በመሬት መንቀጥቀጡ በዱለቻ ወረዳ የፈራረሱ ትምህርት ቤቶች ጤና ጣቢያዎችና መኖሪያ ቤቶች

ማኅበራዊ እየተከሰተ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ወደ ሌላ ሥፍራ ለማሥፈር…

የማነ ብርሃኑ

ቀን: January 5, 2025

የመሬት መንቀጥቀጥ በሚያሠጋቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ወደ ሌሎች ሥፍራዎች ለማስፈር ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑ ታወቀ፡፡

በአፋር አዋሽ ፈንታሌ፣ በኦሮሚያ ፈንታሌና በዱለቻ ወረዳዎች በሚገኙ አሥር ቀበሌዎች በተደጋጋሚ እየተከሰተ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ ለአደጋ ተጋላጭ ናቸው ተብለው የተለዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሌሎች አካባቢዎች ላይ ለማስፈር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የዝግጅት ሥራ በመሥራት ላይ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

እየተከሰተ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ወደ ሌላ ሥፍራ ለማሥፈር ዝግጅት ተጀመረ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በመሬት መንቀጥቀጡ በዱለቻ ወረዳ የፈራረሱ ትምህርት ቤቶች ጤና ጣቢያዎችና መኖሪያ ቤቶች

በኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ዓለማየሁ ወጫቶ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በመስከረም ወር 2017 ዓ.ም. የጀመረውና ከታኅሳስ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ በአካባቢዎቹ ላይ በተደጋጋሚ እየተከሰተ በሚገኘው የመሬት መንቀጥቀጥ የመንገድ መሰነጣጠቅና በተወሰኑ ቤቶች ላይ የመፍረስ ምልክቶች ታይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ታኅሳስ 22 እና 23 ቀን 2017 ዓ.ም. የመሬት መንቀጥቀጥ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በመገኘት የመስክ ምልከታ ማድረጋቸውን የጠቆሙት ሥራ አስፈጻሚው፣ በመስክ ምልከታው በአካባቢው በሚኖሩ ዜጎች ላይ የከፋ አደጋ ሳይደርስ ወደ ሌሎች ሥፍራዎች ስለሚዘዋወሩበት ሁኔታ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ መሠራት እንዳለበት ታምኖበታል፡፡

እንደ ዓለማየሁ (ዶ/ር)፣ የመሬት መንቀጥቀጡ በተደጋጋሚ እየተከሰተባቸው በሚገኙ አካባቢዎች ከመሬትና መንገድ መሰንጠቅ፣ እንዲሁም ከተወሰኑ ቤቶች የመፍረስ ምልክቶች በስተቀር በሰውና በእንስሳት ሕይወት ላይ እስካሁን የደረሰ አደጋ የለም፡፡

‹‹ተፈጥሯዊ ክስተቶች ተገማችነታቸው አዳጋች ነው›› የሚሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎችን ሊደርስ ከሚችለው አደጋ ለመታደግ ከአካባቢው የማንሳትና ከሥጋት የራቁ ቦታዎች ላይ ለማስፈር ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤት፣ ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳና ከአጋር ድርጅቶች የተውጣጣ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

እንደ ዓለማየሁ (ዶ/ር)፣ ምን ያህል ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ከአካባቢው እንደሚነሱና ወደ ተዘጋጀላቸው ሌሎች የማረፊያ ሥፍራዎች እንደሚጓጓዙ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን በፈንታሌ ተራሮች ዙሪያ (በአፋርና ኦሮሚያ ክልሎች) የሚገኙና ለአደጋ ተጋላጭ ናቸው ተብለው በተለዩ ቀበሌዎች የሚኖሩ ዜጎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲሰፍሩ የሚደረግ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አንድ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት በባቡር ሀዲድ መስመሩ ላይ የደረሰ አደጋ መኖር አለመኖሩን የሚያጠና የባለሙያዎች ቡድን ወደ ሥፍራው ልኳል፡፡

