
By አንባቢ
January 5, 2025
በተቐራቒራ ማሕፀን የተገኙት ታላቅ ዓሊም ቡርከይ ሙሐመድ ዓሊ
Byአንባቢ
January 5, 2025
ተቐራቒራ ከዓብይ ዓዲ በስተሰሜን ምሥራቅ ማለትም ከወርቅ አምባ በስተምሥራቅ የምትገኝ መንደር ስትሆን፣ ይህች መንደር ከ700 እና 800 ዓመታት በፊት እንደተቆረቆረች ይነገራል፡፡
የፉቱሑል ሐበሽ ጸሐፊ ዓረብ ፈቂህ እንደሚነግሩን፣ ኢማም አሕመድ ኢብራሂም በ«ትግራይ» ምድር «ቐርቐራህ» የተባለች ምድር ላይ የሰፈሩ ሲሆን ስንዴና ማር የሚበዛባት ሰፊ አገር ናት፡፡ በጋራው አካባቢ ላይ የሚኖሩ ሙስሊሞችን ረሃብ ጎድቷቸው ነበርና አላህ «ቐርቃራህ» ላይ ከረሃብ ገላገላቸው፡፡ ኢማሙ በእዚያው ሥፍራ ተቀምጠው ወዚር ሙጃሒድን ስንቅ እንዲያመጣ ወደ «አስገራ» እና «አበርገለ» ወደሚባሉት አገሮችና ወደ አካባቢያቸው ላኩት፡፡
በፉቱሑል ሐበሽ እንደተጠቀሰውም አበርገለ በደቡብ ተምቤን የጭላይ የምትገኝ ስፍራ ስትሆን ማርና ወተት የሞላት፤ የትግራይና የአገው ሕዝብ የሚኖርባት ናት፡፡ የጥንት የንግድ መስመርም ከምጽዋ ደባራዋ፣ ሐዘሞ ዛና ማይቀነጣለል፣ ተምቤን ዓበርገለ፣ ሰቆጣ፣ ደሃና፣ በለሰሳ፣ ጎንደር… እያለ ይሄዳል፡፡ ወደ ሸዋ መስመርም ከሰቆጣ በመነሳት በላስታ በኩል አድርጎ፣ ዋድላ ደላንታ አድርጎ መጓዝ ነው፡፡ ወደጎንደር የሚወስደው መንገድም ዓበርገለ፣ በለሳ፣ ደንብያ፣ ጎጃም እያለ ሊሄድ ይችላል፡፡
የተምቤን ዓብይ ዓዲ ነዋሪው ሸኽ በድሩ መሐመድ ያሲን (አላህ ይርሐማቸው) በ2000 (በኛ አቆጣጠር) ለዚህ መጽሐፍ አዘጋጅ እንደነገሩት ዛሬ ዓግበ እየተባለ የሚጠራው ስፍራና ወንዝ ላይ የሚገኘው ቤተክርስቲያን ጥንት «እንዳጀነት ጎራ» እየተባለ የሚጠራው የሙስሊሞች መንደርና መቃብር ነበር፡፡ አገሩም በጣም የለማ አትክልትና ፍራፍሬ የሚታፈስበት ገነት ይመስል ነበር፡፡
የቡርከይ ሙሐመድ ዓሊ የልጅ ልጅ የሆኑት ሙሐመድ ዓብደላ ‹‹መሐመድ ዓብደላ፣ ኢብን ሙሐመድ ኑር፣ ኢብን ጀበርቲ፣ ኢብን አሕመዲን፣ ኢብን መሐመድ፣ አቢን ዓብደላሂ፣ ኢብን ቡርከይ መሐመድ ዓሊ›› በማለት ስለ ትውልዳቸውና ስለ ታላቅ ቡርከይ ሙሐመድ ዓሊ ኢብን ሙሐመድ ኑር፣ ሙሐመድ ኢብን ቡርከይ ሙሐመድ ዓሊ›› ትውልድ ያስረዳሉ፡፡
