

ማኅበራዊ በድንበርና በኬላዎች አካባቢ ለሚከናወኑ የላቦራቶሪ አገልግሎቶች የሚያግዙ መሣሪያዎች ርክክብ ተደረገ
ቀን: January 5, 2025
ለክልል ላቦራቶሪዎች አቅም ግንበታ የሚሆኑና አንድ ቢሊዮን ብር ዋጋ የወጣባቸው ልዩ ልዩ የላቦራቶሪ መሣሪያዎች ርክክብ ተከናወነ፡፡ መሣሪያዎቹ በተለይ በድንበርና በኬላዎች አካባቢ ለሚከናወኑ የላቦራቶሪ አገልግሎቶች ያግዛሉ ተብሏል፡፡

ለተለያዩ ጤና ተቋማት ዕገዛ የሚያደርጉና በሃያ አምስት ሚሊዮን ብር የተገዙ 55 ሞተር ሳይክሎችም ለየተቋማቱ ታድለዋል፡፡
ታኅሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቅጥር ጊቢ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት፣ የላቦራቶሪ መሣሪያዎችን ለኢንስቲትዩቱ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ተወካዮች ያስረከቡት የጤና ሚኒስትሯ መቅደስ ዳባ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
ሚኒስትሯ አራተኛው የጤና ፖሊሲ ሥራ ላይ እንዲውል መደረጉን ገልጸው፣ ፖሊሲው በውስጡ ሦስት ዓበይት ጉዳዮችን ማቀፉን፣ ከእነዚህም መካከል ዋነኛውና ትልቁ የጤና ሥርዓትን ማጠንከር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የጤና ሥርዓቱም ለተፈጥሮና ለሰው ሠራሽ አደጋዎች የማይንበረከክ፣ ይበልጥ ተጠናክሮ የሚወጣና የዜጎችን ጤንነት የማስጠበቅ ትልም ያለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
4,000 የጤና ተቋማትን ከላቦራቶሪ ጋር የማስተሳሰር ሥራ መከናወኑንም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሣይ ኃይሉ (ዶ/ር)፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚያዋስኑ ድንበሮች የላቦራቶሪ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውንና የድንበር ጤና ኬላዎች መቋቋማቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ቁሳቁሶቹ በእነዚህ ኬላዎች ለሚከናወኑ የላቦራቶሪ አገልግሎቶች ምላሸ ለመስጠት የሚያስችሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የላቦራቶሪ መሣሪያዎቹና የሞተር ሳይክሎችን ወጪ የሸፈኑት የዓለም ባንክና የኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ ያቋቋሙት በተላላፊ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር፣ በላቦራቶሪ አቅም ግንባታና በሰው ኃይል ሥልጠና ዙሪያ የሚሠራ ፕሮጀክት መሆኑንም አክለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ለወሊድና ድንገተኛ አደጋ ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ 370 አምቡላንሶችንም ለክልሎች ጤና ቢሮዎች ያስረከበውም በዚሁ ሳምንት ነው፡፡
አምቡላንሶቹ የእናቶችንና ሕፃናትን ጤና ከማሻሻልም ባለፈ በወሊድ ወቅት እናቶችን ወደ ጤና ተቋማት በአፋጣኝ እንዲደርሱ በማስቻል የእናቶችን ህልፈት ለማስቀረት እንደሚያስችሉና የድንገተኛ አደጋ ሕክምና አገልግሎትን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሻሽል መቅደስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
አምቡላንሶቹን ማኅበረሰቡ በባለቤትነት ተረክቦ መጠበቅ እንዳለበት፣ የጤና ባለሙያዎችም አምቡላንሶቹን በአግባቡ በመጠቀም ማኅበረሰቡን እንዲያገለግሉ መመርያ አስተላልፈዋል፡፡
የተደረገው ድጋፍ በኢትዮጵያ ያለውን የአምቡላንስ አቅርቦት ሙሉ ለሙሉ የሚሸፍን ባለመሆኑ ወደፊትም ተጨማሪ አምቡላንሶችን ለማዳረስ ባለድርሻ አካላት መሥራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