው።
የሐረሪ ማኅበረሰብ በሰፈረበት መልክዓ ምድር በሐረርና አካባቢው ባሳለፋቸው የሥልጣኔ ዘመናትና ሐረርን የሥልጣኔ ማዕከል በማድረግ የእስልምና መንግሥትና በአሚር ሥርዓት የሚተዳደር ሥርዓት በአሚር ወድ በኒሂሻም አመኽዙሚ (እ.ኤ.አ .896) በመዘርጋት፣ ከአሚር ሓቦባ ቢን ሀሩን ቢን ኢስሃቅ (እ.ኤ.አ. 969) እስከ አሚር አብዱላሂ ቢን መሐመድ (እ.ኤ.አ. 1887) በራሱ ነፃ ግዛት ሐረር ከተማ መስተጋብሮች በመፍጠር፣ የበርካታ የሚዳሰስና የማይዳሰስ ቅርስ (Tangible and Intangible) ባለቤት በሰፈረበት መልክዓ ምድር ላይ ለመሆን የቻለ እስከ ዛሬም የቀጠለ ማኅበረሰብ ነው፡፡ ታዲያ በምን ሥሌት ነው በኦሮሚያ የሚጠቀለለው? የሐረሪ ማኅበረሰብ ከላይ የተዘረዘርውን በርካታ ታላላቅ እስላማዊ ሥልጣኔዎችን በመገንባት ሒደት ውስጥ በርካታ ጦርነቶች ተከስተዋል፣ ብዙ ጥፋቶችን ታይተዋል፡፡ የአዳል ጦርነት፣ የፈጥ ጋር ጦርነት፣ የሰሜን የዋግ ጦርነት፣ የሽንብራኩሬ፣ የአዞሎ፣ የሉባ፣ የገዳ፣ የጨለንቆ፣ ወዘተ. የአገራችን የእርስ በርስ የጦርነት ታሪክ ጥቂቶቹ ናቸው።
በአሥራ ስድስተኛው መካከለኛው ክፍለ ዘመን ከኢማም አህመድ አልጋዚ (እ.ኤ.አ. 1527-41) ጦርነት ማግሥት በከፍተኛ ፍጥነት የአገራችን የሰሜን ክርስቲያን፣ የደቡብ ምሥራቅ የሙስሊም ሡልጣኔቶች እርስ በርስ በጦርነት የተዳከሙበት ስለነበር ለኦሮሞ አባ ገዳዎች ጥሩ ዕድልና አዲስ የጦርነት በአዲስ የግዛት መስፋፋት ዕድል ስለገጠማቸው፣ በዚህ ጦርነት አጠናክረው መገስገስና የቀድሞ የሙስሊምና የክርስቲያን ይዞታዎችን በቁጥጥራቸው በማድረግ መስፈር ጀመሩ፡፡ ይህንን በተመለከተ ዝርዝሩን በመረጃ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡
በደቡብና በምሥራቁ አገራችን ሥልጣኔ የሚጀምረው ከቅድመ ታሪክ ከሐርላ ምድርና ማኅበረሰብ፣ እነዚህ የሐርላ ማኅብረሰብ ቅድመ እስልምና የተፈጥሮ ክስተቶችን አምላኪ (አዎማዊ እምነት) ተከታይ የሆኑ ማኅበረሰብ መሆኑን የታሪክ መረጃዎች ያመለክታሉ። ስለሐርላ ማኅበረሰብ እምነትና ማንነት በተመለከተ የተከበሩ ፕሮፌሰር ላዺሶ ጌ ድሌቦ እንዲህ ያቀርቡታል፡፡
በክፍለ አገሩ የደቡብና የምሥራቅ የመሀል ደጋማና ጤናማ ክልሎች ጥንታዊው የሐርላ፣ የሀዲያ፣ የዳሞት ጎንጋ፣ የጋሞ ወላይታ ሕዝቦችና መንግሥታት በቅርቡ ሦስቱ መለኮታዊ አሀዳዊ የክርስትና፣ የኦሪትና የእስልምና ሃይማኖቶች ወደ አካባቢው ከመግባታቸው በፊት ከላይ ከቀረቡት የግብፅ፣ የዳማት፣ የሳባ፣ የግዕዝ፣ የግሪክና የላቲን ጥንታዊው ሰነዶች በየትም ሥፍራና ጊዜ ተጠቅሰው አልተገኙም፡፡ ይሁን እንጂ በሌላ በኩል በሐረርጌ ደገማ ክፍል ከለገኦዳ ዎሻ ቢሲዲሞከሻቤ ዎሻ (ኤረር ሰቃሸሪፍ ዎሻ) ተሥለው የተገኙት ጥንታዊው የእንስሳትና የሰዎች፣ እንዲሁም በደቡብ ሸዋ በአርሲና በሐረርጌ ደጋ በብዙ ሥፍራዎች የሚገኙ ተክል ድንጋይ ሐውልቶች በጥንታዊው ግብፃዊያን ግሪኮች ሮማዊያንና ዓረቦች ሆነ አክሱማዊያን በቀጥታ ባልደረሱ የደቡብና የመሀል ኢትዮጵያ ክልሎች፣ ቢያንስ ገና ከዛሬ ከ5‚000 ዓመታት በፊት ገደማ ጀምሮ በእንስሳት እርባታ በእርሻና በዕደ ጥበብ ተግባራት የተሰማሩና በአዎማዊ ሃይማኖቶች የተደራጁ ጥንታዊው የሐርላና የሐዲያ ተዛማጅና አጎራባች ሕዝቦች ይኖሩባቸው እንደነበረ በግልጽ ያሳያል (ፕረፌሰር ላጲሶ ጌ ድሌቦ፣ 1999 ገጽ፣ 99—97)፡፡