እዚህ ላይ የነበለትን (ዓዲርጉድ) እና የተቐራቒራን ግንኙነት የበለጠ ለማስተሳሰር ይቻል ዘንድ ከኸቢር ሳሊሕና ከተቐራቂራው ቡርከይ ዓሊ (ከቢር) ማለትም የቡርከይ ሙሐመድ ዓሊ አባት ጋር የተፈጸመውን የጋብቻ ትስስርን በሚመለከት ሸህ በድሩ እንዳሉት፣ የተቀራቂራው ሸኽ ሙሐመድ ኑር አል-ግመላ ከዓዲርጉዱ ዓቢይ ሷሊህ ጋር በጋብቻ ለመተሳሰር ይፈልጉና «ወንድ ልጅ ከኛ ሴት ልጅ ከናንተ አድርገን በጋብቻ እንተሳሰር?» የሚል መልዕክት የያዙ ሽማግሌዎችን ይልካሉ፡፡ ዓቢይ (ከቢር) ሷሊሕም (ምናልባት ሌላ የሚጠብቁት ራዕይ ስለነበር ሊሆን ይችላል) «ለናንተ የሚሆን ልጅ የለንም» የሚል መልስ ሰጥተው ሽማግሌዎቹን ይመልሳሉ፡፡ ሽማግሌዎቹ እንደተመለሱም ዓቢይ (ከቢር) ሷሊሕ በሐቲፍ (በህልም) አንዲት ልጅ አቅፈው ሲያንሰራስሩ አዩ፡፡ «ይህች ልጅ የማን ናት?» ብለው ሲጠይቁም «ይህችማ ከነዚያ አንጋባም ብለህ ከመለስካቸው የተቀራቂራ ሰዎች የምትወለድ ናት» የሚል መልስ አገኙ፡፡ ወዲያውም በድርጊታቸው በመጸጸት ሽማግሌ ላኩና «ሴት ልጅ ከኛ፣ ወንድ ልጅ ከናንተ አድርገን በጋብቻ እንተሳሰር» የሚል መልእክት የያዙ ሽማግሌዎችን ላኩ፡፡ የዓቢይ ዓዲ ሰዎችም ድሮውንም ከኸቢረ ሷሊሕ ጋር በጋብቻ ለመተሳሰር ይፈልጉ ስለነበር «መርሐባ» በለው ጋብቻውን ፈጸሙ፡፡ ከዓዲርጉዱ ከቢር ሷሊሕ ሴት ልጅና እና ከተቐራቒራው ታላቅ ዓሊም ቡርከይ ሙሐመድ ኢብን ዓሊ ተወለዱ፡፡
ቡርከይ ሙሐመድ ዓሊ ስለነበሩበት ዘመን ለማወቅ ስለ ከቢር ሷሊሕ ማወቅ ይጠቅማል፡፡ ስለከቢር ሷሊሕ 1.‹‹ኢማም አሕመድ ኢብራሂም›› 2. ‹‹ዓይን አብራዎቹ››፣ 3. ‹‹ኮናባ›› 4. ሌላው የኢትዮጵያ ታሪክ ገጽታ በሚሉ አርእስት ለኅትመት ባበቃኋቸው መጻሕፍት እንደጠቀስኩት ሁሉ አንድም በኢማም አሕመድ ኢብራሂም ጊዜ (1486-1535) የነበሩ ሙርሺድ፣ ወይም ከሙርሺዶቹ መካከል አንዱ የፈቂ ሙሳ አባትና የከቢር ሷሊሕ አባት የሆኑት (የአባድር የልጅ ልጅ የሆኑት) ዓብይ ሙሐመድ ኑር ልጅ ናቸው፡፡
ከዲር ታጁ ሙራድ ካሚል (ዶ/ር) ‹‹ሲረተል ሐበሻ ሊዓል-ሐይሚ (ገጽ 94) ጠቅሶ እንደጻፈው፣ በ1058 ወርሃ ዙል ሒጃ (ፌብሩዋሪ 1648) አዛዡን ተጓድነን ወደ መኖሪያቸው አካባቢ ሄድን፡፡ ሰፈሩ ሕንጣሎ በሚባል ከፍተኛ ተራራ ውስጥ ተከልሏል፡፡ ይህች አገር ስሟ እንደርታ ነው፡፡ ለ40 ቀናት ያህል በዚች ስፍራ ቆየን፡፡ በዚህ እያለን ዒደል ዓረፋ ሆኖ ስለነበር ወደ አገሪቱ ደልዳላ ሰፍራ አብረው ከተጨመሩት ሙስሊሞች ጋር ሆነን ለመስገድ ወጣን፡፡ ባላገሮቹ እየተገረሙብን እንደሰገዱት ሁሉ እኛም እየተገረምንባቸው ሰገድን፡፡
