በአፍሪካ አገሮች ዋንጫ ኢትዮጵያን የሚወክለው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት (ፎቶ እግር ኳስ ፌዴሬሽን)

ስፖርት ኢትዮጵያ በቻን የአፍሪካ ዋንጫ በዳኝነት ትሳተፋለች

ደረጀ ጠገናው

ቀን: January 5, 2025

ሦስቱ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ታንዛኒያ፣ ኬንያና ዑጋንዳ በጣምራ የሚያዘጋጁት የ2024 የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን)፣ ጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ይጀመራል፡፡ በብሔራዊ ቡድኗ ያልተሳካላት ኢትዮጵያ፣ በአንድ የእግር ኳስ አመራር እንደምትወከል የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በድረ ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡

በአፍሪካ የውስጥ የሊግ ውድድር የሚጫወቱ ብቻ የሚሳተፉበት የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ፣ ከቀናት በኋላ የሚካሄደው መደበኛው የአፍሪካ ዋንጫ በተከናወነ በቀናት ልዩነት የሚካሄድ የጨዋታ መርሐ ግብር መሆኑ ይታወቃል፡፡

የቻን ዋንጫ አኅጉራዊው ተቋም የአባል አገሮች የውስጥ ሊጎቻቸውን እንዲጠናከርና ‹‹አፍሪካውያን ለአፍሪካውያን›› በሚል የጀመረው ሲሆን፣ ውድድሩ በካፍም ሆነ በዓለም አቀፉ ተቋም መደበኛ የውድድር ፕሮግራም እንደሌለው ይነገራል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ካፍ በቅርቡ ሞሮኮ ላይ ባደረገው ስብሰባ የሻምፒዮናውን አስፈላጊነት በሚመለከት ሰፊ ውይይይት ካደረገ በኋላ ነው ውድድሩ ከቀናት በኋላ እንዲቀጥል ውሳኔ ላይ የደረሰው፡፡

ይሁንና 2024 አኅጉራዊ ውድድሮችን ጨምሮ ዓመቱን በሙሉ በውጤት ማጣት ውክልና አጥታ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ በአንድ ረዳት የእግር ኳስ አመራር እንደምትወከል ካፍ አሳውቋል፡፡ ውድድሩን በጨዋታ አመራርነት እንዲመሩ ከተመረጡ የእግር ኳስ ዳኞች መካከል፣ ረዳት ኢንተርናሽናል ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት አንዱ ሆኖ ተመርጧል፡፡