የሐርላ ማኅበረሰብ የቀደምት ሥልጣኔ ፈር ቀዳጅ የሥልጣኔ ቁንጮ ከሆኑት በንግድና በግንባታ በእርሻ መስኖ ሥራ፣ እንዲሁም በእጅ ጥበብ ሥራ ዋናዎች ተጠቃሽ ሥራዎች ናቸው። በዛሬው በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ከሰባተኛ ክፍለ ዘመን እስከ ዘጠነኛ ክፍለ ዘመን በንግድ፣ በእደ ጥበብና በእርሻ፣ እንዲሁም የእስልምና ሃይማኖት ወደ ሐርላ አካባቢ በሚደርስበት ወቅትና ጊዜ የሐርላ ማኅበረሰብ ከአዋማዊ እምነት ወደ እስልምና በቀጥታ የተቀበሉና በእስልምና ሃይማኖት የተጠቃለሉ ማኅበረሰብ የሐርላ ነባር ሕዝቦች ናቸው። በዚህ መሠረት በታሪክ የተረጋገጠው ነባርና ጥንታዊው የሐርላ ማኅበረሰብ የሚከተሉት ናቸው፡፡ እነሱም ሐርላ ጋቱሪ፣ ጊዳያ፣ ጌሲ፣ ኤቡ፣ አፋር፣ አርጎባ፣ ሐረሪ፣ ስልጤ፣ ወለኔ፣ ሱማሌ፣ ሐዲያ፣ አቦኝ፣ አዲሽ፣ ሐርጋይ፣ ሒጋን፣ ዋርጋር፣ አውአሪ፣ ዘሙባራህ፣ ባርዛራህ፣ ያቆላይ፣ ጃዛር፣ ዓረብ፣ ታከላና አልቃ (ምንጭ፣ ከይረዲን ተዘራ 2004፣ ፕሮፌሰር አህመድ ዘከሪያ 1992፣ ፕሮፌሰር ላጲሶ 1999፣ ጥንታዊው የሾንኬ መንደር የአርጎባ ሕዝብ መነሻና የማንነት ግንዛቤ ገጽ 15)፡፡ በተጨማሪም የፈረንሣይ የኢትዮጵያ ጥናት ማዕከል (French Center for Ethiopia Studies) ዋና ተመራማሪና ዳይሬክተር ፍራንስዋ ግዛቭዬ ፍቪል በሐርላ ጥንታዊው ነባር ሕዝቦች ሥልጣኔ ባደረጉት ምርምር እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹ሐርላ ማኅበረሰብ እስልምናን ከተቀበለ በኋላ በሐርላ መንደር የተገነቡትን የፈራረሱ መስጊዶች መቃብሮች የመቃብር ላይ ጽሑፎች ሳንቲሞች ይህም ከ13ኛ እስከ 16ኛ ክፍለ ዘመን የነበሩ ሥልጣኔ ውጤቶች ማግኘታችንን እንገልጻለን››፡፡
ልብ በሉ ከላይ በተጻፈው ጽሑፍ የኦሮሞ ማኅበረሰብ አልተጠቀሰም፣ የለም፡፡ ምክንያቱም ይህ የሆነበት የኦሮሞ ማኅበረሰብ በሐርላው ቅድመ ታሪክ ሆነ ኋላም የሐርላ ማኅበረሰብ እስልምናን ከተቀበለ በኋላም የሐርላ ማኅበረሰብ ከሚኖርበት አካባቢ ኦሮሞ ማኅበረሰብ ባለመኖሩ፣ የኦሮሞ እንቅስቃሴ እስከ ተጀመረበት 16ኛው ክፍለ ዘመን ኦሮሞች በገዳ ባህላዊ (አዋማዊ) አምላኪ በመሆኑ እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን በኋላም በዚሁ አምልኮ ቆይቷል፡፡