እዚያው እያለን አል-ከቢር ሷሊሕ በሚል ስም የሚታወቁ ሊቅ ደረሱ፡፡ ከንጉሣችን (ሙዓየድ ቢላህ) ለእነርሱ የተላኩ መጻሕፍትና በውድ ጌጦች የተጌጡ ምንጣፎችን ሰጠናቸው፡፡ ከነርሱ ውስጥ ውስኖቹ ዓረብኛ ይናገሩ ነበር፡፡ አብዛኛውን መረጃ ያገኘነው ከእነርሱ ጋር ከነበረው ከቢር ኸይረዲን የተባለ ሻፊዒያ የነበረ ሲሆን ከአል-ከቢረ በዕውቀቱ ላቅ ይላል፡፡ ከቢር ሷሊሕ ግን በሚናቸው ከሱ ይልቃሉ ይላሉ፡፡
በዚህ ታሪክ መሠረት የመኖቹ ሕንጣሎ ሆነው ለከቢር ሷሊሕ የተላከላቸውን ስጦታ ለማስረከብ መልእክት አስልከውባቸው ሊሆን ይችላል። የመኖቹ ወደ ዓዲርጉድ ያልሄዱት በወቅቱ ጥቅጥቅ ያለ ደን ስለነበረ፣ በመንገዱም ቀማኛ ስለማይጠፋ፣ ወንዝና ሸለቆ የበዛበት ስለሆነ የአገሬው ሰው ስለከለከላቸው ሊሆን ይችላል። 40 ቀናት የጠበቁትም ከሕንጣሎ ዓበር ገለ፣ ከዓበር ገለ ዓብይ ዓዲ፣ ከዓብይ ዓዲ ገረዓልታ፣ ከገረዓልታ ነበለት (ዓዲርጉድ) ከ120 ኪሎ ሜትር ስለማያንስ በበቅሎና በፈረስ መምጣት ከባድ ስለሆነ ይሆናል። ይህ ግን በኔ ግምት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ በጥናት መረጋገጥ ይኖርበታል።
ሆነም ቀረ፣ የቡርከይ ሙሐመድ ዓሊ ጋብቻ የሆኑት ከቢር ሷሊሕ በ1640ዎቹ ከነበሩ የተከበሩ ሊቃውንት ሲሆን፣ ሁለቱም የአንድ ዘመን ሰዎች መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡ በዚህ ስሌት መሠረት ከቢር ሷሊሕና ቡርከይ ሙሐመድ ዓሊ ከኢማም አሕመድ 100 ዓመት በኋላ የነበሩ ስለሆኑ ‹‹ምናልባት የኢማም አሕመድ ሙጃሂዶች የልጅ ልጆች ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል›› ብሎ መገመት ይቻላል።
የአው አባድር ሲልሲላ ቀጣይ የሆኑት ቡርከይ ሙሐመድ ዓሊ (አውራዳቸው ስለሚገልጽ ነው) በኢትዮጵያ እስልምና ታሪክ ሁነኛ ምዕራፍ ሊሰጣቸው የሚገባ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡
ከዓብይ ዓዲ በስተሰሜን ምሥራቅ ከወርቅ አምባ በስተምሥራቅ በምትገኘው ተቐራቒራ መንደር አካባቢ ፍርስራሽ መንደሮች ይኖሩ እንደሆነ በትኩረት ማየትና ማጥናት ያስፈልጋል።
