ኤልያስ ተገኝ

January 5, 2025

በገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

አምራችና ገጣጣሚ ኢንዱስትሪዎች ይበልጥ ተወዳዳሪ ሆነው ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት እንዲሁም ውጤታማ ለማድረግና የታሪፍ ከለላ እንዲኖራቸው በሚል፣ የገንዘብ ሚኒስቴር የጉምሩክ ታሪፍ ማሻሻያ ማድረጉ ታወቀ፡፡

ገንዘብ ሚኒስቴር የጉምሩክ ታሪፍ ማሻሻያ  አደረገ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
አቶ ደበሌ ቀበታ

ገንዘብ ሚኒስቴር ተግባራዊ እንዲደረግ በሚል ያዘዘው የጉምሩክ ቀረጥ ማስከፈያ ማሻሻያ ከታኅሳስ 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ የተወሰነ ሲሆን፣ ጉምሩክ ኮሚሽንም ለሁሉም የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ለሚፈፀምባቸው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በጻፈው ደብዳቤ፣ በጉምሩክ ማሻሻያው መሠረት አገልግሎት እንዲሰጡ አሳስቧል፡፡

የታሪፍ ምጣኔያቸው ከተሻሻለ የዕቃ ዓይነት ውስጥ ለሞተር መኪናዎች/ለስቴሽን ዋገኖችና ለሽቅድድም መኪናዎች ጭምር የሚያገለግል 25 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ልክ እንዲከፍል የተባለ ሲሆን፣ ለአውቶቢስ ወይም የጭነት መኪናዎች የሚያገለግሉ ዓይነት ዕቃዎች በተመሳሳይ ልክ የጉምሩክ መጠን የታሪፍ ምጣኔያቸው መሻሻሉ ታውቋል።

በሌላ በኩል በታሪፍ ቁጥር 8703 ውስጥ 2321 ላይ የሚመደቡ ተሽከርካሪዎች 25 በመቶ የታሪፍ ምጣኔ እንዲሁም በተመሳሳይ 2322 የሚመደቡ ተሽከርካሪዎች 35 በመቶ የታሪፍ ምጣኔ አንዲኖራቸው ማሻሻያ ያደረገው የገንዘብ ሚኒስቴር፣ በቀጥታ ለምግብነት የሚውል ዘይት ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ ሆኖ እንዲገባ የተላለፈው ውሳኔ ተፈጻሚነት እስከቀጠለ ድረስ፣ በግብዓትነት የሚያገለግሉ በታሪፍ መጽሐፉ ምዕራፍ 15 ውስጥ የተዘረዘሩ ዘይቶች ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ እንዲሆኑ ተወስኗል።

የገንዘብ ሚኒስቴር በተጨማሪም የድንጋይ ከሰል ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም. የተላለፈው ውሳኔ የተሻረ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ በጉምሩክ ታሪፍ ደንቡ በተቀመጠው የታሪፍ ምጣኔ መሠረት ተግባራዊ እንዲደረግ አሳስቧል። አክሎም ውሳኔው ከመሻሩ በፊት የተገዛ ስለመሆኑ በጉምሩክ ኮሚሽን ሲረጋገጥ፣ እንዲሁም አሁን ላይ የተደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ከገንዘብ ሚኒስቴር ወጪ ከሆነበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠሩ 30 ተከታታይ የሥራ ቀናት ውስጥ ለጉምሩክ ኮሚሽን ቀርበው ተቀባይነት የሚያገኙ የድንጋይ ከሰልና ፔት ኮክ ለመጨረሻ ጊዜ ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ መስተናገድ እንደሚችሉ ጠቅሷል።

በታሪፍ ደንብ 87 ከአንቀፅ 87.02 እስከ 87.04 እንዲሁም 87.11 የሚመደቡ ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች የተመረቱበት የጎርጎሮሳውያን የዘመን መቁጠሪያና ቀንና ወር በትክክል ማወቅ የሚቻል ከሆነ፣ ተሽከርካሪዎቹ ከተመረቱበት ቀን ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ የጉምሩክ ክልል እስከደረሱበት ቀን ድረስ ሲቆጠር ከሦስት የጎርጎሮሳውያን የዘመን መቁጠሪያ ዓመታት ያልበለጠ ከሆነ እንደ አዲስ ይቆጠራል የሚል መግለጫ  ቀርቧል።

አሊያም ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች የተመረቱበት የጎርጎሮሳውያን የዘመን መቁጠሪያ ቀንና ወር በትክክል ማወቅ የማይቻል ከሆነ፣ በጎርጎሮሳውያን የዘመን መቁጠሪያ ዓመት የመጀመሪያው ወር የመጀመሪያ ቀን እንደተመረተ ተቆጥሮ ወደ ኢትዮጵያ የጉምሩክ ክልል እስከደረሰበት ቀን ድረስ ሲቆጠር ከሦስት የጎርጎሮሳውያን የዘመን መቁጠሪያ ዓመት ያልበለጠ ከሆነና ከውጭ እስከ ኢትዮጵያ የጉምሩክ ክልል ድረስ የተነዳው ርቀት ከ4,000 ኪሎ ሜትር እስካልበለጠ ድረስ ብቻ እንደ አዲስ የሚቆጠር ይሆናል፣ ሲል ገንዘብ ሚኒስቴር ወስኗል።

በገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ተፈርሞ ለጉምሩክ ኮሚሽን የተላከው የጉምሩክ ታሪፍ ማሻሻያ በጉምሩክ ኮሚሽን የመረጃ ቋት አድራሻ ሳጥን ውስጥ የተጫነ መሆኑ ተገልጿል።