ሌላው የኦሮሞ ማኅበረሰብ ገዳ እምነት ተከታዮች በሠፈራና የግጦሽ መሬት ይዞታ እንቅስቃሴ ባደረጉት ትንቅንቅ የሁለቱን ሃይማኖቶች፣ የሰሜን ሰሎሞናዊያን ክርስትና እምነትና የደቡብ ምሥራቅ የሐርላ የእስልምና እምነትና ሥልጣኔ ውጤቶችን የገዳ ተዋጊዎች በጦርነት አውድመውታል። ይህንን ሁኔታ ግልጽ አድርጎ ለማመልከት በሐርላ ጂኦግራፊያዊ ምድር የነበሩት ጥንታዊው የሐርላ ሙስሊም ሡልጣኔቶች የአካባቢ ነገሥታትና ግዛቶች የኦሮሞ ገዳዎች፣ በገዳና በቡታ አደረጃጀት በመጠናከር ጥቃት በመክፈት የሐርላ እስልምና ሡልጣኔቶች ግዛት፣ እንዲሁም የክርስቲያናዊ ነገሥታት ግዛት በቁጥጥር ሥር ያደረጉበት ቀጥለን እንመልከት። የኦሮሞ ታሪክ ካጠኑት ይልማ ደሬሳ 1999 ዓ.ም. የ16ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ገጽ 223 እስከ 248 የኦሮሞ መጀመሪያ መኖራቸው፣ ወላቡ የሚባል ውብ ቦታ ነበር መሬት ሲጠባቸው ወደ ሰሜን መንቀሳቀስ ተጀመረ፡፡
ከወላቡ ወደ ኦዳኖቤ
ኦዳኖቤ ላይ ለአምስት ትውልድ ከትመው ተቀመጡ፡፡ አራት ትልልቅ የኦሮሞ ነገድ በአንድነት ነበሩ (ከረዩ፣ ቱለማ፣ ሜጫና ወሎ) ከዚያም የሙስሊሞችና የክርስቲያን ወገኖች የሚደረጉት በጦርነት ሲዳከሙ ለገዳዎች ምቹ ሁኔታ ተፈጠረላቸው (“ወላቡ” ቦታውን ደራሲው ሲገልጽ፣ በዋቢ ሸበሌና ጁባ ወንዞች መካከል ከሚገኘው የቤናድር ወደብ አንስቶ በስተምሥራቅ ባሌ በስተደቡብ እስከ ሰሜን ኬንያ በስተሰሜን እስከ ዓባይ ሐይቅና ወላቡ ተራራ ድረስ ሰፍሮ የሚገኝ ቦታ ነው)፡፡
የኦሮሞ ገዳ እንቅስቃሴ የግዛት ወረራ በዓመተ ምሕረት
በ1524 ዓ.ም. ኦሮሞዎች ለመጀመሪያ ከደቡብ መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ ጃዊ የተባሉት የበርቱማ ከፊል ጎሳዎች ናቸው የዋቢን ወንዝ ተሻግረው ደቡብ ባሌን ወረሩ፡፡ በ1538 ዓ.ም. የሙደና ገዳ ስምንቱ ዘመን በተፈጸመበት ጊዜ በርቱማዎች ባሌን በሙሉ ይዘው የኦሮሞ ጦር በፈጥጋርና ደዋሮን ማጥቃት ጀመረ። ይህ ሁሉ ሲሆን ዘመቻ ያደረገው የከረዩ ነገዶች ሲሆኑ የቀሩት ቱለማ፣ ሜጫ፣ ወሎ የተባሉት ከወላቡና ከኦዳነቤ ሳይንቀሳቀሱ ቆዩ። በ1551 ዓ.ም. የምችሌ ገዳ ጦር አድፍጦ ጠበቀው አሚር ኑር ከገላውዶዮስ ጦርነት ገጥሞ ጦርነት በጦርነት የተረፈ በድል ሲመለስ የአሚር ኑር ሠራዊት ሐዘሎ በሚባለው ሥፍራ ባላሰቡት ባልሰሙት የምችሌ ገዳ ጦር የአዳልን ጦር ድባቅ መታው፡፡ በታሪክ ውስጥ የአዳል ጦር እንዲህ ተብሎ የማይባል ጉዳት ደረሰበት፡፡ ከዚህ በኋላ የአዳል ጦር ማገገም አልቻለም፡፡ በ1544 ዓ.ም. የኦሮሞ ጦር ከሰሜን ባሌ ተጉዞ ፈጥጋርንና ደዋሮን ማጥቃት ጀመረ፡፡ በ1554 ዓ.ም. የምችሌ ገዳ ጦር የደዋሮን ፈጥጋር ማጥቃት ጀመረ። እስካሁን ያየነው የኦሮሞ ማኅበረሰብ ከሐርላ ማኅበረሰብና ከሰሎሞናዊ ክርስቲያን ከሚኖርበት ጂኦግራፊ (መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ) ውጪ ከሚኖርበት ገዳዎች በከፍተኛ የተደራጀ ኃይል፣ አቅምና ችሎታ ተንቀሳቅሶ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ግዛቶች ይህንን በተመለከተ የኦሮሞ ታሪክ ምሁራን መሐመድ ሐሰን “The Oromo of Ethiopia” በሚል ርዕስ፣ አሰፋ ጃለታ ‹‹Oromia and Ethiopia›› በሚል ርዕስ፣ እንዲሁም ከአገር ውጪ ጸሐፊያን ኡልሪች በራውካመር (Ulrich Braukamper) ‹‹Oromo Country of Origin›› በሚል ርዕስ የጻፉትን መመልከት ይቻላል፡፡