በመስከረም ወር 2017 ዓ.ም. በመጀመሪያው ዙር በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በመስመሩ ላይ ምንም ዓይነት የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ባለሙያዎች አረጋግጠዋል ያሉት የሥራ ኃላፊው፣ አሁን ላይ በድግግሞሽ የሚታየውና የማግኒትዩድ መጠኑ እየጨመረ በመጣው አደጋ በባቡር መስመሩ ላይ የደረሰ አደጋ መኖር ያለመኖሩን ባለሙያዎች የሚያረጋግጡት ይሆናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ሲስተም ማኔጅመንት ዳይሬክተር ኢንጂነር ዮሴፍ ታምሩ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት በመንገድና በድልድዮች ላይ የደረሱ አደጋዎችን የሚያጠና የባለሙያ ቡድን ወደ አካባቢው ተንቀሳቅሷል፡፡ በመሆኑም ቡድኑ በሚያመጣው የጥናት ውጤት መሠረት ጉዳት መኖርና ያለመኖሩ የሚረጋገጥ ይሆናል፡፡

‹‹በመጀመሪያው ዙር በአካባቢው ላይ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ በአካባቢው በሚገኙ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ላይ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ መሥራት እንዳለብን የጠቆመን ነው፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ መንገዶቻችንና ድልድዮቻችን ለመሬት መንቀጥቀጥ ምን ያህል ተጋላጭ ናቸው? የትኞቹስ ይበልጥ ያሠጋቸዋል? የሚለውን የመለየት ሥራ በአስተዳደሩ በኩል እየተሠራ ያለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ኢንጂነር ዮሴፍ፣ ከዋናው መንገድ ተገንጥሎ የሚሄደውና ወደ ከሰም ስኳር ፋብሪካ የሚወስደው መንገድ የመሰንጠቅ አደጋ ደርሶበታል፡፡ ሆኖም ግን ይህን የተመለከተና በዋናው መንገድ ላይም የመሬት  መንቀጥቀጡ ያደረሰው ተፅዕኖ ካለ በሥፍራው ካሉ ባለሙያዎች ጥናት በመነሳት ውጤቱ በቀጣይ ሳምንት ይፋ የሚደረግ ይሆናል ብለዋል፡፡

በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምድር ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ጌታቸው ገብረ ጻድቃን ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የመሬት መንቀጥቀጡ እየታየ ያለው በአዋሽ ፈንታሌ ዙሪያ ነው፡፡ የድግግሞሽ መጠኑ እየጨመረና የማግኒቲዩድ መጠኑም እስከ 5.3 ከፍ በማለት ላይ ይገኛል፡፡

‹‹የመሬት መንቀጥቀጡ ሲስተዋልባቸው በነበሩ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ዱለቻ ወረዳ፣ ዶፋን ተራራ ላይ በዛሬው የዕለት እሳተ ጎመራ መፈንዳቱን ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምተናል፤›› ያሉት ኃላፊው፣ ፍንዳታው ኃይለኛ ድምፅ የነበረውና ጭስ የታየበት ነው፡፡ እሳተ ጎመራው የፈነዳበት ሥፍራ በመጀመሪያው ዙር የመሬት መንቀጥቀጥ የፍል ውኃ የፈለቀበት አካባቢ ስለመሆኑም ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ጌታቸው፣ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምድር ትምህርት ክፍል የመጀመሪያውን ዙር የመሬት መንቀጥቀጥ ለማጥናት ወደ ሥፍራው አቅንቶ ነበር፡፡ በአደጋውም ከሰም ስኳር ፋብሪካ አካባቢ ያሉ መኖሪያ ቤቶች፣ የፋብሪካው ጽሕፈት ቤቶትና ሕንፃዎች መፍረሳቸውንና መሰንጠቃቸውን ተመልክቷል፡፡ ለሸንኮራ አገዳ ልማት የተዘጋጀ መስኖ የሚሄድበት የዳይቨርሽን ካናልም ጉዳት ሊደርስበት ችሏል፡፡ ከታኅሳስ ወር ጀምሮ በተደጋጋሚ በመከሰት ላይ በሚገኘው አደጋ የደረሱ ጉዳቶችን በተመለከተ ምን ያህል እንደሆነ ወደ ሥፍራው ያቀኑ የትምህርት ክፍሉ ባለሙያዎች የሚያመጡትን ውጤት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

‹‹ወደ ስኳር ፋብሪካው የሚወስደው መንገድ በመሬት መንቀጥቀጡ የመሰንጠቅ አደጋ ደርሶበታል፤›› የሚሉት ኃላፊው፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና የድርጅቱ ሠራተኞች ሥፍራውን ለቀው አዋሽ ሰባትና አዋሽ አርባ ወደሚባሉ አካባቢዎች መሄዳቸውንም አስታውቀዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎችን ከቦታው በማንሳት ሌሎች አካባቢዎች ላይ ለማሥፈር፣ በክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሸን የሚመራና የሰመራ ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