ኢማም አሕመድም ወደ ተምቤን የመጡት የሸዋ ትግራይ መንገድን ተከትለው ነው፡፡ እዚህም ስፍራ ማለትም ተቐራቂራ ሁለት ዓመታት ያህል ኖረዋል፡፡ እሳቸውም ሲኖሩ የሸሪዓ ሕጋቸውን አስፍነው መቀመጣቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የሸሪዓ ሕግ ተግባራዊ የሚሆነው በፈቂሆች የሚመራ ነው፡፡ ስለዚህ የፈቂህ ምህመድ/ሙሐመድ ኑር በተቐራቂራ መኖርና የኢማም አሕመድ በዚያ አካባቢ መኖር ይያያዝ እንደሆነ ለመዳሰስ ትውፊቱን አንድ በአንድና በስፋት መመርመር ያስፈልጋል፡፡
እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት ግን ሰይድ ቡርከይ የከቢር ሷሊሕ አማች ከመሆናቸውም በላይ እስልምናን በሰፊው ያስፋፉ፣ በርካታ መጻሕፍትን የጻፉ፣ እስካሁንም ሥራዎቻቸው የሚነገርላቸውና የሚዘከርላቸው ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ በዘመናቸው ወደ ሐጅ የሚሄዱ የሰሜን ኢትዮጵያ ሰዎች እርሳቸውን ጎብኝተው ይሄዱ እንደነበር ሲታወቅ ካለፉም በኋላም መቃብራቸውን ጎብኝቶ መሄድ የተለመደ ነበር፡፡
በመሠረቱ የዓዲርጉድና የተቐራቒራ ዝምድና ቀደም ያለ መሠረት ሲኖረው ሸኽ በድሩ ጨምረው እናቴ ነግራኛለች ብለው እንዳስረዱኝ ሌላው አያታቸው የመጡት በበሪ ሳዕዲዲን አድርገው ከድሆኖ ሲሆን፣ እሳቸውም ደብሪ ዒሳና በወርቃንባ መካከል ያለው ስፍራ ተቀመጡ፡፡ ይህም ስፍራ በር ሳዕዲዲን እየተባለ በአካባቢው ሙስሊሞች ዘንድ ይጠራ ነበር፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በለዎች ከድሆኖ መጥተው አክሱም፣ ሽሬ፣ ዓድዋ፣ ተምቤን አካባቢ እንደተቀመጡ እንረዳለን፡፡ ዓድዋ፣ አክሱም፣ ተምቤንና ዓጋሜ አጎራባች አውራጃዎች ሲሆኑ በሃይማኖትም በቋንቋም በባህልም በታሪክም አንድ ስለሆኑ የሳዕደዲን ወገኖች የሆኑ በለዎች ከዓብይ ዓዲ፣ ከሽሬ፣ ከአክሱም አካባቢ ወደ ደንከል ግዛት ሄደው ወይም ከዚያ መጥተው እንደሆነ ፍንጭ ይሰጣል፡፡
በታሪኩ ውስጥ ሌላው ትኩረት የምንሰጥበት ጉዳይ ዓግበ የአጀሞ ሸህ ግዛት እንደነበረች የሚጠቁመው ነው፡፡ ለመሆኑ የአጀሞ ሸህ ማንናቸው? የዓዲ ኸቢረ ሰዎች እንደሚሉት የአጀም ሸህ ከበር ሳዕደዲን ማለትም ከወርቃምባ ባሻገር ዛሬ በዓጋሜ ክልተ-አውላዕሎ፣ ዓድዋ፣ ዓብይ ዓዲና ዓበርገለ አካባቢን ሁሉ ሲገዙ የነበሩ ዋና ከተማቸውም «በዓግበ» የነበሩ ገዥ/አቅኚ ናቸው፡፡
ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