እነዚህንና ሌሎችንም ማጣቀሻ በማድረግ አቶ አባ ዱላ ገመዳ በ1996 ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ከየት ወዴት?›› በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቁት መጽሐፋቸው ስለኦሮሞ ገዳ እንቅስቃሴና በጦርነት በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ግዛቶች በ16ኛ ክፍለ ዘመን በገጽ 6፣ ‹‹የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት የኦሮሞ ሕዝብ ለ12 ተከታታይ ቦታዎች (የገዳ ሥርዓቶች) በመዋጋት ከ1522 እስከ 1618 ከሞላ ጎደል አሁን ያለበትን መልክዓ ምድራዊ ይዞታ በቁጥጥር ሥር አውሏል። በመጀመሪያዎቹ ሁለት ገዳዎች ማለትም በሜልባና በሙዳ ከ1522 እስከ 1538 የባሌን ግዛት ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል።
‹‹በሦስተኛና በአራተኛ ገዳዎች በኪሎሌና ቢፎሌ ከ1554 እስከ 1554 ዓል ደዋሮንና ፈጥጋርን ተቆጣጥሯል። በአምስተኛው ገዳ በሚችሌ ከ1554 እስከ 1562 ድረስ የፊንፊኔ (ሸዋ) አካባቢዎችና በአቅራቢያው የሚገኙትን የክርስቲያንና የእስላም ይዞታዎች በእጅ ለማግባት የቻለ ሲሆን፣ በስድስተኛውና በሰባተኛው ገዳዎች ሀርመፋና ሮበሌ ከ1562 እስከ 1578 መንዝ፣ ጎንደር፣ ደንቢያ፣ ጎጃምን በቁጥጥር ሥር አስገብቷል። በስምንተኛው የቢርመጂ ገዳ ከ1578 እስከ 1586 አስቀድሞ በደምቢያና አካባቢው ላይ የተከፈተውን ጥቃት በማጠናከር የጣና ሐይቅ አካባቢዎች ለመያዝ በቅቷል። በዘጠነኛው የሙለታ ገዳ 1586 እስከ 1594 የጎጃምን አንዳንድ አካባቢዎችና የተመረጡ የትግራይ የዳሞት አካባቢዎችን ለመያዝ ችሏል፤›› በማለት አሥፍረዋል፡፡
ከብዙ መረጃ ጥቂቱን ከላይ ለመመልከት እንደተሞከረው የኦሮሞ ማኅበረሰብ ከሐርላ ነባር ማኅበረሰብ መልክዓ ምድር ክልል ውጪ የነበረ፣ ከጊዜ በኋላ ወደ ሐርላ (አዳል)ና ክርስቲያን ምድር ኦሮሞች እንደተንቀሳቀሱ በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ከላይ አባ ዱላ መረጃውን አስነብበውናል። አሁንም ይህንን መረጃ ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ ድሌቦ፣ 2008 ዓል፣ የኢትዮጵያ ታሪክ መነሻ ሒደት ከዘመነ ሜጋሊቲዝም እስከ ሪፐብሊክ ከ1500 ዓል ለም እስከ 2000 ዓል ገጽ 44 ውስጥ፣ ‹‹ከ1520ዎቹ እስከ 1620ዎቹ አሥርታት ዘመን ድረስ በአንድ ምዕተ ዓመት ውስጥ በርቱማና ቦረና በተባሉ ሁለት አውራ ጎሳዎችና ከረዩ፣ ወሎ፣ ቱለማና ሜጫ በተባሉት አራት ቅርንጫፍ ማኅበረሰቦች ተከፍሎ በሚከተሉት አሥራ ሦስት ጠንካራ የፊለሳና የሠፈራ አባ ሉባዎች (አዝማቾች)፣ ሜልባህ ከ1522 እስከ 1530፣ ሙደና ከ1530 እስከ 1538፣ ኪሎሌ ከ1538 እስከ 1546፣ ቢፎሌ ከ1546 እስከ 1554፣ ምስሌ ከ1554 እስከ 1562፣ ሐርሙፋ ከ1562 እስከ 1570፣ ሮበሌ ከ1570 እስከ 1578፣ ቢርመጃ ከ1578 እስከ 1586፣ ሙልአታ ከ1586 እስከ 1594፣ ዱሎ ከ1594 እስከ 1602፣ ዳግማዊ ሜልባ ከ1602 እስከ 1610፣ ዳግማዊ ሙደና ከ1610 እስከ 1618፣ ዳግማዊ ኪሎሌ ከ1618 እስከ 1618 ተብሎ ይጠራል፡፡
ፕሮፌሰር ላጲሶ እንደሚገልጹት በድምሩ በ104 ዓመታት ድርጅታዊና ትውልዳዊ ስምንት ዓመት የዘመቻ አመራር (እንቅስቃሴ) በደቡብ ምሥራቅ ከገናሌ ወንዝ በመነሳት በአብዛኛው የዛሬ ደቡብ ምሥራቅ መሀልና ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ላይ በመስፋፋት፣ ብሎም በተጠቀሱት አካባቢዎች ከጥንቱ ነባር ኩሻዊ፣ ሴማዊና ኦሞአዊ የባሌ፣ የደዋሮ፣ የአዳል፣ የሐዲያ፣ የፈጥጋር፣ የወርጅ፣ የሐርላ፣ የሱማሌ፣ የአፋር፣ የአርጎባ፣ የይፋት፣ የአማራ፣ የትግሬ፣ የጋፋት፣ የአይመላል፣ የጉራጌ፣ የዳሞት፣ የቦሻ፣ የእናሪያ፣ የቢዛም፣ ሕዝቦችና መንግሥታት ጋራ በሰፈራ፣ በጊዜ፣ በጦርነት፣ በጋብቻ፣ በቋንቋ፣ በጎሳ፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በሥርዓት በመወራረስ በአጭር የታሪክ ዘመን ውስጥ ከሥፍራና ከቁጥር አኳያ ዛሬ የኢትዮጵያ ትልቁ ማኅበረሰብ ለመሆን በቃ (ለተጨማሪ መረጃ ፕሮፌሰር ላጲሶ፣ 2008 ዓል ገጽ፣ 44 ይመልከቱ)፡፡
እስካሁን ከላይ ባየናቸው የምሁራን መረጃዎች ቀደምት የሐርላ ነዋሪዎች የኦሮሞን ማኅበረሰብ ያላቀፈ፣ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ከጊዜ በኋላ በ16ኛ ክፍለ ዘመን ወደ ሐርላ ሙስሊም ሡልጣኔቶችና የሰሎሞናዊያን ክርስቲያን ግዛቶች የተቆጣጠሩት መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ሐርላዎች ከአዋማዊ እምነት ቀጥታ ወደ እስልምና ሃይማኖት እስላማዊ መንግሥት (ሡልጣኔቶችን) ገንብተዋል፣ መሥርተዋል፡፡ ኦሮሞዎች የገዳ ሥርዓትና እምነቱም ዋቀይፈቻ አማኞች የሐርላ ሡልጣኔት እምነት ሥልጣኔን በጦርነት የተዋጉና በቁጥጥር ሥር ያዋሉ፣ እንዲሁም የክርስቲያን በተመሳሳይ ግዛቱን የሠፈሩበትና የገዳን ሥርዓት አጠናክሮ የገነባ ማኅበረሰብ ነው።
የኦሮሞ አሠፋፈር በምሥራቅ አገራችንና በሐረር አካባቢ በተመለከተ አቪሻይ ቤን ዶር፣ ‹‹አሚራዊቷ ሐረር፣ ግብፅና ኢትዮጵያ›› (Avishai Ben-Dror; Emirates, Egyptians and Ethiopia) በሚል ርዕስ በ2018 ዓ.ም. ለዶክትሬት ማሟያ ባሳተመው መጽሐፍ በገጽ 19 እንዳሠፈረው፣ ‹‹የሐረር ኦሮሞ በምሥራቅ በሐረር በኩል የሚኖሩ ኦሮሞዎች ዋና ምንጫቸው ባሬንቱ ነው፡፡ ከደቡብ ከቦረና ተንቀሳቅሰው በምዕራብ በኩል አድርገው ወደ ምሥራቅ የሐረር አካባቢ የመጡት፡፡ ባሬንቱ ወደ ሐረርጌ አካባቢ የመጣው እ.ኤ.አ. ከ1530 እስከ 1540 ባለው ጊዜ በመንቀሳቀስ ጨርጨር፣ ወቦራ፣ ሐብሮ፣ በጋራ ሙለታ፣ ድሬዳዋ፣ ጉርሱም፣ ጂጂጋና ሐረር ሠፈሩ፡፡ ባሬንቱ በወቅቱ ወደነዚህ አካባቢዎች በተንቀሳቀሰበት ወቅት ዘመን ሙሉ በሙሉ እስልምናን ሃይማኖት አልቀበልም በተጨማሪም የእስልምና የፖለቲካ መንግሥትን ሥልጣን ዕውቅና አልቀበልም በማለት ውድቅ አደረገ:: ባሬንቱ ከጥገኛ ውጪ የራሱ የሆነ ተቋም በማቋቋም እንደ ገዳ፣ ቦኩና ሞቲ መሪ ራሱን ከእስልምና ሃይማኖትና መንግሥት ጥገኛ ያልሆነ ለመሆን የቆመ የባሬንቱ ጎሳ ነበር፤›› በማለት ይተነትናል፡፡
አቪሻይ ቤን (ዶ/ር) በተጨማሪም፣ ‹‹በሐረር አካባቢ የተሰባሰቡት የባሬንቱ ጎሳ ወደ ውስጥ ሲወርድ ወደ ተለያዩ ጎሳዎች ይከፈላል፡፡ በዚህ መሠረት በሐረር በዙሪያው የሚገኝት በባሬንቱ ጎሳ ሥር የሚከተሉት ጎሳዎች ይገኛሉ፤›› ካለ በኋላ፣ ‹‹ኢቱ፣ አኒያ፣ አላ፣ ባቢሌ፣ ኦቦራ፣ ጃርሶ፣ ኖሌ ናቸው፡፡ በኦሮሞ ጎሳዎች ባህላዊ ገለጻ መሠረት ቃሉ አራት ልጆች አሉት እነሱም አላ፣ ባቢሌ፣ ዶጋ፣ ኦቦራ ናቸው:: ዶጋ፣ ሦስት ልጆች አሉት እነሱም ኖሌ፣ ጃርሶ፣ ሁሚ፤›› ናቸው::
እነዚህ ካላይ የተጠቀሱት የኦሮሞ ጎሳዎች በሐረር ዙሪያ የሚገኙ ናቸው:: በሐረር አካባቢ ዙሪያ ያሉ የኦሮሞ ጎሳ ጥምረት አፍረንቀሎ ይባላሉ፡፡ እነሱም አራቱ የቃሉ ልጆች ናቸው:: አፍረንቀሎ በሐረር ታሪክ ትልቁን ሚና የተጫወቱ ናቸው፡፡ ይህ ማለት አፍረንቀሎ በሐረር የእስልምና ታሪክ በሐረር አሚሮች ታሪክ እስከ እ.ኤ.አ. 1875 የግብፆች ሠፈራና ወረራ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው፣ በማኅበራዊና በሃይማኖት ተሳትፎ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል [ለተጨማሪ መረጃ Avishai Ben-Dror Emirate,Egyptian,Ethiopian p:20 ይመልከቱ]፡፡ የሐረሪ ታሪክ ምሁር አብዱሰመድ እንድሪስ በአንድ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ እ.ኤ.አ. በአፕሪል 2019 ከፖለቲካና አክቲቪስት ጀዋር መሐመድ ጋር በሐረር አዳራሽ በስብሰባ ላይ የታሪክ መረጃችንን በማመሳከር በቀረበው ትንተና፣ ከላይ የቀረበውን የኦሮሞ አሠፋፈር በሐረር ዙሪያ በነበሩ ቀደምት ነባር የሐረሪ ማኅበረሰብና መስተጋብርን የሚያመለክት ነው፡፡ የታሪክ ምሁሩ አቶ አብዱሰመድ የሐረሪ ሕዝብ አገር በቀል (Native and Indigenous) የኦሮሞ ታሪክና ባህል አዋቂዎች የተናገሩትን የሚከተለውን አቅርቧል፡፡
አፍረንቀሎ እዚህ አካባቢ ላይ ሲወርና ሲይዝ ሲያደላድል ለአራቱ ልጆች ይህንን (ሐረር) አካባቢ ሲያከፋፍል መሀል ላይ ያለችውን አልነካም፡፡ አራቱ ልጆች ዳጋ፣ ኢቱ፣ ባቢሌና ኦቦራ ናቸው:: እነዚህን ክፍፍል ድልድል ያደረገው ከሐረር ውጭ ያሉት ቦታ ላይ ነው:: ይህንን ቦታ (ሐረርና ዙሪያውን) ለማንስ ተውከው ብለው በየነ ሰንበቶን ሲጠይቁት?
‹‹ተና ሁንዴዳ (ይህ የሁንዴ ነው)
ሁንዴን ሆለላቲ (ሁንዴ የሆለላ ነው)
ሆለላን ከአባቲ›› (ሆለላ መሬት ደግሞ የነባሩ የባለቤቱ ነው)
ብሎ ለበየነ ሰንበቶ የሐረር ዙሪያ ሐረሪዎች የነበሩበት “ሆለላን ከአባቲ” ሐረሪዎች ባለመሬትና አገር በቀል መሆናቸውን በመግለጽ፣ መሬታቸውን ሆለላን ሳይነካና ሳይደለድል በታሪክና በኦሮሞ ባህልና ወግ መታወቁን አስረድቷል፡፡
የሐረር ነፃ አሚራዊ አስተዳደር ሥርዓት ያከተመው በሐረር አሚር አብዱላሂና በአፄ ምኒልክ በጨለንቆ ጦርነት እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 6 ቀን 1887 ወደ ኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግሥት ስትጠቃለል ነው፡፡ አፄ ምኒልክ ከራስ መኮንን ጋር በመሆን የዕርቅና የሰላም ድርድር ያደረጉት፣ ከአገሩ ከመሬቱ ባለቤት ከሆነው ከሐረሪ የአገር ሽማግሌና የፖለቲካው ባለቤት ከሆኑት ከሐረሪዎች ጋር ነበር፡፡ አፄ ምኒልክ ያደረጉት የሰላም ስምምነት ራሱን በራስ ያስተዳድር ከነበሩት የመሬቱ ባለቤት ከሆኑ የሐረሪ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር የሰላም ስምምነት ተደረገ የሚከተለው መረጃ መታየቱም በቂ ነው፡፡
ስምምነቱ የተከናወነው በሼኽ አቦከር ቦታ በድሬ ሹንቡሬ ጥላ ሥር በወርኃ ግንቦት 2 ቀን 1879 ዓ.ም. (ጁማዱል አወል 1304 ሂጅሪያ) የሐረር ሹማምንቶችና ተወካዮች፣ በሐረሪዎች እጅግ የተወደዱና የተከበሩ ሽማግሌዎች ለድርድር የሚከተሉት ሐረሪዎች አፄ ምኒልክ ፊት ቀረቡ፡፡ እነሱም ሐጂ ዩሱፍ በርኸድሌ፣ ሼኽ ዓሊ አቡበከር፣ ቃዲ አብዱላሂ አብዱረህማን፣ ገራድ አብዱረህማን ኬነዋቅ፣ ገራድ አብዱል ወሃብ፣ ሼኽ አህመድ አማኖ ናቸው፡፡
በተመሳሳይ በአፄ ምኒልክ በኩል ሦስት ሰዎች ለድርድር ቀረቡ፡፡ እነሱም ፊታውራሪ ተሰማ፣ ፊታውራሪ ዘራይ፣ ሰይድ ቡሽራ ነበሩ፡፡ በዚህም መሠረት የሐረር ሽማግሌዎች አንደኛ በሃይማኖታችን ጣልቃ አትግቡ፣ ሁለተኛ ወግ ልማዳችንን አክብሩ፣ ሦስተኛ ማንም ክርስቲያን በጉዳዮቻችን አያገባውም፣ አራተኛ የምንፈልገው የውስጥ አስተዳደራችን እንዲጠበቅልን ነው፣ አምስተኛ የሐረሪ ሕዝብ ከያዘው የመሬት ርስቱ እንዳይነጠቅ እንሻለን፣ ስድስተኛ በደል እንዲፈጸምብን ከቶ አንፈልግም፡፡ ‹‹ይህ ይከበርልን ዘንድ ጥያቄያችን ነው፤›› ብለው አቀረቡ፡፡
አፄ ምኒልክ የሐረሪዎችን ጥያቄ በጥሞና ካዳመጡ በኋላ፣ ‹‹ጥያቄያችሁ ይህ እስከሆነ ድረስ ምን ገዶ ችግር አይኖርም፤›› ብለው ቃል ገቡ፡፡ በተራቸው፣ ‹‹እናንተ የሐረር ሰዎች ሦስት ጉዳዮችን ታሟሉ ዘንድ የግድ ነው፡፡ እነሱም አንደኛ የግብፅ መንግሥት ይወስደው ከነበረ ማንኛውም ዓይነት የገቢና ወጪ ግብር እንዳትደብቁኝ፣ ሁለተኛ ማንኛውም ዓይነት አገሬን የሚጎዳ ጉዳይ ከባዕድ ስታዩ አትደብቁኝ፣ ሦስተኛ ሕዝብ ላይ በደል ሲደርስ ሲያጋጥም በኃላፊነት ባስቀመጥኳቸው ሰዎች ጆሮ አድርሱ፣ እንዲከለከልም አድርጉ፡፡ ካልሆነላቹሁ ጉዳዩን ወደ እኔ አድር፤›› ብለው አዘዙ፡፡ በዚህም መኋላ ተፈጸመ (ለተጨማሪ መረጃ የሐረሪ ዓመጽ ገጽ 104-105 ይመልከቱ)፡፡
በዚህ ስምምነት ምክንያትም ሐረሪዎች የእርሻ መሬታቸውን በገባር ሥርዓት አልተነጠቁም፡፡ የሐረሪ ሕዝብ በገባር ሥርዓት ሥር አልወደቀም፡፡ የሐረር ሕዝብ በጢሰኛ ሥርዓት ሥር አልወደቀም፡፡ ይህ ሁሉ ከሆነና የፌዴራል ሥርዓት ከተዘረጋ ከ1883 ዓ.ም. እና የራስ ዕድል በራስ ማስተዳደር ከተረጋገጠበት በኋላ በኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ ኦሮሚያ የሚል ክልል ካርታና አካባቢ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ፀደቀ፡፡ ከዚያ በፊት በዚህ ስምና በካርታ የተካለለ ክልል በኢትዮጵያም ሆነ ቅድመ ኢትዮጵያ አልነበረም፡፡ በተመሳሳይም የሐረሪ ማኅበረሰብ የሐረርን ከተማና ምሥራቁን የአገራችን አካባቢዎች ከአንድ ሺሕ ዓመታት በላይ በራሱ አሚሮችና መሪዎች ራሱ በራሱ ያስተዳደረና እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀ የባለብዙ የታሪክ፣ በ1883 ዓል የሐረሪ ብሔራዊ ክልል የፌዴራሉ አንድ ክልል ሆኖ ፀደቀ፡፡ ይህ ብሔራዊ ብቻ ሳይሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የነባር ሕዝቦች መብት (United Nations Declaration on the Rights of Indigenous Peoples) ያረጋገጠው ሀቅ ነው፡፡
በእርግጥም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስለነባር ሕዝቦች መብቶች መግለጫ እ.ኤ.አ. በ2007 የተቋቋመው “UNDRIP” በዓለማችን የነባር ሕዝቦች ሰብዓዊ መብትና እ.ኤ.አ. መስከረም 13 ቀን 2007 ታስቦ እንዲውል ሲደረግ፣ በዚህ ጉባዔ ከመቶ በላይ የዓለማችን የነባር ሕዝቦች (Indigenous) ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ የነባር ሕዝቦች የመሬት፣ የውኃ፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ የማዕድን፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የተፈጥሮ ብክለት፣ የሀብት ክፍፍሎሽ፣ ወዘተ. ነባሩን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ መብታቸው እንዲጠበቅ የሚያስደርግ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስምምነትን ከአባል አገሮች 143 ሲደግፉት፣ 11 ድምፅ ተአቅቦ በሆነ አብላጫ ድምፅ ሊፀድቅ ችሏል።
ይህም ሆኖ ባለፉት ቅርብ ዓመታት በሕገወጥ መሬት ወረራና በሕገወጥ እርሻ ከማሳቸው የተፈናቀሉ የሐረሪ ገበሬዎች የእርሻ ማሳቸው እንዲመለስላቸው አገራዊ የምክክር ኮሚሽንን እየተጠየቀ ባለበት ጊዜ፣ ጥቂት የኦሮሞ የዘውግ ብሔርተኞች ሕገ መንግሥትን በመናድ የሐረሪ ብሔራዊ ክልል አፍርሰን ወደ ኦሮሚያ እንቀላቀላለን የሚለውን ዕሳቤ አመንጭተዋል፡፡ ይህም ትልቅ ሕገ መንግሥታዊ ወንጀል ሲሆን የታላቁን የኦሮሞን ማኅበረሰብ አቃፊነት ለሌሎች ብሔር ብሔረሰብ ያለውን ክብር የሚያሳንስ ድርጊት ነው። እንዲህ ያለው አመለካከት ካልቆመ ለአገሪቱ አደገኛ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው nur_man77@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